ኮሮናቫይረስ፡ በኬንያ የመጀመሪያው ዙር ክትባት በጥር ወር ይደርሳል ተባለ

የኮሮናቫይረስ ክትባት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኬንያ የመጀመሪያው ዙር የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት በሚቀጥለው፣ ጥር ወር እንደሚደርሳት አስታውቃለች።

የጤና ሚኒስትሩ ሙታይ ካግዌም ይህንኑ ማሳወቃውን የኔሽን አፍሪካ ጋዜጣ ዘግቧል።

ሚኒስትሩ የኦክስፎርዱ አስትራዜኔካ የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት ለህዝቡ እናቀርባለን ብለዋል።

አስትራዜኑካ የሚባለው ክትባት ከሞደርናና ፋይዘር ከተሰኙት የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባቶች ጋር ሲነፃፀር ዋጋው ረከስ እንደሚልም ተናግረዋል።

ነገር ግን የኦክስፎርዱ ክትባት በየትኛውም አገር እስካሁን እውቅና አላገኘም።

ኬንያ በግሎባል ቫክሲን አሊያንስ ኢንሺዬትቭ በተባለው ድርጅት አማካኝነት 24 ሚሊዮን መጠን ብልቃጥ ክትባቶችን ያዘዘችው ባለፈው ሳምንት ነው።

ይህም መጠን ከአገሪቷ ህዝብ መካከል 20 በመቶውን ይሸፍናል ተብሏል።

የኬንያ መንግሥት 10 ቢሊዮን የኬንያ ሽልንግ (89 ሚሊየን ዶላር) ገንዘብ ለክትባቱ እንዳወጣም ተገልጿል።

ክትባቱ ሲደርስ ቅድሚያ የሚሰጣቸው የጤና ባለሙያ ሰራተኞች፣ ፖሊሶች፣ አረጋውያንና መምህራን ይሆናሉ።

ከዚህም በተጨማሪ ህዝብ በተጨናነቀበት አካባቢ የሚኖሩና እንዲሁም ከአንድ ወይም ሁለት በላይ ተደራራቢ ህመም ያለባቸውም እንዲሁ የመጀመሪያው ዙር ክትባት ተጠቃሚም ይሆናሉ ተብሏል።

ኢትዮጵያም ኮቫክስ ከተሰኘው ዓለም አቀፍ የክትባት ድጋፍ ሰጪና እቅራቢ በኩል ለአገልግሎት ከሚቀርቡት የኮሮናቫይረስ ክትባት ለማግኘት ጥያቄ እንዳቀረበች የጤና ጥበቃ ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ባለፈው ሳምንት ገልጸዋል።

ሚኒስትሯ ጨምረውም ለአገልግሎት ብቁ ከሆኑ የክትባት ዓይነቶች መካከል ኢትዮጵያም እንድታገኝ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረው፤ በኮቫክስ በኩል ክትባቱን በፍጥነት ለማግኘትና በቅድሚያ መከተብ ለሚገባቸው ወገኖች እንዲደርስ እንደሚደረግ አስረድተዋል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ አንድ ዓመት ሊሞላው ተቃርቧል።

በአፍሪካ ከ2.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በበሽታው ሲያዙ ከ56 ሺህ በላይ ደግሞ ለሞት ተዳርገዋል።

ከዚህ ውስጥ ደግሞ በኢትዮጵያ ከ117 ሺህ በላይ ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን ከ1 ሺህ 800 በላይም ህይወታቸውን አጥተዋል።

ከ72 ሚሊዮን በላይ የምድራችን ነዋሪዎችም በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከ1.6 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በወረርሽኙ ሰበብ ሕይወታቸውን ማጣታቸው የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ያሳያል።