ናይጄሪያ፡ በቦኮሀራም ታግተው የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ተለቀቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሰሜን ምዕራብ ናይጄሪያ ካትሲና ግዛት ባሳለፍነው ሳምንት ከወንዶች አዳሪ ትምህርት ቤት ታፍነው የተወሰዱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ህጻናት መለቀቃቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት ለቢቢሲ ገልጹ።
የግዛቲቱ አስተዳዳሪ ቃል አቀባዩ ለቢቢሲ እንደገለጹት 344 ወንድ ህጻናት ተማሪዎች ተለቀው እንደሚገኙና በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳሉ ገልጸዋል።
ነገር ግን ከሌሎች ምንጮች እየወጡ ባሉ መረጃዎች መሰረት እስካሁንም ድረስ ጥቂት ተማሪዎች በታጣቂዎቹ ቁጥጥር ስር ይገኛሉ።
ለጠፉትና ለታገቱት በመቶዎች የሚቆጠሩ ወንድ ተማሪዎች ኃላፊነቱን ፅንፈኛው ቦኮ ሃራም የወሰደ ሲሆን ከሰአታት በፊት አንዳንድ ህጻናትን የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ለቅቆ ነበር።
የግዛቲቱ አስተዳዳሪ ቃል አቀባይ አብዱል ላብራን እንዳሉት ተማሪዎቹ ወደ ግዛቲቱ ዋና ከተማ ካትሲና ሲቲ እንደተወሰዱ ገልጸዋል።
አክለውም ተማሪዎቹ የሚታዩበት ቦኮ ሀራም የለቀቀው ተንቀሳቃሽ ምስል ትክክለኛ መሆኑን ገልጸው በቡድኑ መሪ ተላልፏል የተባለው መልዕክት ግን መሪውን መስሎ በቀረበ ሰው የተሰራ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ማክሰኞ ዕለት ባለስልጣናት ታግተዋል ስለተባሉት ህጻናት ቁጥር አነስተኛ ግምታዊ ቁጥር አስቀምጠው የነበረ ሲሆን እስካሁንም ድረስ ግን በትክክል የታገቱት ወንድ ተማሪዎች ምን ያክል እንደሆኑ አይታወቅም ተብሏል።
የግዛቲቱ አስተዳዳሪ አሚኑ ቤሎ ማሳሪ ከሮይተርስ የዜና ወኪል ጋር በነበራቸው ቆይታ ''አብዛኛዎቹን ተማሪዎች አስመልሰናል። ግን ሁሉንም አይደለም'' ማለታቸው ተገልጿል። ኤኤፍፒ ያነጋገራቸው አንዳንድ ሰዎች ደግሞ አሁንም ድረስ ጥቂት ህጻናት በአጋቾቹ ቁጥጥር ስር ይገኛሉ።
የአስተዳዳሪው ቃል አቀባይ አብዱል ላብራን በበኩላቸው ከታገቱት ተማሪዎች መካከል አንዳቸውም ህይወታቸው አላላፈም ብለዋል። ነገር ግን በአንድ ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ አንድ ህጻን የናይጄሪያ ተዋጊ ጄቶች በተኮሱት ጥይት አንዳንድ ተማሪዎች ተገድለዋል ሲል ይታያል።
ምንም እንኳን ተማሪዎቹ እንዴት ባለ ሁኔታ ሊለቀቁ እንደቻሉ የተገለጸ ነገር ባይኖርም ተማሪዎቹ በእርግጥም ስለመለቀቃቸው ግን ከግዛቲቱም ሆነ ከሌላ የመንግስት ኃላፊ ቢቢሲ መረጃ አግኝቷል።
ጥቃቱ እንዴት ተፈጸመ
ታጣቂዎች በሞተርሳይክል ተጭነው በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ ከደረሱ በኋላ ወደ ሰማይ መተኮስ እንደጀመሩና በርካቶችም በፍራቻ ተበታትነው ከአካባቢው እንደጠፉ አንድ የአይን እማኝ ተናግሯል።
ካትሲና ግዛት የሚገኘው የመንግሥት አዳሪ ትምህርት ቤት 800 ተማሪዎች ያሉበት ሲሆን ከበባውም የደረሰው ባሳለፍነው ሳምንት አርብ አመሻሹ ላይ ነው። እሁድ ዕለት ደግሞ የናይጄሪያ ጦር ታጣቂዎቹ የተደበቁበትን ስፍራ እንዳገኘውና ከሰራዊቱ አባላትም ጋር የተኩስ ልውውጥ እንደነበርም ተገልጿል።
በዚህ የወንዶች አዳሪ ትምህርት ቤት አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች ተኩስ ከምሽቱ አምስት ሰዓት አካባቢ እንደሰሙና ለአንድ ሰዓትም የዘለቀ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በትምህርት ቤቱ ውስጥ የሚገኙ የፀጥታ ኃይሎች ፖሊስ በቦታው ከመድረሱ በፊት ታጣቂዎቹን መግታት እንደቻሉ ባለስልጣናት አስረድተዋል።
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ የትውልድ ቦታ በሆነችው ካትሲና የደረሰው ጥቃት መንግሥት በደህንነት ቁጥጥር ላይ ያለውን ቸልተኝነት ያሳየ ነው በሚል ከፍተኛ ትችት እየደረሰበት ነው።
በሃምሌ ወር ቡድኑ ባወጣው ቪዲዮ ግዛቱን እያስፋፋ መሆኑንና በአገሪቷ ሰሜን ምዕራብ ክፍልም መግባቱን አስታውቋል። በአካባቢው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መንግሥት "ሽፍቶች" አደረሱት ባሉት ጥቃቶች ተገድለዋል።
እነዚህ "ሽፍቶች የተባሉት የወንጀለኞች ቡድን ከቦኮ ሃራም ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳላቸው ግልፅ አይደለም።
ሆኖም ከአልቃይዳ ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው የሚባለው አንሳሩ የተባለ ሌላ ቡድን በግዛቲቱ በከፍተኛ ሁኔታ ይንቀሳቀሳል።
ቦኮ ሃራም ከ2009 ጀምሮ አስከፊ የሆነ የሽምቅ ውጊያ እያካሄደ ሲሆን በተለይም በሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ በኩል አትኩሮቱን አድርጓል ።
በዚህም ግጭት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል እንዲሁም ከሁለት ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ቤት ንብረታቸውን ትተው ተፈናቅለዋል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደሚለው በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ብቻ ከ1 ሺ 100 በላይ ሰዎች በሰሜናዊ ናይጄሪያ በሽፍታዎች የተገደሉ ሲሆን መንግሥት እስካሁን ተጠያቂዎችን ለሕግ ማቅረብ አልቻለም።












