እግር ኳስ ፡ ከማራዶና ሞት ጋር በተያያዘ ፖሊስ ሐኪሙ ላይ ምርመራ ጀመረ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የአርጀንቲና ፖሊስ በዲያጎ አርማንዶ ማራዶና ሞት ጋር ተያይዞ የዝነኛውን እግር ኳስ ተጫዋች ሐኪም እየመረመረ ይገኛል።
ፖሊስ በዋና ከተማዋ ቦነስ አይረስ የሚገኘውን የዶ/ር ሊዮፖልዶ ሉኮን መኖርያ ቤትና የግል ክሊኒክ በርብሯል።
ምርመራው ሊጀመር የቻለው ማራዶና የተሳካ የተባለ ቀዶ ህክምና ማድረጉን ተከትሎ በድንገት መሞቱ ምናልባት የሕክምና ቸልተኝነት ተጫዋቹን ለሞት ዳርጎታል የሚል ጥርጣሬ በመፈጠሩ ነው።
የ60 ዓመቱ የእግርኳስ ኮከብ የሞተው ከ4 ቀናት በፊት በልብ ድካም ነው። ማራዶና ከሕመሙ እያገገመ ሳለ ነበር በድንገት የሞተው።
ዶ/ር ሊዮፖልዶ እስካሁን ክስ አልተመሰረተበትም። ሆኖም አንድም ጥፋት የለብኝ ሲል እንባ እየተናነቀው ለጋዜጠኞች ተናግሯል።
ማራዶና ከመሞቱ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ የተሳካ የተባለ የጭንቅላት ቀዶ ህክምና አድርጎ ነበር። ቀዶ ጥገናው ያስፈለገው በጭንቅላቱ ውስጥ የደም መርጋት ምልክቶች በመታየታቸው ነበር።
በሚቀጥለው ወር ደግሞ ከአልኮል ሱስ ለመውጣት አዲስ ሕክምና ይጀምራል ተብሎ ቀጠሮ ተይዞለት ነበር።
የማራዶና ሴት ልጆች ስለ አባታቸው የሕክምና ሁኔታ ምርመራ እንዲደረግ ግፊት አድርገዋል ተብሏል።
ትናንት እሑድ ወደ 30 የሚሆኑ ፖሊሶች የማራዶና የግል ሐኪም ወደ ሆነው የ39 ዓመቱ ዶ/ር ሊዮፖልዶ ቤት በድንገት በመድረስ ብርበራ አድርገዋል። ሌሎች 20 የሚሆኑ ፖሊሶች ደግሞ ክሊኒኩን ፈትሸዋል።
ፖሊስ የማራዶና የመጨረሻ ቀናት ሕክምና ምን ይመስል እንደነበር ለመፈተሽ ነው ፍላጎቱ።
ኮምፒውተሮችን፣ ስልኮቹንና የሕክምና ማስታወሻዎችን ጭምር አንድ በአንድ እየመረመሩ ነው ተብሏል።
ፖሊስ ጥርጣሬ አለኝ የሚለው የማራዶና ቀዶ ጥገናን ተከትሎ ምናልባት ሐኪሙ ሊያደርጋቸው ይገቡ የነበሩ ጥንቃቄዎችን ሳያደርግ ቀርቶ ከሆነ በሚል ነው።
ማራዶና ቀዶ ጥገናውን አሳክቶ ወደ ቤቱ ከሄደ በኋላ እንዲያገግም የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች ነበሩ ወይ? የሚለው በምርመራው ይካተታል።
ለምሳሌ 24 ሰዓት በተጠንቀቅ የሚንከባከቡት ነርሶች መኖር፣ በአደገኛ እጽ ሱስ ለሚሰቃይ ሰው ክትትል የሚያደርጉ ባለሙያዎች መኖር፣ በአስቸኳይ ሊጠሩ የሚችሉ ሐኪሞች እና በተጠንቀቅ የሚቆም አምቡላንስ ነበረ ወይ? የሚለው ይፈተሻል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
መርማሪ ፖሊስ ዶ/ር ሊዮፖልዶ እነዚህ ሁኔታዎች ለታማሚው አሟልቶ ነበር ወይ፣ የሐኪሙ የመጨረሻ ቀናትን ምን ይመስላሉ የሚለውን እየመረመረ ነው።
የ39 ዓመቱ የማራዶና የግል ሐኪም ዶ/ር ሊዮፖልዶ ደንበኛው ከሞተ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ትናንት ዝምታውን ሰብሯል።
ዶ/ር ሊዮፖልዶ ስሜታዊ ሆኖ በእንባ እየታጠበ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ የማራዶናን ሕይወት ለማትረፍ የሚችለውን ሁሉ እንዳደረገለት ተናግሯል።
ማራዶና በመጨረሻ ቀናት ከፍተኛ ሐዘን ይሰማው እንደነበረም ጠቅሷል።
ዶ/ር ሊዮፖልዶ በጋዜጠኞች በእንዝህላልነት ለደንበኛው መሞት ተጠያቂ ይሆን እንደሆነ ሲጠየቅ በቁጣ እንዲህ መልሷል፣ "እኔ ተጠያቂ የምሆነው በምን ምክንያት እንደሆነ ልናገር? ማራዶናን በጣም በመውደዴ፣ ለእሱ በጣም እንክብካቤ በማድረጌ፣ በአጭር ይቀጭ የነበረውን ሕይወቱን በማራዘሜ፣ እስከመጨረሻው ከእሱ ጋር በመሆኔ ነው መጠየቅ ካለብኝ" ሲል በድንገተኛ ቁጣ ገንፍሎ ምላሽ ሰጥቷል።
ፖሊስ በበኩሉ ዶ/ር ሊዮፖልዶ ለማራዶና ቀዶ ጥገና ካደረገለት በኋላ ክትትል ማድረግ ሲገባው አላደረገለትም ብሎ ጠርጥሮታል። በዚህ ረገድ ዶ/ር ሊዮፖልዶ ሲመልስ "የእኔ ሙያ የአንጎል ቀዶ ህክምና ነው። እኔ ህክምናውን ጨርሻለሁ" በማለት ማራዶና ከእሱ ክሊኒክ ከወጣ በኋላ ላለው ነገር ተጠያቂ እንዳልሆነ አስገንዝቧል።
ዶ/ር ሊዮፖልዶ እንደሚለው ማራዶና ከቀዶ ህክምናው በኋላ መሄድ የነበረበት ወደ አደገኛ እጽ ማገገሚያ ማዕከል እንጂ ወደ ቤት አልነበረም።
ማራዶና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሳለ ቤቱ የተዘጋጀና የሕክምና ቁሶች የተሟሉለት አምቡላንስ እንዴት ላይኖር ቻለ የሚለው እያነጋገረ ነው።
ማራዶና በመጨረሻው ሰዓት ልጆቹንም፣ ቤተሰቡንም ማስጠጋት አልፈለገም፣ ከፍ ያለ ሐዘን ይሰማው ስለነበር ብቻውን መሆን ፈልጓል ሲል ሐኪሙ አብራርቷል።
ማራዶና የድኅረ ዝና መስቅልቅልና የኮኬይን ሱሰኝነት ለሕይወቱ ማጠር ሚና እንደነበራቸው ይታመናል።















