በትግራይ ክልል ተጨማሪ ከተሞች የስልክ አገልግሎት መጀመራቸው ተገለፀ

የኢትዮ ቴሌኮም አርማ

የፎቶው ባለመብት, Ethiotelecom

በትግራይ ክልል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ተቋርጦ የነበረው የስልክ አገልግሎት በ363 ጣቢያዎች መጀመሩን ኢትዮ-ቴሌኮም አስታውቋል።

ድርጅቱ በሰሜን ሪጅን የቴሌኮም መሰረተ ልማት ጥገና እና አገልግሎትን በተመለከተ በሰጠው መግለጫ እስካሁን ድረስ የጥገናና የኃይል አቅርቦት ስራዎች በመጀመር በ363 ጣቢያዎች የሞባይል ድምፅና የመደበኛ ስልክ አገልግሎት ተጀምሯል ብሏል።

በዚህም መሰረት አገልግሎት ማግኘታቸው ከተጠቆሙ ከተሞች መካከል መቀለ፣ አድዋ፣ አክሱም፣ አዲግራት፣ ሽረ እንዳስላሴ፣ ነጋሽ፣ ዲንሻ፣ ውቅሮ፣ አዳጋ ሃሙስን ጨምሮ በ26 ከተሞች የቴሌኮም አገልግሎት ማግኘት እንደጀመሩ ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ አመላክቷል።

ቀደም ሲል የፌደራል መንግሥቱ መቀለን ከተቆጣጠረ ጥቂት ሳምንታት በኋላ በደቡብና ምዕራብ ትግራይ የሚገኙት አንዳንድ ከተሞች ተቋርጦ የቆየውን አግልግሎቱን መጀመሩ ይታወቃል።

በተለይ ማእከላዊ የትግራይ ዞን ከማናቸውም የግንኙነት መስመሮች ተቋርጦ ስለ ነበር በርካታ ሰዎች ስጋታቸውን ሲገልፁ ነበር።

በአሁኑ ወቅት በማእከላዊ ዞን የሚገኙት እንደ ዓድዋ፣ አክሱም፣ ሽረ እንዳስላሰ፣ ቤተመራ፣ ውቕሮማራይ እና ሰለኽለኻ የመሳሰሉት ከተሞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መደረጋቸው ኢትዮ ቴሌኮም ገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ በክልሉ ውስጥ የተቋረጠውን የባንክ አገልግሎት ለማስጀመር በሽረ እንዳስላሴ፣ በአክሱም እና በአድዋ ከተሞችና አካባቢዎች የሚገኙ የሚገኙ ባንኮች የብሮድ ባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት ማግኘታቸውን አስታውቋል።

ድርጅቱ ባሰፈረው መረጃ መሰረት በመቀሌና በአዲግራት የሚገኙ ባንኮች እንዲሁ የብሮድ ባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት እያገኙ ናቸው።

ሆኖም በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች አገልግሎት እንዲያገኙ የተደረገው ጊዜያዊ የስርጭት መስመሮችን በመዘርጋት በመሆኑ የአገልግሎት መቆራረጥና ጥራት ጉድለት ሊያጋጥም እንደሚችል ተጠቁሟል።

በአጠቃላይ በሰሜን ሪጅን ያሉት የቴሌኮም መሰረተ ልማቶችን ሙሉ በሙሉ ለመጠገን እየተሰራ እንደሆነ ገልፆ በሙሉ አቅም አገልግሎቱ እስጂመር ነዋሪዎች እንዲታገሱ ኢትዮ-ቴሌኮም ጠይቋል።

ቢቢሲ በአንዳንድ ከተሞች ስልክ በመደወልና የደወሉ ሰዎችን የጠየቀ ሲሆን ከከተሞች ውጪ በገጠር አካባቢዎች የሞባይል ስልክ መስመሮች እንደማይሰሩ ተናግረዋል።

ቢቢሲ ወደ ሽረና ሰለኽለኻ ተቋርጦ የቆየው የሞባይል ስልክ መስራቱን በአካባቢዎቹ ከሚኖሩ ነዋሪዎች ጋር በመደወል ማረጋገት ችሏል።

በውጭ አገራት ነዋሪዎች የሆኑና በተለያዩ ከተሞች የሚገኙ የትግራይ ክልል ተወላጆች ከቤተሰቦቻው፣ ዘመድ አዝማዳቸውና ወዳጆቻቸው ጋር ከሶስት ወር በኋላ መነጋገራቸውን ለቢቢሲ አስረድተዋል።

በርካቶች የስልክ ግንኑነት መቋረጡን ተከትሎ የቤተሰቦቻቸውን ደህንነት ሁኔታ ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ አለማወቃቸው እንዳስጨነቃቸው በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች ሲገልፁ መቆየታቸው ይታወሳል።

ግጭቱን ተከትሎ በተለያዩ ምክንያት ህይወታቸውን ያለፈ ቤተሰባቸውን ሞት በዚህ አጋጣሚ የተረዱም እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል።

የስልክና የባንክ አገልግሎት ተቋርጦ መቆየቱ ቤተሰቦቻቸው መሰረታዊ የሚባሉ ሸቀጦችን ለመግዛት ተቸግረው እንደነበርና ለከፋ ችግርም እንዳይጋለጡ ስጋት እንደነበራቸው የገለፁት ነዋሪዎች በአሁኑ ወቅት የስልክ መስመሮች መከፈታቸው እንዳስደሰታቸው አክለው ተናግረዋል።

የባለፉት 100 ቀናት ለበርካታ የክልሉ ነዋሪዎች አስቸጋሪው የፈተና ጊዜ እንደነበር ያስረዳሉ።

አንድ የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚ ከ97 ቀናት በኋላ ወላጅ ኣባት እና እናቱን ማነጋገር ቢችልም "እርስ በርስ ከመላቀስ ውጪ መነጋገር አልቻልንም" በማለት አስፍሯል።

ሌላ ወደ ሽረ ከተማ ስልክ ደውሎ ቤተሰቡን ማናገር የቻለ በውጭ አገር የሚኖር የትግራይ ተወላጅ መኖርያ ቤታቸው ተደርምሶና ፈራርሶ እንደሆነ ለማወቅ መቻሉን ለቢቢሲ ተናግሯል።

"በሰፈራችን በርካታ ቤቶች ወድሟል። ሰውም ሞቷል። የእኛም ቤት በከባድ መሳርያ መመታቱና የቤት መሰተዋቱን መሰባበሩን ነግረውኛል። ቤተሰቦቼ በህይወት ተርፈው ማነጋገር መቻሌ ግን ትልቅ ነገር ነው" ብሏል።

አብዛኛዎቹ የቤተሰቡ ኣባላት ሽረ ላይ ጦርነት ከተጀመረበት ወቅት ጀምሮ ከከተማው ሸሽተው በገጠር ማሳለፈቻውን ይናገራል። በአሁኑ ወቅት መጠነኛ መረጋጋት እንዳለና ወደ ከተማ ተመልሰው ኑሯቸውን መጀመራቸውን እንደነገሩት ይኸው ግለሰብ ለቢቢሲ ያስረዳል።

ሆኖም ሌሎች ቤተሰቦቹን ጨምሮ በርካታ የሰፈሩ ነዋሪዎች ከከተማ ወደ ገጠር እየተመላለሱ እንዳሳለፉትና አሁንም ባለባቸው ስጋት ምክንያት ያልተመለሱ እንዳሉ መስማቱን ለቢቢሲ ገልጿል።

በትግራይ ክልል የሕወሓት ኃይሎች በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መክፈታቸው ከተገለፀ ከተገለፀ በኋላ መንግሥት "የሕግ የማስከበር" የሚለውን ወታደራዊ ዘመቻ መውሰዱን ተከትሎ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጦ መቆየቱ ይታወሳል።

በክልሉ በተከሰተው ወታደራዊ ግጭት ሳቢያ ተቋርጠው የነበሩት የመብራት፣ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎቶች በመሠረተ ልማቶቹ ላይ በደረሰው ውድመት እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን፤ ለዚህም የፌደራል መንግሥት ህወሓት ተጠያቂ እንደሆነ መግለፁ የሚታወስ ነው።