ትግራይ ፡ በተወሰኑ የትግራይ ክልል አካባቢዎች የቴሌኮም አገልግሎት መጀመሩ ተገለፀ

የፎቶው ባለመብት, Ethiotelecom
በፌደራሉ መንግሥት እና በትግራይ ክልል ኃይሎች መካከል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ በትግራይ ክልል ተቋርጦ የነበረው የቴሌኮም አገልግሎት በተወሰኑ አካባቢዎች አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ ለቢቢሲ ተናገሩ።
ለሳምንት አገልግሎቱ ተቋርጦባቸው ከነበሩት አካባቢዎች መካከል አንዱ በሆነው በአላማጣ ሙሉ በሙሉ የቴሌኮም አገልግሎት መጀመሩንና የተወሰኑ ቀናትም መቆጠሩንም ኃላፊዋ ገልፀዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በምዕራብ በኩል በዳንሻ፣ በተርካን፣ ሁመራ፣ ሽራሮ፣ ማይካድራና ማይፀብሪም አገልግሎቱ በከፊል ተጀምሯል ብለዋል።
በእነዚህ አካባቢዎች በከፊል አገልግሎት መስጠት የተጀመረበትንም ምክንያትም ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ሲያስረዱ በአካባቢው የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ባለመኖሩ መሆኑን አመልክተው፤ ለዚህም እንደመፍትሄ አማራጭ ኃይል ብለው የጠቀሷቸውን ጄኔሬተርና ሶላር የኃይል ማመንጫዎችን በመጠቀማቸው እንደሆነ ገልፀዋል።
በአጠቃላይ በክልሉ የተቋረጠውን የቴሌኮም አገልግሎት ለመመለስ ኢትዮ-ቴሌኮም የጥገና ሥራ እያካሄደ መሆኑን የገለፁት ፍሬሕይወት ለዚህም የኃይል አቅርቦት ችግሩን ለመቅረፍ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በጥምረት እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።
ከሦሰት ሳምንታት በላይ ወታደራዊ ግጭት በተካሄደባት ትግራይ ክልል የቴሌኮም አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ በመቆየቱ ግንኙነት ተቋርጦ መቆየቱ ይታወሳል።








