በትግራይ ለሕጻናት የሚደረገው ድጋፍ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ተባለ

ሕጻናት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ እርዳታ ተቋማት በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ አስቸጋሪ ሁኔታ በመኖሩ፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ረሃብና የምግብ እጥረት ሊያጋጥማቸው እንደሚችል መግለጻቸው ይታወሳል።

የኖርወጂያን ረፊዩጂ ካውንስል ዋና ጸሐፊ በሳለፍነው ሳምንት ባወጣው ሪፖርት፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሰብዓዊ እርዳታና ጥበቃ በማያገኙበት ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ ብሎ ነበር።

ይህን ተከትሎ ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች፤ ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ወደ ክልሉ የሚገቡበትና አስቸኳይ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች የሚደርሱበት መንገድ እንዲመቻችላቸው ሲጠይቁ ቆይተዋል።

ከትናንት በስቲያ የዓለም የምግብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቤስለይ በትዊተር ገጻቸው የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ ከኢትዮጵያ መንግሥት ከስምምነት መድረሳቸውን በመግለጽ "ሦስት ሚሊየን የሚጠጉ የእኛን እርዳታ የሚሹ ሰዎች አሉ፤ የምናጠፋው ጊዜ የለም" ብለዋል።

መንግሥት በበኩሉ፤ እስከ አሁን ለ1.8 ሚሊዮን ሰዎች የሰብዓዊ እርዳታ ቁሳቁሶች ማድረሱን በመግለጽ 2.5 ሚሊየን ህዝብ ለመርዳት የሚያስችለው ዝግጁነት እንዳለው ይገልጻል።

ይሁን እንጂ፤ ጦርነቱ ለዜጎች መፈናቀል፣ ለጾታዊ ጥቃትና ሌሎች ውድመቶችን ምክንያት እንደሆነ ሲገለጽ፤ በዚህ ውስጥ ሕጻናት ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ መሆናቸውን ይነገራል።

በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ ሚኪኤል ሰርቫዲ ለቢቢሲ በሰጡት ማብራሪያ፤ በክልሉ ባለው ሁኔታ ከፍተኛ የሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎት መኖሩን፣ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ዝግ መሆናቸውንና ከፍተኛ የስነ ልቦና ችግር እንዳለ ገልጸዋል።

"በክልሉ 1.3 ሚሊየን ሕጻናት ትምህርታቸውን አቋርጠዋል። በርካታ ትምህርት ቤቶች የወደሙ ሲሆን በመቀለ አስር ሺ የሚጠጉ ተፈናቃዮች የተጠለሉባቸው ትምህርት ቤቶች አሉ። በግጭቱ ምክንያት ያጋጠመውን ስነ ልቦናዊ ችግር ለማከምም እርዳታ ያስፈልጋል" ይላሉ።

በክልሉ ያለው የትምህርትና የሕጻናት ጉዳይ ድሮም አሳሳቢ እንደነበረ የሚናገሩት ሚኪኤል፤ ሁኔታው በምግብ እጥረት የተጠቁ ሕጻናት ቁጥር እንዲጨምር ምክንያት መሆኑን ይናገራሉ።

"ድሮም በትግራይ ከባድ የተመጣጠነ የምግብ እጥረት ችግር ነበር። ከግጭቱ በፊት በ2020 በርካታ እርዳታ ፈላጊዎች ነበሩ። ከኮሮናቫይረስ ስርጭት እና ከየአንበጣ መንጋ ወረራ ጋር በተያያዘ 34 በመቶ ከባድ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የነበረባቸው ሕጻናት ነበሩ፤ አሁን ባገኘነው ሪፖርት መሰረት ደግሞ ቁጥሩ ከ4 እስከ 4.5 በመቶ ሊሆን እንደሚችል ነው። ይህም ከግጭቱ በፊት ከነበረው የላቀ ነው" ብለዋል።

ከመቀለ ሆስፒታል መረጃ የሰጠን አንድ የጤና ባለሙያ፤ በምግብ እጥረት የተጠቁ ሕጻናት ወደ ህክምና እንደሚመጡና ለዚህ የሚሰጡ መድሃኒቶች የማግኘት ችግር መኖሩን ይናገራል።

"ምግብ መብላት አስቸግሯቸው ሆዳቸው አብጦ፣ ቆስለው የመጡ ህጻናት አሉ። በዚህ ምክንያት ተቅማጥና የሳምባ ምች እያጠቃቸው ነው። ይህ ከምግብ እጥረት የሚመነጭ ነው። ስንጠይቃቸው 'ቤተ-ክርስቲያ ተጠልለን ነው የቆየነው፣ በረሃ ላይ የሚበላና የሚጠጣ ውሃ ሳናገኝ ነው የቆየነው' ስለሚሉ ችግራቸው የምግብ እጥረት እንደሆነ ያሳያል" ይላል።

በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ ወደ ክልሉ ለሕጻናት አልሚ ምግብ መላኩን ቢገልጽም ይህ ግን ከፍላጎት አንጻር ሲታይ በቂ አይደለም ይላል።

እንደ ሚኪኤል ገለጻ በክልሉ ያለው ሁኔታ ወደ ሁሉም አካባቢዎች ለመድረስ የሚያስችል አለመሆኑ እና አብዛኛዎቹ በገጠር አካባቢዎች የነበሩ መዋቅሮች አሁን ባለመኖራቸው አልሚ ምግብ ወደ ክልሉ መላክ ካልተቻሉባቸው ምክንያቶች ተጠቃሽ ናቸው።

"ከ600 በላይ የጤና ባለሙያዎች ወደ መቀለ ተፈናቅለዋል። ከ40 ሆስፒታሎች 14ቱ ተዘርፈዋል፤ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ሆስፒታሎች 4 ብቻ እንደሆኑ መረጃው አለን" ብለዋል።

የስነ ልቦናዊ ቀውስ ስጋቶች

በትግራይ ክልል በተከሰተው ግጭት ከባድ ጦር መሳሪያዎች ጥቅም ላይ ውለዋል። ግጭቱ በሰዎች ላይ ስነ ልቦናዊ ቀውስ ሊፈጥርም ይችላል።

የመቀለ ከተማ ነዋሪ እና የሦስት ልጆች እናት የሆነችው ወ/ሮ ለተብርሃን ግደይ፤ በትንሽ ንግድ ልጆችዋን ታሳድግ እንደነበረ ትናገራለች።

ከግጭቱ በፊትም በድህነት እንደምትኖር ገልጻ፤ ዛሬ ላይ ግን ግጭቱን ተከትሎ በልጆቿ ላይ የደረሰው ስነ ልቦናዊ ጫና እንዳሳሰባት ትገልጻለች።

"በተለይ ትንሹ የአምስት አመት ሕጻን ስለ ጦርነት የሚያውቀው ነገር የለም። መቀለን ለመቆጣጠር በነበረው የአየርና የከባድ መሳሪያ ድብደባ ደንግጦ፤ አሁንም ድንጋጤው አልለቀቀውም። ጮክ ያለ ድምጽ ሲሰማ ያለቅስብኛል፤ ከእቅፌ መውጣት አይፈልግም" ትላለች።

በምስራቃዊ ዞን ተንቤን አካባቢ በከፍተኛ ጦር መሳሪያዎች ከባድ ጦርነት እንደነበረ የምትናገረው ትርሐስ፤ ለሳምንታት በእግሯ ተጉዛ መቀለ እንደደረሰች ትናገራለች።

"እስከ ዛሬ የሚሰማኝን ድንጋጤ መግለጹን ትቼ፤ ስለ ልጄ ልናገር። እዚህ የአየር ድምጽ ስትሰማ 'መጣችብኝ' እያለች ትደነግጥብኛለች። አይዞሽ . . . የእኛ ናት እያለኩ ማባበል ስራዬ ሆኗል" ትላለች።

ሞትና የአካል ጉዳት እንዲሁም መፈናቀል፤ ጦርነትን ወይም ግጭትን ተከትለው የሚመጡ ችግሮች ሲሆኑ፤ በኢትዮጵያ የሕጻናት አድን ድርጅት ተወካይ ሚኪኤል ሰርቫዲ በግጭቱ ምክንያት በርካታ ሕጻናት ስነ ልቦናዊ ጫና ደርሶባቸዋል ብለዋል።

"በትግራይ በርካቶች ተፈናቅለዋል። እኛ ማረጋገጥ ባንችልም ጾታዊ ጥቃቶች እየተፈጸሙ ነው የሚሉ ሪፖርቶች ያሳስቡናል። በዚህና በሌሎች ምክንያቶች ሕጻናት ለስነ ልቦናዊ ችግር ተጋላጭ ሆነዋል" ይላሉ።

"በምኖርባት መቀለ ከተማ እንኳን ብዙ የሚታይ ነገር ነው ያለው" የሚለው በመቀለ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ፕሮፌሰር ቢነጋ ሃይለስላሴ፤ ቀውሱ በአንድ ማህበረሰብ ሊያደርሰው የሚችለው ሁለንተናዊ ጉዳት ብዙ ነው ይላል።

"አሁን ባለንበት ሁኔታ የአየር ወይም የመኪና ድምጽ ሰምቶ የሚደሰት ሕጻን የለም፤ ሁሉም ደንግጠዋል" የሚለው ተባባሪ ፕሮፌሰር ቢነጋ፤ በተለያዩ አካባቢዎች የነበሩ የጦርነት መሳርያ ድምጾች በልጆች ስነ ልቦና ትተውት ያለፉት ጠባሳ አለ ይላል።

እንደዚህ አይነት ችግሮች የገጠሟቸው የባለሙያ ድጋፍ ማግኘት የማይችሉ ከሆነ ወደ አእምሮ ጤና ችግር ሊያድግ እንደሚችልና ችግሩ ተባብሶ የሚጥል በሽታን የመሰሉ ህመሞች የመስፋፋት እድል እንዳላቸው ስጋቱን ይገልጻል።

"ከአጸደ ሕጻናት ጀምሮ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ትምህርት ቤቶች ዝግ ናቸው፤ መደበኛ ትምህርት የለም። የአንድ ሕጻን አእምሮአዊ እድገት የሚወሰንበት እድሜ እስከ ሰባት አመት ነው። ስለዚህ አጸደ ሕጻናቶቹ ከተዘጉ፣ መደበኛ ትምህርት ከተቋረጠ፤ የሕጻናቱ አእምሮ መሰረታዊ ቅርጽ የሚይዝበት ጊዜ ያልፋል ማለት ነው" በማለት እነዚህ ህጻናት ወደ ትምህርታቸው ለመመለስ ሰላም መስፈን አለበት ሲል ያብራራል።

መሬት ላይ ብዙ ፍላጎቶች እንዳሉ የሚገልጹት ሚኪኤል በበኩላቸው፤ ለተለያዩ ጥቃቶች ተጋላጭ የሆኑ ሕጻናት በመኖራቸው ሁሉም የግጭቱ ተሳታፊ ወገኖች ሕጻናትና ንጹሀን ዜጎችን ከጥቃት እንዲከላከሉ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም መረጋጋት በሚታይባቸው አካባቢዎች ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ እና ተጠቂ የሆኑ ሕጻናት እርዳታ እንዲያገኙ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።

ለዚህም የተሻለ መንገድ እንዲከፈት ፍላጎታቸው እንደሆነ በመግለጽ ከመንግሥት ጋር እየሰራን ነው ብለዋል።