የዲያጎ ማራዶናን ሞት ተከትሎ በአርጀንቲና የሶስት ቀን ሐዘን ታወጀ

ዲያጎ ማራዶናን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዲያጎ ማራዶናን

የዲያጎ ማራዶናን ሞት ተከትሎ በአርጀንቲና የሶስት ቀን ሐዘን ታወጀ።

በአገሩ የእግር ኳስ ንጉስ እየተባለ የሚንቆለጳጰሰው ማራዶና በ60 ዓመቱ ትናንት ረቡዕ ምሽት ሕይወቱ ማለፏን ተከትሎ በአርጀንቲና የሶስት ቀናት ሐዘን ተጀምሯል።

የማራዶና አስክሬንም በመጪዎቹ ሶስት ቀናት የአርጀንቲና መንግሥት መቀመጫ በሆነቸው ካሳ ሮዛዳ እንደሚቆይ ተገልጿል።

የማራዶና ሞትን ተከትሎ በርካቶች ሐዘናቸውንም እየገለጹ ይገኛሉ ነው።

''ማራዶና እግጅ አስገራሚ ፍጥረት ነው፤ ነገር ግን እሱን መሆን በጣም ከባድ ነበር። ገና በለጋ እድሜው በታዋቂነቱ ምክንያት የመገናኛ ብዙሃን ትኩረትን ማግኘት ችሏል። እንደ ሌሎቻችን አይነት ሕይወት አላሳለፈም።'' ብሏል የማራዶና ቡድን አባል የነበረው ኦሲ አርዲለስ ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ።

የቀድሞው የአርጀንቲና ኮከብ ተጫዋች እና በኋላም የአገሩ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበረው ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና ያረፈው ቤቱ ውስጥ ሳለ በልብ ሕመም እንደሆነ ተገልጿል።

ማራዶና በዚህ ወር መጀመሪያ አካባቢ በአንጎሉ ውስጥ ላጋጠመው የደም መርጋት የተሳካ ቀዶ ሕክምና ተደርጎለት የነበረ ሲሆን በተከታይነትም ከአልኮል ሱስ ለመላቀቅ ሕክምና ይደረግለታል ተብሎ ነበር።

ትናንት ምሽት በተደረጉ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታዎች መጀመሪያ ላይ ለማራዶና የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት የተደረገ ሲሆን በዚህ ሳምንት በሚደረጉ ሁሉም የአውሮፓ ውድድሮች ላይ በተመሳሳይ ማራዶና ይታሰባል።

ሜሲ እና ሮናልዶን ጨምሮ ብራዚላዊው የእግር ኳስ ጥበበኛ ፔሌ እንዲሁም በርካታ የእግር ኳስ ፈርጦች በማራዶና ሕልፈት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።

''አንድ ቀን በሰማይ ቤት ከማራዶና ጋር እግር ኳስ እንደምንጫወት ተስፋ አደርጋለሁ'' ብሏል ፔሌ።

የማንቸስተር ሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ በበኩሉ ''የዓለምን እግር ኳስ ያሻሻል ሰው ነበር'' ብሏል።

የቀድሞ የቶተንሀም አሰልጣኝና የአርጀንቲናዊው ማውሪሲዮ ፖቼቲኖ ''በሀዘን ልቤ ተሰብሯል። ማራዶና የእኔ ጀግና እና ጓደኛዬ ነበርክ። ከአንተ ጋር እግር ኳስና ሕይወትን በማየቴ በጣም ዕድለኛ ነኝ'' ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል።

የማራዶና ሕይወት

የዓለማችን የምንጊዜም ታላላቅ ተጫዋቾች ከሚባሉት አንዱ የሆነው ማራዶና አርጀንቲና እአአ በ1986 የዓለም ዋንጫ ባለቤት ስትሆን የቡድኑ አምበል የነበረ ሲሆን ድንቅ ችሎታውንና የታወቀባቸውን የኳስ ጥበቡን በማሳየት ዓለምን አስደምሞ ነበር።

በተለይ አርጀንቲና ከእንግሊዝ ጋር ባደረገችው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ላይ እሱ "የእግዜር እጅ" ያላትና ዳኞች ሳያዩ በእጁ ያስቆጠራት ግብ ዘወትር ትታወሳለች።

በተጨማሪም ለስፔኑ ባርሴሎናና ለጣሊያኑ ናፖሊ ቡድኖች በአውሮፓ ውስጥ የተጫወተ ሲሆን፤ በጣሊያን ሴሪ አ ውስጥም ሁለት ጊዜ ዋንጫ ማንሳት ችሏል።

የአርጀንቲና እግር ኳስ ማኅበር የማራዶና ሞት በተሰማ ጊዜ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባወጣው መግለጫ "በጀግናችን ሞት በጣሙን አዝነናል" በማለት "ሁልጊዜም በልባችን ውስጥ ትኖራለህ" ብሏል።

ማራዶና ለአገሩ አርጀንቲና በአራት የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ላይ በተደረጉ 91 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ 34 ግቦችን አስቆጥሯል።

ማራዶና የተከለከሉ አበረታች መድኃኒቶችንና ዕጽ በመጠቀም ስሙ በተደጋጋሚ ሲነሳ የቆየ ሲሆን ከስፖርትም እገዳ ተጥሎበት ነበር።

ማራዶና ፕሮፌሽናል እግር ኳስን ከዛሬ 23 ዓመት በፊት በ37 ዓመት ዕድሜው ያቆመ ሲሆን፤ በአርጀንቲና ውስጥ ያሉ ቡድኖችን በአሰልጣኝነት ከመራ በኋላ የአገሩን ብሔራዊ ቡድንንም በማሰልጠን ለዓለም ዋንጫ አብቅቷል።

ከዚያም በኋላ በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ እና በሜክሲኮ ውስጥ የሚገኙ ቡድኖችን በተለያዩ ጊዜያት አሰልጥኖ ህይወቱ እስካለፈበት ጊዜ ድረስ ደግሞ የአገሩን አንድ ቡድን በማሰልጠን ላይ ነበር።