በትግራይ ከተሞች ላይ በዘፈቀደ የጦር ድብደባ መፈፀሙን ሂውማን ራይትስ ዋች ገለፀ

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል ከተሞች ላይ ልዩነት ባላደረገ መልኩ፣ በዘፈቀደ ድብደባ እንዳደረሰና ይህም የጦርነት ሕግን የሚጥስ እንደሆነ ሂውማን ራይትስ ዋች በዛሬው እለት ባወጣው ሪፖርቱ አስታወቀ።
ሪፖርቱ በተለይም ግጭቱ በተጀመረበት ወቅት በከባድ መሳሪያዎች ቤቶች፣ ሆስፒታሎችና፣ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም የገበያ ቦታዎች ጥቃት ደርሶባቸዋል ብሏል።
ሪፖርቱ እነዚህ ድብደባዎች የደረሱት በመቀለ፣ ሁመራ፣ ሽረ እንዳስላሴ ከተሞች እንደሆነ ጠቅሶ ህፃናትን ጨምሮ 83 ንፁሃን ዜጎች ተገድለዋል፤ እንዲሁም 300 ሰዎችም ቆስለዋል ይላል።
መንግሥት ለሂውማን ራይትስ ዎች ሪፖርት እስካሁን የሰጠው ምላሽ ባይኖርም፤ ከዚህ ቀደም "በሕግ የማስከበር እርምጃው" በሲቪሎች እና በቅርሶች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ጥንቃቄ መደረጉን አስታውቋል።
"ጦርነቱ በተጀመረበት ወቅት የኢትዮጵያ ፌደራል ኃይሎች በከባድ መሳሪያ ከተሞች ላይ ልዩነት ባላደረገ መልኩ፣ በዘፈቀደ ደብድበዋል። ይሄም ማለት የሲቪሎች መሞትና የንብረት መውደም ማስከተሉ የማይቀር ነው" ይላሉ የድርጅቱ የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ላይቲታ ባዴር።
አክለውም "እነዚህ ጥቃቶች የንፁኃን ዜጎችን ህይወት አደጋ ውስጥ ጥለዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ የክልሉ ነዋሪዎችን አፈናቅሏል። እነዚህ ህጋዊ ያልሆኑ ጥቃቶች እንዲቆሙና ኃላፊነት መውሰድ ያለባቸው አካላት ወደ ፍትህ ይቅርቡ" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ህዳር 21፣ 2013 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት የፌደራል መንግሥት ሰራዊት "በህግ ማስከበር ዘመቻው አንድም የንፁህ ዜጋ አላጠፋም" ማለታቸው ይታወሳል።
ግጭቱን አስመልክቶ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ እንዲሁ በትዊተር ገፁ ላይ ባሰፈረው ፅሁፍ የፌደራል ኃይሎች "በከተሞችና ህዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች ላይ ውጊያ አላካሄዱም" ብሏል።
ማጣሪያው አክሎም "መከላከያ ኃይሉ ንፁኃን ዜጎች እንዳይሞቱና ውድመትን ለመካከል ፈታኝ መልክዓ ምድሮችን ለማቆራረጥ ተገዷል። እስካሁንም ባለው የመከላከያ ሠራዊቱ ለንፁኃን ዜጎችን ከፍተኛ ጥበቃ በማድረግ የተሳካ ስራ ሰርቷል" በማለት አስፍሯል።
ጥቅምት 24፣ 2013 የትግራይ ኃይሎች በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የፌደራሉን ጦር ወደ ትግራይ ማዝመታቸው ይታወሳል።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ ያለውን ሁኔታ የገመገመው የሂውማን ራይትስ ዎች ሪፖርት፤ ግጭቱን ተከትሎ በርካታ የክልሉ ነዋሪዎች በቂ ምግብ የላቸውም፣ የውሃ፣ የነዳጅና የመድኃኒት ዕጥረት አጋጥሟቸዋል። ከ200 ሺህ በላይ ነዋሪዎች በዚያው በክልሉ ውስጥ ተፈናቅለው የሚገኙ ሲሆን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን ሸሽተዋል ብሏል።
ሂውማን ራይትስ ድርጅት 37 የአይን እማኞችን እንዲሁም በመንግሥት ኃይሎች ጥቃት ደርሶብናል ያሉ የሁመራ፣ ሽረ እንዳስላሴና መቀሌ ነዋሪዎችን፣ ዘጠኝ ጋዜጠኞችን፣ የረድዔት ድርጅት ሰራተኞችን፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችንና የፎረንዚክ ባለሙያዎችን አናግሮ ይሄንን ሪፖርት እንዳጠናቀረ አስታውቋል።
ድርጅቱ ከዚህም በተጨማሪ የሳተላይት ምስሎችን እንዲሁም ጥቃት ከተፈፀመባቸው ስድስት ቦታዎች የተገኙ ፎቶዎችንና ቪዲዮዎችን እንደመረመረ አስታውቆ፤ ከአይን እማኞቹ ምስክርነት ጋርም ተመሳሳይነት እንዳለው በሪፖርቱ አካቷል።
ድርጅቱ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱን ለኢትዮጵያ መንግሥት ቢያሳውቅም ምላሽ እንዳላገኘ እንዲሁ አስፍሯል።
በሌላ በኩል የአይን እማኞችን አባሪ አድርጎ ድርጅቱ እንዳሰፈረው የፌደራል ሰራዊቱ የሁመራ፣ ሽረና መቀለ ከተሞችን ለመቆጣጠር በከፍተኛ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት ማድረሱን ነው።
እነዚህ ጥቃቶች ወታደራዊ (የጦር ሰፈሮችን) ኢላማን ያደረጉ ሳይሆኑ በርካታ ነዋሪዎች የሚኖሩባቸው አካባቢዎች ላይ የተፈፀሙ መሆናቸውን አስረድተዋል። እንደነዚህ አይነት ተመሳሳይ ድብደባ በአክሱም እንደደረሰም ከ13 ነዋሪዎች ጋር ባደረገው ውይይት ተረድቻለሁ ብሏል።
በሁመራ ደረሰ የተባለው ድብደባ
በምዕራባዊ የሁመራ የድንበር ከተማ ጥቅምት 30፣ 2013 ዓ.ም ከኤርትራ ሠራዊት የተሰነዘረ ጥቃት በንፁሃን ዜጎች ላይ ጥቃት ያደረሰ ሲሆን፤ በርካቶችም እንደሸሹ ሪፖርቱ አስፍሯል።
በጥቃቱ ቀበሌ 2 የሚባለው አካባቢ የነዋሪዎች ቤት ላይ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን እንዲሁም ጥቃቱ በቤተ ክርስቲያንና መስጊድ አካባቢ የደረሰ ነው ብለዋል። በቀበሌ 01 የደረሰው ጥቃት በከተማዋ ዋነኛ ሆስፒታል አካባቢ ላይ ጥቃት ማድረሱን ድርጅቱ ነዋሪዎቹን ዋቢ በማድረግ ሪፖርቱ ያትታል።
በከተማዋ ዋነኛው ካህሳይ አበራ ተብሎ በሚጠራው ሆስፒታል የሚሰሩ የህክምና ባለሙያዎች ደግሞ በሟቾች አስከሬንና ከፍተኛ ጉዳት በደረሰባቸው ህሙማን ምክንያት ሆስፒታሉ ድንገተኛ መጨናነቅ አጋጠመው በማለት ለድርጅቱ መናገራቸው ተገልጿል።
አንደኛው ዶክተር በጥቅምት 30 ቀን የሞቱት ሰዎች ቁጥር ወደ 46 ይገመታል ያለ ሲሆን የቆሰሉ ደግሞ 200 ናቸው ማለቱን ድርጅቱ አስፍሯል።
በሽረ እንዳስላሴደረሰ የተባለው ጥቃት
በሰሜን ምስራቅ ሽረ እንዳስላሴ ከተማ ህዳር 8፣ 2013 ዓ.ም ጥቃት የተጀመረ መሆኑን ያመላከተው ሪፖርቱ በከተማዋ ማዕከል የሚገኙ ህንፃዎችን እንዲሁም የኢንዱስትሪ ስፍራዎችም ጥቃት ደርሶባቸዋል።
"በነዚህም ድብደባዎች ንፁሃን ዜጎች ተገድለዋል እንዲሁም ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በአቅራቢያቸው ወደሚገኘው አቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን ሸሽተዋል" ይላል። በዚያኑ ቀን የአይን እማኞች የኢትዮጵያ ሰራዊትና የኤርትራ ጦር በከተማው ሲያልፉ ማየታቸውን ተናግረዋል።
በተለያዩ ሪፖርቶች የኤርትራ ወታደሮች መሳተፋቸው የተጠቀሰ ሲሆን በቅርቡ የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ክልል በአስቸኳይ እንዲወጡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት (ስቴት ዲፓርትመንት) የአውሮፓ ህብረት መጠየቃቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ በተደጋጋሚ በትግራዩ ግጭት የኤርትራ ጦር አለመሳተፉን ማሳወቁ የሚታወስ ነው።
በመቀለ ደረሰ የተባለው ጥቃት
በመቀለ ከተማ ህዳር 19፣ 2013 ዓ.ም በደረሰው ከፍተኛ ድብደባ ልጆችን ጨምሮ 27 ንፁኃን ዜጎች ተገድለዋል እንዲሁም ከመቶ በላይ ቆስለዋል ይላል ሪፖርቱ።
በመቀለ አይደር ክፍለ ከተማ በገበያ አካባቢ በሚገኝ አንድ መኖሪያ ቤት በደረሰ የቦንብ ጥቃት አራት የቤተሰብ አባላትን ገድሏል ያለው ሪፖርቱ ከነዚህም ውስጥ ሁለቱ ህፃናት ልጆች ሲሆኑ አምስት ትልልቅ ሰዎችና አንድ የ9 አመት ልጅም ቆስሏል።
"የዘፈቀደ ወይም ደግሞ ያልለየ ጥቃት የምንለው በአንድ ወታደራዊ ኢላማ ያላደረገ ዝም ብሎ የደረሰ ጥቃት ነው። ከዚህም በተጨማሪ በከተሞችና ህዝብ በሚኖርባቸው ቦታዎች ላይ ወታደራዊ ኢላማ ላይ ያነጣጠሩ የቦንብ ድብደባዎች የዘፈቀደ ጥቃት ይባላሉ። እነዚህን የጦር ህጎች በቸልተኝነትም ሆነ ዝም ብለው የጣሱ ግለሰቦች ለጦር ወንጀሎች ተጠያቂ ይሆናሉ" በማለት ሪፖርቱ አፅንኦት ሰጥቷል።
ሁሉም ኃይሎች ቢሆኑ የንፁኃን ዜጎችን ህይወት አደጋ እንዳይጥሉ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው በማለት አስምሯል። በትግራይ ክልል ያለው ውጊያ አሁንም በቀጠለበት ሁኔታ ሁሉም ኃይሎች ለጦር ህግጋት እንዲታዘዙ አሳስቧል።
የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት በኅዳር ወር አጋማሽ ላይ መቀለን ከተቆጣጠረ በኋላ በትግራይ ያካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ መጠናቀቁን መግለጹ ይታወሳል።
"የኢትዮጵያ የፌደራል ሰራዊት ልዩነት ካላደረገ ጥቃት እንዲታቀቡ፣ ተፈፀሙ የተባሉ የጦርነት ህግ መጣስን እንዲመረምርና ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ባለባቸው ቦታዎች ላይ ተቀጣጣይ መሳሪያዎችን ከመጠቀም መቆጠብ አለበት" በማለት ጥሪውን አቅርቧል።
ከዚህም በተጨማሪ በአካባቢው የሰብዓዊ ረድዔቶች እርዳታ ያለ ምንም እክል እንዲገባ ሊመቻች ይገባል ብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ በክልሉ ደረሱ የተባሉ የጦርነት ህግ ጥሰቶችን የሚያጣራና መረጃዎችን የሚሰበስብ አንድ ቡድን የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ሊልክ ይገባል ብሏል።
"የኢትዮጵያ መንግሥት የተባባሩት መንግሥት መርማሪዎች በክልሉ ገብተው እንዲመረምሩ እንዲፈቅድና ሚሊዮኖችን ህይወት አደጋ ውስጥ የከተተው ጦርነት ችላ ሊባል አይገባም ብሏል።








