የማራዶና ሬሳን የማቃጠሉ ሥነ ሥርዓት እንዲዘገይ ፍርድ ቤት ወሰነ

የእግር ኳሱ ንጉሥ አርጀንቲናዊው ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የእግር ኳሱ ንጉሥ አርጀንቲናዊው ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና አባታችን ነው የሚሉ ልጆች የማራዶና ሬሳ በሰላም እንዳያርፍ እያደረጉት ነው።

ትናንት የአርጀንቲና አንድ ፍርድ ቤት የማራዶና ሬሳ ለዘረ መል (DNA)ምርመራ ስለሚፈለግ ‹ባለበት ይጠበቅ› የሚል ውሳኔን አሳልፏል፡፡

አሁን ሬሳው ለጊዜው ቦነስ አይረስ ውስጥ በሚገኝ በአንድ የግል መካነ መቃብር ላይ ያረፈ ሲሆን የዳኛው ውሳኔ ሬሳውን ወደ አመድነት የመቀየር ሥነ ሥርዓቱን ያዘገየዋል ተብሏል፡፡

ማራዶና ባለፈው ወር በተወለደ በ60 ዓመቱ ከልብ ጋር በተያያዘ በሽታ ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ይታወሳል፡፡

ዳኛው ሬሳው ‹ በመልካም ሁኔታ እንዲቆይ ይደረግ› የሚለውን ውሳኔ ሊያስተላልፉ የቻሉት አንዲት ሴት ማራዶና አባቴ ሳይሆን አይቀርም በሚል ለፍርድ ቤቱ ማመልከቷን ተከትሎ ነው፡፡

ማራዶና አባቷ እንደሆነ ለማረጋገጥ የግድ የዘረመል ናሙና ስለሚያስፈልግ ነው ሬሳውን የማስወገዱ ሥነ ሥርዓት እንዲዘገይ የሆነው፡፡

ማራዶና በጋብቻ ያፈራቸው ሁለት ሴት ልጆች ብቻ ነው ያሉት፡፡ ከነዚህ ሴት ልጆች እናት ጋር ከተፋታ በኋላ ግን በትንሹ 6 ልጆችን ‹ልጆቼ ናቸው› ብሎ ተቀብሏቸዋል፡፡

ሆኖም እርሱ ከጋብቻ ውጪ የወለዳቸው ልጆች ቁጥር ከዚህ በብዙ እጥፍ ሊኖሩ እንደሚችሉ የአኗኗር ዘይቤውን የሚያውቁ ይገምታሉ፡፡

የሱን ሞት ተከትሎ ልጆቹ ነን ያሉ በርካታዎች ሲሆኑ አሁን ለጊዜው ለፍርድ ቤት ያመለከተችው የ25 ዓመቷ ማጋሊ ጊል ናት፡፡

ማጋሊ ጊል ማራዶና በሕይወት እያለ ልጄ ናት ብሎ እውቅና ሰጥቷት አያውቅም፡፡

ማጋሊ በጉዲፈቻ ያደገች ሲሆን እናቷን ከ2 ዓመት በፊት ባገኘቻት ጊዜ አባቴ ማን ነው ብላ ስትጠይቃት፣ አርማንዶ ማራዶና ሊሆን ይችላል እንዳለቻት አስታውሳለች፡፡

ማጋሊ ጊል በኢንስታግራም በለቀቀችው ቪዲዮ ሰዎች ገንዘብ በመሻት ያደረገችው አድርገው እንደሚያስቡ ጠቅሳ ነገር ግን አባቷን የማወቅ ሂደት ዓለም አቀፍ መብት ነው ብላለች፡፡

ማራዶና በኖቬምበር 25 መሞቱን ተከትሎ ቦነስ አይረስ በአንድ መካነ መቃብር ውስጥ ነው የተቀበረው፡፡

ፍርድ ቤት የማራዶና ሬሳ ወደ አመድነት የመቀየሩ ተግባር እንዲዘገይ መጀመርያ የወሰነው በአሟሟቱ ላይ የሬሳ ምርመራ እንዲደረግ በማስፈለጉ ነበር፡፡

ማራዶና በሕክምና ስህተት ነው እንጂ አይሞትም ነበር ብለው የሚገምቱ ብዙዎች ናቸው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በግል ሐኪሙ ላይ ፖሊስ መርመራ መጀመሩ ይታወሳል፡፡

የትናንቱ የፍርድ ቤት ውሳኔ ግን የማራዶና ልጅ ነን የሚሉትን ለማስተናገድ በሚል የተራዘመ ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ ሮይተርስ የዜና ወኪል የማራዶናን ጠበቃ አናግሮ ባገኘው መረጃ መሰረት የማራዶና ዘረ መል ቅንጣት ማራዶና ከመሞቱ በፊት የተወሰደና የተቀመጠ ስለሆነ ሬሳውን የማቃጠሉ ሥነ ሥርዓት ማዘግየት አያስፈልግም ብሏል፡፡

ማራዶና የፋይናንስ አያያዙ የተዝረከረከ ስለነበረ በህጋዊ ልጆቹና ከጋብቻ ውጭ የተወለዱት ልጆቹ እንዲሁም የማራዶና ልጆች ነን እያሉ በመጡ ልጆች መሀል ዘለግ ያለ የፍርድ ሒደት ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡