ኬንያ፡ የናይሮቢው ገዢ በቀረበባቸው የሙስና ክስ ከስልጣናቸው ተነሱ

ማይክ ሶንኮ በወጣቶች ዘንድ ዝነኛ ናቸው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኬንያ ዋና መዲና ናይሮቢ ገዢ የሆኑት ማይክ ሶንኮ ምቡቪ በክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ የቀረበባቸው የሙስና ወንጀል ክስ ተቀባይነት በማግኘቱ ከሥልጣን እንዲሱ ተደረገ።

የምክር ቤቱ አባላት የናይሮቢ ከተማ ገዢን ከቀረበባቸው አራት ክሶች በተጨማሪ፣ ሕገመንግሥቱን በመጣስ፣ ሥልጣንን ያለ አግባብ በመጠቀም፣ ያልተገባ ጠባይ በማሳየት እንዲሁም ሌሎች የአገሪቱን ሕጎች በመጣስ ጥፋተኛ ሆነው መገኘታቸውን ገልፀዋል።

ማይክ ሶንኮ ላይ ከቀረቡባቸው ክሶች መካከል አንዱ የሕዝብ ገንዘብን ተጠቅመው በ2018 ልጃቸው ወደ ኒውዮርክ እንድትጓዝ አድርገዋል የሚል ሲሆን፣ እንዲሁም በናይሮቢ ለተለያዩ ጉዳት ለተጋለጡ ሕጻናት የተመደበውን ፈንድ ለግል ጥቅም አውለዋልም ተብለዋል።

የናይሮቢ ከተማ ገዢ የነበሩት ማይክ ሶንኮ እጅጉን ተሽቀርቅረው መታየት የሚወዱ፣ የወርቅ ጌጣጌጦችን የሚያዘወትሩ መሪ የነበሩ ሲሆን የቀረበባቸውን ክስም አስተባብለዋል። እንደ እርሳቸው ከሆነ በናይሮቢ ከተማ በሙስና በተዘፈቁ ቡድኖች የሕዝብ ገንዘብ እንዳይዘረፍ የሚያደርጉትን ትግል ለማስቆም የተሰራ ሴራ ነው።

የናይሮቢ ከተማ ገዢ የነበሩት ሶንኮ ባለፈው ዓመት ሕዳር ወር ላይ ነበር በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት። ማይክ ሶንኮ ከተለያየ እሰጥ አገባዎች ጀርባ በተደጋጋሚ ስማቸው ይነሳል። በቅርቡ የኬንያ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ባለስልጣናት ሶንኮ ከ20 ዓመት በፊት ከጥብቅ እስር ቤት ውስጥ በማምለጥ ወንጀል ስማቸውን አንስተው ከስሰዋቸዋል።

ማይክ ሶንኮን በቴሌቪዥን ቃለመጠይቅ እየተደረገላቸው ባለበት ሰዓት ከማረሚያ ቤት ማምለጣቸውን እውነት መሆኑን ተናግረዋል። የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኬንያ ከተከሰተ ወዲህም ለናይሮቢ ነዋሪዎች በሚከፋፈል የእርዳታ እህል ውስጥ ሄኔሲ ቢራ እንዲካተት ያደረጉ ሲሆን ለዚህም ምላሽ ሲሰጡ “በቢራው ውስጥ ያለው የአልኮል መጠን ኮሮናቫይረስን ያስቆመዋል” ብለው ነበር።

ሶንኮ የናይሮቢ ገዢ ሆነው የተመረጡት በ2017 በፕሬዝዳንት ኡሁሩ ጁቢሊ ፓርቲ ስር ነበር። ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት ሁለቱ ግለሰቦች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት የተነሳ ሶንኮ ወደ ሌላ ፓርቲ እንዲሄዱ ሆኗል።

ፕሬዝዳንት ኬንያታ ከተማዋን የሚያስተዳድር ከዚህ በፊት በውትድርና ሙያ ላይ ያገለገለ ግለሰብ በመመደብ ማይክ ሶንኮ ለይስሙላ በቦታው እንዲቀመጡ አድርገው ቆይተዋል። ማይክ ሶንኮ ከአዲሱ ተሿሚ ጋር የስልጣን ርክክብ ካደረጉ በኋላ፣ በሰጡት ቃለምልልስ ላይ ሰነዶቹ ላይ ስፈርም ጠጥቼ ነበር ብለዋል።

ማይክ ሶንኮ የፖለቲካ ስልጣናቸውን የጀመሩት ኢስትላንድ በሚባል አካባቢ ሲሆን ከፍተኛ ድጋፍ ያገኙት ደግሞ ዝቅተኛ ኑሮ ከሚመራው ሕብረተሰብ ክፍል እና ከወጣቱ ነበር።

ሶንኮ የራሳቸው የሆነ የንግድ ተቋም ያላቸው ሲሆን “ሶንኮ ሬስኪው ቲም” በመባል ይታወቃል። ይህ ድርጅት አምቡላንሶች፣ የእሳት አደጋ መኪኖች፣ ለሰርግ የሚከራዩ ሊሞዚኖችንና የቀብር ማስፈፀሚያ መኪናዎች ያከራያል።

ተቺዎቻቸው ግን የሕዝብ ገንዘብ በመመዝበር እና ያልተገባ ጥቅም በማካበት ይኮንኗቸዋል። የናይሮቢ ከተማ ነዋሪዎች በስድሳ ቀናት ውስጥ ወደ ምርጫ መሄድ እና የከተማቸውን ገዢ መምረጥ ይጠበቅባቸዋል።

ሶንኮ በኬንያ በስልጣን ላይ እያለ በቀረበበት ውንጀላ ከኃላፊነቱ የተነሳ ሁለተኛው ሰው ናቸው። ከዚህ ቀደም በታሕሳስ ወር የኪያምቡ ካውንቲ ገዢ ፈርዲናንድ ዋይቲቱ በተለያዩ የሙስና ወንጀሎች ክስ ቀርቦባቸው ከሥልጣናቸው እንዲነሱ የተደረገ ሲሆን እርሳቸው ግን እኔ ንፁህ ነኝ ሲሉ ተከራክረዋል።