በትግራይ ክልል አጣሪዎችና ሚዲያዎች እንዲገቡ በመንግሥት ላይ ጫና እንዲደረግ ጥሪ ቀረበ

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS
የኢትዮጵያ የውጭ አጋሮች የመብት መርማሪዎችና ሚዲያዎች ያለ ምንም እክል በመላው ትግራይ ክልል እንዲንቀሳቀሱ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።
በተለያዩ የዓለማችን አገራት ውስጥ ግጭቶችን የሚከታተለው አለም አቀፉ ክራይሲስ ግሩፕ ነው ይኼንን ጥሪ ያቀረበው።
ቡድኑ "Finding a Path to Peace in Ethiopia's Tigray Region" በሚል ርዕስ ባወጣው የ19 ገፅ ሪፖርት አገሪቷ ወደ ሰላም በዘላቂነት የምትመለስበትን፣ ከትግራይ ክልል ጋር ያለው ግጭት በቋሚነት የሚፈታበትን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዮችን አካቷል።
ቡድኑ ለአሜሪካ መንግሥት፣ ለአውሮፓ ህብረትና ለአፍሪካ ህብረት እንዲሁም ሌሎች አጋሮች የመብት ተመራማሪዎችና ሚዲያዎች ያለምንም እክል ገብተው ስራቸውን እንዲያከናውኑ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት እንዲፈቅዱ ጫና እንዲያደርጉ ጠይቋል።
ተፈፀሙ የሚባሉ ጥሰቶች በሙሉ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ እነዚሁ አካላት ጫና ሊያደርጉ ይገባል ብሏል።
የተረጋጋ ፖለቲካ ለመፍጠር ባለስልጣናቱ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን ጨምሮ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ለሚጠይቀው የህይወት አድን እርዳታ ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያ መንግሥት በሩን ሊከፍት እንደሚገባም በሪፖርቱ አካቷል።
በክልሉ ውስጥ በፌደራል መንግሥት የተቋቋመው የአዲሱን ጊዜያዊ አስተዳደር ባለስልጣናት ጨምሮ፣ የተለያዩ የረድዔት ድርጅቶች እያስጠነቀቁ ያለው የሰብዓዊ ቀውስ ከዚህ እንዳይከፋ እንዲሁም በርካቶችን ከሞት ለመታደግ የተለያዩ የረድዔት ድርጅቶች ያለ ምንም እክል ሊንቀሳቀሱና እርዳታቸውን ሊለግሱ እንደሚገባም አስምሯል።
ለሳምንታት ያህል የዘለቀውን ውጊያ ተከትሎ የፌደራል መንግሥቱ የክልሉን አስተዳዳሪ ህወሃት ከስልጣን በማስወገድ የክልሉን መዲና እንደተቆጣጠረና ድል እንደተቀናጀ አሳውቋል።
ምንም እንኳን የፌደራል መንግሥቱ ጦርነት እንዳለቀ ቢያውጅም የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ ሌሎች ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ውጊያው መቀጠሉን ነው።
በዚህ ውጊያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዳለቁ፣ በትግራይ 1/3ኛ የሚሆነውን ነዋሪ አፈናቅሏል፣ በርካታ ጥሰቶችም በሁሉም ወገኖች ተፈፅመዋል ያለው ሪፖርቱ እንዲሁም 4.5 ሚሊዮን የሚሆኑ የክልሉ ነዋሪዎች አስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።
የፌደራል መንግሥቱ፣ ከስልጣን የተወገዱት የትግራይ አመራሮች፣ ሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና አቀንቃኞች መሬት ላይ ስላለው ነገር የተለያየ እውነታን መናገራቸውን ተከትሎ ልዩነቶች እየሰፉ ነው፤ ለሚያስፈልገው እርዳታም እንቅፋት ሆኗል ይላል ሪፖርቱ።
ይህንንም ለማስተካከል መደረግ ያለበት ብሎ ሪፖርቱ ያሰፈረው የፌደራል መንግሥቱ ጋዜጠኞች ሪፖርት እንዲያደርጉ እንዲሁም ሪፖርት የተደረጉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ተጨማሪ ምርመራ እንዲያደርግ መሆን አለበት።
ከዚህም በተጨማሪ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ከፍተኛ ኮሚሽነር እንዲሁ የራሱን ምርመራ እንዲያከናውን መፈቀድ እንዳለበትና መንግሥት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባኤን ጨምሮ በአገሪቷ ላሉት የሲቪል ሶሳይቲ ድርጅቶች፣ እንዲሁም ሂውማን ራይትስ ዋች፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ለመሳሰሉ አለም አቀፍ ድርጅቶች በሩን ሊከፍት ይገባል ብሏል።
በተለያዩ ሪፖርቶች የኤርትራ ወታደሮች መሳተፋቸው የተጠቀሰ ሲሆን በቅርቡ የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ክልል በአስቸኳይ እንዲወጡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት (ስቴት ዲፓርትመንት) የአውሮፓ ህብረት መጠየቃቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ በተደጋጋሚ ይህ ህግ የማስከበር ዘመቻ እንደሆነና በትግራዩ ግጭት የኤርትራ ጦር አለመሳተፉን ማሳወቁ የሚታወስ ነው።
የአውሮፓ ህብረትን ተከትሎ አሜሪካም ሆነ ሌሎች ተባብረው የሰብዓዊ ረድዔት ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ እርዳታ እንዲደርስ እንዲያደርጉም ካስፈለገም ከትግራይ ኃይሎች ጋር እንዲደራደሩ መሆን እንዳለበት ሪፖርቱ አቅጣጫ ያስቀምጣል።
የፌደራል መንግሥቱ "የኢትዮጵያን ለውጥ ለመቀልበስና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሚሞክሩ ኃይሎች ናቸው ብሎ የሚጠራቸው የህወሃት ኃይሎች" ጋር ምንም አይነት ድርድር አይኖርም ይላል።
በአንፃሩ "የወንጀለኞች ቡድን" የጠራቸውን ግለሰቦች ወደ ፍትህ መቅረብ አለባቸው ማለቱ ይታወሳል።
የህወሃት ኃይል ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት በአገሪቷ ላይ ለደረሱ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲሁም በባለፉት አመታት ለተነሱ የብሔር ግጭቶችና አለመረጋጋቶች የፌደራል መንግሥቱ ተጠያቂ አድርጓቸዋል።
የህወሃት ከስልጣን መወገድ ለክልሉ ዘለቄታዊ ሰላም ያመጣል ብሎ የሚያምነው የፌደራል መንግሥት የትግራይ ክልል መሰረተ ልማት ለመገንባትና በግጭቱ ወቅት የወደሙ ልማቶችን እንደገና ለመቀጠል ጥረት እያደረግኩ ነው በማለት በተደጋጋሚ በመግለጫዎቹ አስታውቋል።
ሪፖርቱ በበኩሉ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ከተፈለገ "የፌደራል መንግሥቱ የትግራይ ተወላጆችን ከአዲሱ አስተዳደር ጋር በጋራ በመሆን ትግራይን እንደገና እንዲገነቡ ሊያሳምናቸው ይገባል" ብሏል።
አሁን ባለው ሁኔታ በፌደራል መንግሥቱ በተሾመው አዲሱ አስተዳደር ላይ በክልሉ የተነሳው ተቃውሞን ለመቀልበስ መንግሥት ማድረግ አለበት ያላቸውንም ሪፖርቱ አስቀምጧል።
የአካባቢውን ትብብር ለማሳደግ የፌደራል መንግሥቱ የኤርትራን ወታደሮች እንዲያስወጣ እንዲሁም ለበርካታ የትግራይ ተወላጆች አልዋጥ ያለውን የአማራ የግዛት መቆጣጠር እንዲያስመልስ ማድረግ አለበት የሚል ነጥብ አስቀምጧል።
በአማራ በኩል የይገባኛል ጥያቄዎች የሚነሳባቸውን የደቡብና ምዕራብ ግዛቶች በፌደራል የድንበር አጣሪ ኮሚሽን ተገምግሞ በፖለቲካዊ ድርድር መፍትሄ እንዲያገኝ መደረግ እንዳለበትም አቅጣጫ አስቀምጧል።
በተለይም በተለያዩ ሪፖርቶች ላይ በግጭቱ ተሳታፊ መሆኑ የተጠቀሰው የኤርትራ ሰራዊት ከአካባቢው እንዲወጣ ለማድረግ በኤርትራው መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ ላይ የእርዳታ መቋረጥን ጨምሮ ሌሎች ጫናዎችን እንዲያደርጉ ቡድኑ ለአውሮፓ ህብረትና ለአለም አቀፍ አካላት ጥሪውን አቅርቧል።
ከዚህም በተጨማሪ የባይደን አስተደዳደር እንዲሁ የኤርትራ ሰራዊት እንዲወጣ ያደረገውን ጥሪ እንዲደግምና በአስመራ ላይ ተፅእኖ ማድረስ የሚችሉትን አጋሮቹ የሆኑትን የተባበሩት አረብ ኤምሬትስና ሳዑዲ አረቢያ በኩል መልዕክት እንዲደርስ ማድረግ አለበት ይላል።
በአጠቃላይም "በዋናነት የኢትዮጵያ ተፎካካሪ ልሂቃን በዋናነት የትግራይን በራስ የማስተዳደር መብት እንዲሁ ሰፋ ባለ መልኩ ሲታይ ደግሞ በማዕከላዊ መንግሥትና በክልሎች መካከል ሊኖር የሚገባውን የስልጣን ክፍፍል፣ በፌደራል ስርዓቱ ላይ የብሔር ሚና ምን ሊሆን ይገባዋል የሚለው ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ እየተካሄደ ያለው ሽግግር ወደ ከፋ ቀውስ ከማምራቱ በፊት፤ የኢትዮጵያን ስር የሰደደና መሰረታዊ ፖለቲካዊ ክፍፍልን ለመፍታት ሁሉን ያካተተ ውይይት አስፈላጊነትን" አስምሯል።
በፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል ለረዥም ጊዜ የዘለቀው መቃቃርና አለመግባባት ተካሮ የህወሓት ኃይሎች የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል በማለት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የፌደራሉን ጦር ወደ ትግራይ ማዝመታቸው ይታወሳል።











