ኮሮናቫይረስ፡ የአፍሪካ አገራት የኮቪድ-19 ክትባትን የሚያገኙት መቼ ነው?

ክትባት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኮቪድ-19 ክትባቶች በዓለም ላይ ተስፋን አጭረዋል። ነገር ግን አሁንም የአፍሪካ አገራት ይህንን ክትባት እንዴትና መቼ እንደሚያገኙት ጥርት ያለ መልስ አልተገኘም።

የዓለም ጤና ድርጅት የሰራው አንድ ጥናት እንደሚያሳየው የኮቪድ-19 ክትባት ዝግጁ ከሆነ፣ 40 የአፍሪካ አገራት ክትባቱን ለመስጠት ዝግጁ ናቸው።

ነገር ግን እነዚህ አገራት በሙሉ በተመሳሳይ ዝግጁነት ላይ ያሉ አይደሉም።

አንዳንድ አገራት ግብረ ኃይል አቋቁመው ክትባቱ ሲመጣ እንዴት መከፋፈል እንዳለበት የሚያስረዳ ፍኖተ ካርታ አዘጋጅተዋል። ሌሎች ደግሞ ክትባቱን ለማከማቸት የሚያገለግል መጋዘን መግዛት አልያም ያላቸውን ለዚህ ዝግጁ እንዲሆን በማድረግ ላይ ናቸው።

ነገር ግን እንደ ፋይዘር ያሉ የኮቪድ-19 ክትባቶች መሠረታዊ ችግራቸው የሚያስፈልጋቸው ማከማቻ መጋዘን ቅዝቃዜው ከዜሮ በታች 70 ዲግሪ ሴንቲግሬድ መሆኑ ነው።

ሌሎች አገራት ከፊታቸው የተደቀነባቸው ፈተና በተለያዩ የማሕበራዊ መገናኛ ብዙኀን ክትባቱ ላይ የሚሰራጩ ሐሰተኛ እና መሰረተ ቢስ መረጃዎች ናቸው።

ይህንን ችግር ለማስወገድ የመረጃን እውነታነት የሚያጣሩ ተቋማት፣ እንዲህ አይነት መረጃዎችን በመሰብሰብ ሐሰተኛነታቸውን እያጋለጡ ሲሆን እንደ ዓለም ጤና ድርጅትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ላሉ ተቋማት መረጃውን በማጋራት የተሻለ ምላሽ በሚያገኙበት መንገድ ላይ እየሰሩ ነው።

በአፍሪካ የክትባቱ ሙከራ እየተካሄደ ነው?

እስካሁን ድረስ አራት የአፍሪካ አገራት የኮሮናቫይረስ ክትባት ሙከራ እያደረጉ ነው።

እነዚህም ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብጽ እና ሞሮኮ ናቸው።

ኬንያና ደቡብ አፍሪካ እየሞከሩት ያለው የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ እና አስትራዜኔካ የባለጸጉት ክትባት ነው።

ግብጽ በበኩሏ ራሷ የሰራችውን እና "ኮቪድ ቫክ 1" ስትል የሰየመችውን ክትባት እየሞከረች ትገኛለች።

ተመራማሪዎች የአፍሪካ አገራት በኮቪድ-19 ክትባት ምርምሮች ላይ አፍሪካውያን መሳተፋቸው ወሳኝ ነው ሲሉ ይመክራሉ።

ይህ ካልሆነ ግን በመላው ዓለም የሚሰራ ክትባት ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት ያደናቅፈዋል ሲሉም ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

የአፍሪካ አገራት የኮቪድ ክትባቶችን መቼ ሊያገኙ ይችላሉ?

የአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ድርጅት እንደሚለው ከሆነ በአህጉሪቱ እስከ ሚያዚያ ወር ድረስ የኮቪድ-19 ክትባት ላይሰጥ ይችላል።

እንደ ድርጅቱ ገለፃ ከሚያዚያ እስከ ሰኔ ባለው ወር ውስጥ ሊጀመር ቢችልም የአህጉሪቱን ሕዝብ 60 በመቶ (700 ሚሊዮን) ሕዝብ ለመከተብ ከ ሁለት እስከ ሶስት ዓመት ድረስ ሊፈጅ እንደሚችል ግምቱን አስቀምጧል።

ይህ ደግሞ አህጉሪቱ በክትባት እንዲሁም አስቀድመው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የተነሳ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የጋርዮሽ የመከላከል አቅም (ሀርድ ኢሚዮኒቲ ) እንድታዳብር የራሱን አስተዋጽኦ የሚጫወት ሲሆን ይህም ቫይረሱ ከአንድ ሰው ወደ ሌላው የመተላለፍ እድሉን በእጅጉ ይቀንሰዋል ይላሉ።

ድርጀቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ ጉባዔ እንዲያካሂድ እና የኮቪድ-19 ክትባትን በተሻለ ፍትኃዊነት ለአለም ሕዝብ እንዴት ማከፋፈል እንደሚቻል እንዲመክር ፍላጎት አለው።

የድርጅቱ ዳይሬክተር ዶ/ር ጆን ንኬጋሶንግ እንዳሉት የገንዘብ አቅማቸው ፈርጣማ የሆነ አገራት የአፍሪካ አህጉር መድሃኒቱን ለማግኘት ስትራኮት ቁጭ ብለው የሚመለከቱ ከሆነ አሳዛኝ ነው።

እነዚህ በምጣኔ ኃብታቸው ኃያል የሆኑ አገራትም ለሕዝባቸው ተጨማሪ ክትባቶችን ለማግኘት ከመድሃኒት አምራች ኩባንያዎች ጋር የሚያደርጉት ስምምነት እና የስምምነት ገንዘብ መጠንም አስጨንቋቸዋል።

ከበጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመተባበር የተሰራ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው በምጣኔ ሃብታቸው ደካማ የሆኑ አገራት ይህ የሐብታም አገራት ጉዳይ ካልተፈታ ክትባት ማቅረብ የሚችሉት ከአስር ዜጎቻቸው መካከል ለአንዱን ብቻ ነው።

አፍሪካ የትኞቹ አገራት መድሃኒቱን ለማግኘት ተማምናለች?

በቅርቡ በተካሄደው የአፍሪካ ቻይና ጉባዔ ወቅት፣ ቻይና የምታዘጋጀው ክትባት ዝግጁ እንደሆነ ለአፍሪካ አገራት ቅድሚያ እንደምትሰጥ ቃል ገብታለች።

ቻይና የክትባት ድጋፍ አደርጋለሁ ብላ ቃሏን ከሰጠቻቸው አገራት መካከል ዛምቢያና ቡርኪናፋሶ ይገኙበታል። ኬንያም አይኗን በቻይና ላይ የጣለች ሲሆን ከአገሪቷ ሕዝብ መካከል 20 በመቶ ያህሉን መከተብ የሚያስችላትን 24 ሚሊዮን ክትባቶች አዝዛለች።

አንዳንድ አገራት ክትባቱን በቀጥታ ለመግዛት የተዘጋጁ ሲሆን፣ በርካቶች ግን ክትባቱን ለማግኘት ኮቫክስ ላይ ተስፋቸውን ጥለዋል።

ኮቫክስ ምንድን ነው?

ኮቫክስ (COVAX) ምጣኔ ኀብታቸው ደካማና መካከለኛ ለሆኑ አገራት ክትባቱን ለማቅረብ ያለመ፣ በዓለም ጤና ድርጅት እና በሌሎች ዓለም አቀፍ የጤና ተቋማት የተመሰረተ ኢኒሼቲቭ ነው።

ሁሉም የአፍሪካ አገራት ይህንን ኢኒሼቲቭ ተቀብለውታል።

ይህም ማለት አፍሪካ በዚህ ኢኒሼቲቭ በኩል ክትባቱ ፍቃድ ካገኘና ከፀደቀ በኋላ፣ 220 ሚሊዮን ክትባቶችን ታገኛለች።

እኤአ በ2021 መጨረሻ ላይ ኮቫክስ 2 ቢሊዮን የኮቪድ-19 ክትባቶችን ለመግዛት እቅድ ይዟል።

ክትባቱን ቀድሞ የሚያገኘው ማን ነው?

ይህ አገራቱ የኮቪድ-19 ክትባትን ስርጭት እንዴት ለማካሄድ በሚወስኑት ውሳኔ ላይ ይመሰረታል።

የዓለም ጤና ድርጅት መመሪያ የጤና ባለሙያዎች የኮሮና መካለከል ላይ ከፊት ያሉ በመሆኑ ክትባቱን ቅድሚያ ማግኘት እንዳለባቸው ያስቀምጣል።

በመቀጠል ደግሞ ወደ አገራት መግቢያና መውጫ ላይ የሚሰሩ ግለሰቦች፣ በእድሜ የገፉ ሰዎችና የተለያዩ ተያያዥ የጤና ችግር ያለባቸው ግለሰቦች ክትባቱን ከሌሎች ዜጎች ቀድመው ያገኛሉ ሲል አስቀምጧል።

ቀሪው ሕዝብ እነዚህ ዜጎች ከተከተቡ በኋላ ይሰጠዋል ሲል የዓለም ጤና ድርጅት በመመሪያ ላይ አመልክቷል።