የአንበጣ መንጋ፡ ምስራቅ አፍሪካ ሁለተኛ ዙር የአንበጣ ወረርሽኝ ስጋት ተደቅኖበታል

ኬንያዊው ገበሬ የበቆሎ እርሻው በአንበጣ መንጋ ከተጠቃበት በኋላ

የፎቶው ባለመብት, FAO/Luis Tato

የምስሉ መግለጫ, ምስራቅ አፍሪካ ባለፉት ዓመታት ከ70 ዓመታት በላይ ያልታየ የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝን አስተናግዷል

ለዓመት ያህል ለመቆጣጠር ጥረት ቢደረግም አዲስ የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ በሚሊዮን የሚቆጠሩ በየመንና በአፍሪካ ቀንድ የሚኖሩ ሕዝቦችን ሕይወት ላይ አደጋ መደቀኑን የተባበሩት መንግሥታት አስታወቀ።

የተባበሩት መንግሥታት በምስራቅ ኢትዮጵያ እና ሶማልያ እንዲሁም ኬንያን ጨምሮ ለአንበጣ መራባት ምቹ ሁናቴ አለ ብሏል።

በቀይ ባሕር ሁለቱም አቅጣጫዎች እየተራባ የሚገኘው አንበጣ በኤርትራ፣ ሳዑዲ አረቢያና የመን ላይ አደጋ መደቀኑን አክሎ ገልጿል።

ምስራቅ አፍሪካ ባለፈው ዓመት ከ70 ዓመታት በላይ ያልታየ የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝን አስተናግዷል።

"ለኬንያ አደጋው የማይቀር ነው፤ ከአሁን ጀምሮ በማንኛውም ወቅት ሊደርስ ይችላል" ያሉት የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት ከፍተኛ የአንበጣ ወረርሽኝ ትንበያ ባለሙያ የሆኑት ኪት ክሬስማን ናቸው።

ስለ ስጋቱ መጠን ሲያስረዱም " ባለፈው ዓመት እንዳየነው የከፋ ሊሆን ይችላል ምክንያቱም በእነዚህ አገራት አንበጣው እየተራባባቸው የሚገኙት ስፍራዎች 350,000 ስኬይር ኪሎ ሜትር ድረስ ስፋት አላቸው።"

በዚህ ዓመት ከታሕሳስ እስከ ነሐሴ ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ምስራቅ አፍሪካ በቢሊዮን የሚቆጠሩ የበረሃ አንበጣዎች በቀጠናው ሰብሎችን ሲያወድሙ ይመለከታሉ ብለዋል።

"በርካታ የግጦሽ ሳር እና ተክሎችን በበረሃ አንበጣው የተነሳ አጥተናል፤ በዚህም የተነሳ ቀላል ቁጥር የማይሰጣቸው የእንስሳት ሀብቶቻችን እየሞቱ ነው" ያሉት ደግሞ በሰሜን ኬንያ የሚኖሩት አርብቶ አደሩ ጎንጆባ ጉዮ ናቸው።

"በበረሃ አንበጣው ወረርሽኝ የተነሳ 14 ፍየሎቸን፣ አራት ላሞች፣ ሁለት ግመሎች አጥቻለሁ። አሁን ደግሞ ተመሳሳይ ነገር ይገጥመናል የሚል ጽኑ ፍርሃት አለን"

የተባበሩት መንግሥታት ምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) አገራት ከዚህ ቀደም ከደረሰው ወረርሽኝ በተሻለ የመከላከል ዝግጅት አላቸው ሲል ተናግሯል።

ኬንያ-የበረሃ አንበጣ በዛፎች ላይ ሰፍሮ

የፎቶው ባለመብት, FAO/Sven Torfinn

እንደ ድርጅቱ ከሆነ ቅኝት የማድረግም ሆነ በምድርና በአየር የፀረ ተባይ ርጭት ለማድረግ ያለው ዝግጁነት እጅጉን የተሻለ ነው። በ10 አገራት በላይም ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር በላይ ከአንበጣ ወረርሽ እንዲያገግሙ ተደርጓል።

ወረርሽኙ ትልቅ ከሆነ ግን ማሕበረሰቦች በአንበጣ መንጋው ሊጥለቀለቁ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ።

የበረሃ አንበጣው እንዲህ አስጊ በሆነ መልኩ እንዴት ሊራባ ቻለ?

ምቹ የአየር ጠባይ

ባለሙያዎች እንደሚሉት ማዕከላዊ ሶማልያ እና ምስራቅ ኢትዮጵያ ከመስከረም እስከ ሕዳር ወር ድረስ ወትሮ ከሚያገኙት መደበኛው የዝናብ መጠን ከፍያ ያለ አግኝተዋል።

ይህም ማለት መሬቱ የተሻለ ለምለም እጽዋት ማብቀል የቻለ ሲሆን ይህም በስፋት ይገኛል።

"ይህ ለበረሃ አንበጣው ምቹ የመራብያ ስፍራ ሆኖታል" ያሉት ክሪስማን " እነዚህ አካባቢዎች ደግሞ በጣም ሰፊ የመራብያ ቀጠናዎች ናቸው" ሲሉ አክለዋል።

ሉካ በሚላል የኢትዮጵያ መንደር የአንበጣ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ባለሙያዎች ርጭት ሲያካሄዱ

የፎቶው ባለመብት, FAO/Michael Tewelde

ይህ ምቹ ሁኔታ ባለበት በሁለት ወራት ውስጥ እንድ ነፍሳት የነበረው በቡድን የሚንቀሳቀስ የበረሃ አንበጣ ሆኖ ሰብሎች ላይ ውድመት ያደርሳል ሲሉም ያብራራሉ።

እንደ ተባበሩት መንግሥታት እና የዓለም ሜቲዎሮሎጂ ድርጅት ሪፖርት ከሆነ የበረሃ አንበጣዎች በፍጥነት ሊራቡ እና በዓመት ውስጥ 160 ሺህ እጥፍ በመሆን ጥፋት ሊያደርሱ ይችላሉ።

ሳይክሎን ጋቲ

ሰሜን ሶማሊያ ያለው የመልከዓ ምድር አቀማመጥ አንጻር ለበረሃ አንበጣ መራባት ሁኔታዎችን አስቸጋሪ ሊያደርገው ይችላል ሲሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ነገር ግን በሕዳር ወር ሳይክሎን ጌቲ በአካባቢው ላይ በመድረስ ተቃራኒውን አደረገ።

በሁለት ቀናትም ውስጥ አካባቢው በሁለት ዓመት የሚያገኘውን ዝናብ በማዝነብ ለበረሃ አንበጣ መራብያነት እንቅፋት የነበረውን አካባቢ ምቹ አደረገው።

ከጎርፉ በኋላ እርጥበታማው አፈር አንበጣዎች እንቁላላቸውን እንዲጥሉ እና እንቁላላቸው ሲፈለፈል የሚመገበው የአረንጓዴ ተክል ፍሪዳ አዘጋጀላቸው።

ሶማሊያ በዚህ ዓመት በአንበጣ ወረርሽኝ ክፉኛ ከተጎዱ አገራት መካከል አንዷ ናት።

በሶማሌ ላንድ የበረሃ አንበጣ የወረረው መሬት

የፎቶው ባለመብት, FAO/Isak Amin

ግጭት

ባለሙያዎች እንደሚሉት በአንበጣ ወረርሽኝ በተጠቁ በርካታ አገራት ቅኝት የማድረግ አቅም ማደጉ ለመከላከል እጅጉን ጠቅሟል።

ነገር ግን በአካባቢዎቹ ያለው የፀጥታ ስጋት እስካልተወገደ ድረስ የአንበጣ መከላከሉን ሙሉ በሙሉ ማሳካት አይቻልም።

"ለምሳሌ በሰሜን ሶማልያ ምንም ዓይነት የቅኝት ሥራ አልተሰራም" ይላሉ ክሪስማን።

ለበረሃ አንበጣ መራቢያነት በርካታ ምቹ ስፍራዎች ካሏቸው አገራት መካከል አንዷ የመን ናት።

ነገር ግን በአገሪቷ በውስጥ ያለው ግጭት በበርካታ አካባቢዎች ቅኝት ለማካሄድ ፈተና ሆኗል።

ባለሙያዎች አክለውም የበረሃ አንበጣዎች ከየመን ተነስተው ወደ ሳዑዲ አረቢያ በመጓዝ ላይ ናቸው።

እነዚህ የበረሃ አንበጣዎች 300 ኪሎ ሜትር ተሻግረው ቀይ በሃርን ማቋረጥ እንዲሁም አየር ላይ ለረዥም ጊዜ መቆየት ይችላሉ።

በኬንያዋ መርሳቤት ፍየሎች ሳር ሲግጡ

የፎቶው ባለመብት, Jeremiah Lekoli

የፀረ ተባይ መድሃኒት ርጭት

በቀጠናው የሚገኙ አገራት በምድርም ሆነ በአየር የፀረተባይ ርጭት ለማካሄድ ተዘጋጅተዋል።

"በእነዚህ በምግብ እህል እጥረትና በድህነት በተጎዱ አገራት ከዚህ ቀደም የተደረጉ የመድሃኒት ርጭቶች ዋጋው ወደ 800 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት፣ 2.7 ሚሊዮን ቶን እህልን ከአንበጣ መንጋጋ ማትረፍ ተችሏል።" ያለው የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት ነው።

ባለሙያዎች ግን ከፊት አፍጥጦ እየመጣ ያለውን ተግዳሮት ለመቋቋም በርካታ ድጋፍ ያስፈልጋል ይላሉ።

በሰሜን ኬንያዋ መርሳቤት የአካባቢ ጥበቃ ተመራማሪ የሆነውና በአንበጣ ወረርሽኝ ቅኝት ላይ የተሰማራው ጄርሜያህ ሌኮሊ " ቅኝቱን እያካሄድን ነው፤ ነገር ግን ምንም አይነት መሳሪያም ሆነ የምንረጨው ፀረ ተባይ አልተሰጠንም" ሲል ተናግሯል።

አክሎም "እነዚህ ነገሮች አሁን ቢኖሩን ጥሩ ነው፤ አለበለዚያ መሳሪያዎቹ የሚደርሱት የበረሃ አንበጣው መጥቶ ውድመቱን አድርሶ ከሄደ በኋላ ይሆናል።"

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ በተጠቁ አገራት ከ35 ሚሊዮን ሕዝቦች በላይ በምግብ እጥረት ክፉኛ ተጎድተዋል ሲል አስጠንቅቋል።

አሁን የሚከሰተውን ወረርሽኝ መቆጣጣር ካልተቻለ ይህ ቁጥር በ3.5 ሚሊዮን ሊጨምር ይችላል ሲልም ተናግሯል።