ትግራይ፡ መንግሥት “20 ሺህ የኤርትራ ስደተኞች የገቡበት ጠፋ” የተባለው ሐሰት ነው አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢትዮጵያ መንግሥት ከ20 ሺህ የኤርትራ ስደተኞች በላይ የገቡበት ጠፋ ተብሎ በማሕበራዊ ሚዲያ የተሰራጨው መረጃ የሐሰት ነው አለ።
ከአንድ ሳምንት በፊት በትግራይ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ 20 ሺህ የኤርትራ ስደተኞች ከህጻጽ እና ሽመልባ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያ ጠፍተዋል የሚል ዜና በበርካታ መገናኛ ብዙሃን ተዘግቦ ነበር።
በተጨማሪም በትግራይ ክልል የሚገኙ ሁለት የኤርትራውያን ስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎችን በቅርቡ ልትዘጋ መሆኑን የስደት እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ላይ አስታውቋል።
እንደ ኤጀንሲው ከሆነ የሚዘጉት መጠለያ ጣብያዎች ሽመልባ እና ህጻጽ የተሰኙት ሲሆኑ ለዚህም ምክንያት ነው ያሉትን ዘርዝረዋል።
ሽመልባ የተመሰረተበት ቦታ ከኢትዮ-ኤርትራ ድንበር በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ በመሆኑ ለመዘጋቱ በምክንያትነት ሲጠቀስ፣ በበረሃማ ቦታ የሚገኘው ህጻጽ፤ ለኑሮም ሆነ ለስደተኞች መጠለያነት አመቺ ባለመሆኑ በተመሳሳይ እንደሚዘጋ ኤጀንሲው ገልጿል።
በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት የስደተኛ መጠለያ ጣቢያ ከአገራት አዋሳኝ ድንበር ቢያንስ በ50 ኪሎ ሜትር እርቀት ላይ መገንባት እንዳለበት እንደሚያስቀምጥ ተገልጿል።
የህወሓት ኃይሎች ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን ተከትሎ በክልሉ ፌደራል መንግሥት "የሕግ ማስከበር ዘመቻ" እያካሄደ መሆኑ ይታወቃል።
ከዚህ ግጭት መቀስቀስ በኋላ በርካታ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በክልሉ ስለተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ አሳሳቢነት እየተናገሩ ሲሆን ከህጻጽ እና ሽመልባ ስደተኛ ጣብያዎችም ጦርነቱን የሸሹ 20 ሺህ ኤርትራውያን የደረሱበት እንደማይታወቅ ተዘግቦ ነበር።
የስደት እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ተስፋሁን ጎበዛይ ከሁለቱ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የጠፋ ስደተኛ የለም ሲሉ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ዛሬ በሰጡት መግለጫ “19 ሺህ ስደተኞች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳሉ እናውቃለን። በረሃብ እና በሕመም የተጎዱ ሊኖሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ የጠፋ ሰው የለም” ብለዋል።
በኢትዮጵያ ከ200 ሺህ በላይ ኤርትራውያን ስደተኞች እንዳሉ ይገመታል። የስደት እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ተስፋሁን ጎበዛይ በትግራይ ክልል ደግሞ ከግጭቱ በፊት ከ92 ሺህ በላይ ስደተኞች እንደነበሩ ተናግረዋል።
ከእነዚህ መካከል 49 ሺህ የሚሆኑት በክልሉ በሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ ይኖሩ ነበር። አቶ ተስፋሁን በትግራይ ክልል በሚገኙቱ ዓዲ ሃሩሽ፣ ማይ ዓይኒ፣ ሕጻጽ እና ሽመልባ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ግጭቱ ሲከሰት የእርዳታ አቅርቦት ተቋርጦ ነበረ ብለዋል።
“በሕግ የማስከበር ስራው ወቅት ላይ በተለያዩ ምክንያቶች የእርዳታ ሥራ ተስተጓጉሏል። በተለይ በሕጻጽ እና ሽመልባ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በርካታ ኦፕሬሽን ይካሄድ ስለነበረ ሥራ መስራት አልተቻለም። በስፍራው የነበሩ ሰራተኞች አካባቢውን ጥለው ወጥተዋል። ሰብዓዊ ድጋፍ ያደርጉ የነበሩ ተቋማትም ሰራተኞቻቸውን ከስፍራው አስወጥተዋል። በእነዚህ ምክንያቶች በአራቱ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ሥራ ቆመ” ብለዋል።
በዚህም ምክንያት በመጠለያ ጣቢያዎቹ የነበሩ ስደተኞች ለከፋ ችግር ተጋልጠው ነበር። በተለይ በሕጻጽ እና ሽመልባ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የነበሩ ስደተኞች፤ መጠለያ ጣቢያዎቹን ጥለው ወጥተው ነበር ሲሉ ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።
ከመጠለያ ጣቢያዎቹ የወጡ ስደተኞችን ወደ መጠለያ ጣቢያዎች ለመመለስ በተሰራው ሥራ ወደ 5ሺህ የሚጠጉ “ሠላም ወዳለበት” ዓዲ ሃሩሽ እና፣ ማይ ዓይኒ መጠለያዎች መመለስ እንደተቻለ የስደት እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ተስፋሁን ጎበዛይ ተናግረዋል።
3ሺህ ስደተኞች ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚገኙ እና የተቀሩት ስደተኞች ደግሞ በትግራይ እና አማራ ክልል ከተሞች ተበታትነው እንደሚገኙ አስረድተዋል።
ተበታትነው የሚገኙ ስደተኞችን አገልግሎት ማግኘት ወደሚችሉበት አንድ ስፍራ የመሰብሰብ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አቶ ተስፋሁን ተናግረዋል። በሌላ በኩል ዳይሬክተሩ፤ አንዳንድ ኤርትራውያን ስደተኞች ወደ ኤርትራ እንደሄዱ መስማታቸውን ገልጸው፤ “በትክክልም ወደ ኤርትራ ስለመሄዳቸውን እና ቁጥራቸው ምን ያክል እንደሆነ የምናጣራው ይሆናል” ብለዋል።
በክልሉ የተከሰተው ግጭት በርካቶች ቀያቸውን ጥለቀው እንዲሰደዱ አድርጓል።
ከ2 ሚሊዮን በላይም በዚያው በክልሉ ውስጥ ተፈናቅለው ይገኛሉ። ከ50 ሺህ በላይ ደግሞ ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን ሸሽተዋል።
የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢዎች ከትግራይ ክልል እየተሰደዱ ያሉ ዜጎችን ለመድረስ እንዲቻል ያለገደብ አመቺ ሁኔታ እንዲፈጠር በተደጋጋሚ ጠይቀዋል። በክልሉ ያለው ሁኔታም ወደ ሰብዓዊ ቀውስ ሊሸጋገር ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በትግራይ ክልል በተከሰተው ግጭት ምን ያህል ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ እስካሁን የሚታወቅ ነገር የለም።













