የአሜሪካ ማዕቀብ በቀጣናው ስትራቴጂያዊ ለውጥን ያስከትል ይሆን?

የኢትዮጵያና የአሜሪካ ባንዲራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ግንቦት 15/2013 የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንቶኒ ብሊንከን በትግራይ ካለው ግጭት ጋር እየተፈፀሙ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ጥቃቶች አገራቸው በተደጋጋሚ ስጋቷን ብታሰማም ትርጉም ያለው ምላሽ ባለመኖሩ አገራቸው የጉዞ እቀባ መጣሏን አስታውቀዋል።

በዚህም በኢትዮጵያና በኤርትራ የቀድሞ እና የአሁን ባለስልጣናት፣ ወታደራዊ እና ደኅንነት ኃላፊዎች እንዲሁም የአማራ ክልል መደበኛና ኢ-መደበኛ የጸጥታ አባላትና ግለሰቦች፣ ሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን ባደናቀፉ የህወሓት አባላት ላይ የቪዛ እቀባ አሜሪካ ጥላለች።

ይህ በግጭቱ ላይ እጃቸው ያለበት ወይም ተባባሪ የሆኑትን የሚመለከት ሲሆን እንዲሁም የቅርብ ቤተሰቦቻቸውም ጭምር እቀባው ተግባራዊ ሊሆንባቸው እንደሚችል የወጣው መግለጫ ጠቁሟል።

ከጉዞ እቀባው በተጨማሪ አሜሪካ የምታደርገውን የምጣኔ ሀብትና የደኅንነት እገዛ እንዲቋረጡና ግጭቱ ካልቆመና መሻሻሎች ካልታዩ፤ ተጨማሪ እርምጃዎችን እንደምትወስድም አስጠንቅቃለች። ሌሎችም አገራት የአሜሪካን ፈለግ እንዲከተሉ ጥሪ አድርጋለች።

ይህ የማዕቀብ ሁኔታ አሜሪካ በኢትዮጵያ የምታደርገው ያልተገባ ጫና አካል ነው በሚልም ኢትዮጵያን አሳዝኗል።

ምንም እንኳን አሜሪካ ለግጭቱ መፍትሄ ለማምጣት ትርጉም ያለው እርምጃ ሊወሰድ አልተቻለም ብትልም ኢትዮጵያ በበኩሏ ከአሜሪካ አስተዳደር ጋር ገንቢ ግንኙነት በመፍጠር በጋራ እየሰራች ነበር ብላለች።

ኢትዮጵያ በትግራይ የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር በጥምረት ሆነው ለመመርመር እየሰሩ መሆናቸውንና ተጠያቂ የሚሆኑበትንም ስራ እያከናወነች እንደሆነ አስታውቃለች።

እንዲሁም በኢትዮጵያ መንግሥት ግብዣ በአፍሪካ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምርመራ እያካሄደ እንደሆነ በመጥቀስ ቀውሱን ለመፍታት ያላትን ቁርጠኝነት ገልጻለች።

አሜሪካ ያሳለፈቻቸው እርምጃዎች የሁለቱንም አገራት የዘመናት ግንኙነት የሚጎዳ ነው ትላለች ኢትዮጵያ። የአሜሪካንን እርምጃዎች በውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ ገብነት ነው የምትለው ኢትዮጵያ፤ አሜሪካ በዚሁ የምትቀጥል ከሆነ ግንኙነታቸውን የምታጤነው መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አሳስቧል።

የማዕቀቡ አንድምታ፤ ስትራቴጂዊ ለውጥ ይሆን?

ኢትዮጵያና አሜሪካ በትግራይ ቀውስ ውስጥ እየተደረጉ ስላሉ እርምጃዎች ተመሳሳይ አረዳድ የላቸውም። በቀጣናው ከአልሻባብ መግነን ጋር ተያይዞ ሸብርተኝነትን ለመዋጋት በሚል የአሜሪካ ቀኝ እጅ የነበረችው ኢትዮጵያና አሜሪካ በትግራይ ባለው ቀውስ ምክንያት ግንኙነታቸው ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።

ለአስርት ዓመታት ኢትዮጵያ የአሜሪካ የደኅንነት አጋር ነበረች የሚሉት የአሜሪካ የቀድሞ ዲፕሎማትና በአትላንቲክ ካውንስል የደኅንነት ኃላፊ የሆኑት ካሜሮን ሀድሰን ናቸው።

ለረጅም ጊዜያት ፖለቲካዊ ድርድሮችንና ሽምግልናዎችን በዋነኝነት በመምራት፣ በሰላም በማስከበር ስምሪት እንዲሁም በአጠቃላይ መረጋጋት በሌለባቸው የቀጣናው አካባቢዎች መረጋጋትን በማምጣት ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሚና መጫወቷን ካሜሮን ይናገራሉ።

ነገር ግን ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ ራሷ መረጋጋት የሌለባት አገር ናት የሚሉት ዲፕሎማቱ፤ አሜሪካም ይሄንን ለመቆጣጠር የራሷን አስተዋፅኦ ማበርከት አለባት ይላሉ።

በተለይም ከማዕቀቡ ጋር ተያይዞ በሁለትዮሽ ግንኙነቱ ላይ አዲስ የሆነ ግንኙነትን የሚያሳይ ነው፤ እንዲሁም አሜሪካ ስትራቴጂያዊ ለውጥን ማድረጓን ጠቋሚ ነው ይላሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰላምና ደኅንነት ጥናት ተቋም ዳይሬክተርና መምህር ዶክተር ዮናስ አዳዬ በበኩላቸው በዲፕሎማቱ ሃሳብ አይስማሙም፤ የአሁኑን ማዕቀብ በአገራቱ መካከል መሰረታዊ የሚባል የርዕዮተ ዓለም ልዩነት የሌለበት ስለሆነ "ጊዜያዊ ነው" በማለት።

ኢትዮጵያ ካላት መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ አንጻር ስትራቴጂክ ቦታ ላይ ከመሆኗም ጋር ተያይዞ አሁንም በምሥራቅ አፍሪካም ሆነ በቀጣናው ካሉ አገራት ከኢትዮጵያ የተሻለ ወዳጅ ለአሜሪካ ማግኘት ያስቸግራል ብለው እንደሚያምኑ ምሁሩ ይናገራሉ።

ለዚህም እንደ ዋቢ የሚጠቅሱት የሶማሊያ በአልሻበብ ቁጥጥር ስር መውደቅ፣ የሶማሌላንድና የፑንትላንድ ዕውቅና አለማግኘት፣ በኬንያና በሶማሊያ መካከል ያለው የሻከረ ግንኙነት፣ የሱዳን የሽግግር መንግሥት ትርምስ ውስጥ መሆኑ ኢትዮጵያ አሁንም ለቀጣናው የተሻለች የአሜሪካ አጋር ናት እንዲሉ አስችሏቸዋል።

በተለይም አሜሪካ የምጣኔ ሀብትና የደኅንነት ድጋፍ እቀባ ማድረጓን ተከትሎ አገራቱ ሽብርተኝነትን በጋራ እንዋጋለን የሚሉትን ፕሮጀክት እንዲቆም አያደርገውም ወይ? ብለው በርካቶች ጥያቄ ያነሳሉ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቃል አቀባዩ ዲና ሙፍቲ በኩልም በሰጠው መግለጫ እርምጃው ቀጣናውን ችግር ላይ የሚጥል እንዲሁም ኢትዮጵያ በፀረ-አልሻባብ የሽብር መከላከል እና በሰላም ጥበቃ ላይ ያላትን ሚና በጉልህ የሚጎዳ ሲሉ ተችተውታል።

ዶክተር ዮናስም በተመሳሳይ መልኩ "ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ለአሜሪካ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ቀኝ እጅ ነበረች አሁንም ናት" ብለው ያምናሉ።

የዲፕሎማቱ ካሜሮን ሀድሰን እይታ ግን ከውጭ ጉዳይ መግለጫም ሆነ ከምሁሩ አስተያየት ለየት ይላል። አገሪቱ በአሁኑ ወቅት በውስጧ ካለው ቀውስ የተነሳ ለዓመታት የሚጠበቅባትን በቀጣናው የተጫወተችውን ሚና በአሁኑ ወቅት መጫወት አትችልም ይላሉ።

"ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ በሕዝቡ ላይ የምታደርገውን ጦርነት ለማካሄድ አዳዲስ የደኅንነት አጋሮችን እንደነ ሩሲያ፣ ቻይናና የባሕረ ሰላጤው አገራትን አገራትን አጋርነትን እየተመለከተች ነው። ሁኔታዎች በዚሁ የሚቀጥሉ ከሆነ እነዚህን የመሳሰሉ የደኅንነት ግንኙነቶች በአፍሪካ ቀንድ ያለውን የምዕራባውያን ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ ስትራቴጂያዊ ለውጥ ያስከትላል" ይላሉ።

አሜሪካ ከዚህ ቀደም ከፀረ-ሽብር ጋር በተገናኘ ለኢትዮጵያ ስልጠናዎችን፣ እንዲሁም የደኅንነት መረጃዎችን በመለዋወጥ ይሰሩ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም የቀድሞው የሲአይኤ አባል የነበሩት ዲፕሎማት ሀድሰን እንደሚሉት አሜሪካ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የጦር መሳሪያም አቀባይ ነበረች።

በቅርቡ ያወጣችው የጉዞ እቀባና 'ዲፌንስ ትሬድ ኮንትሮል ፖሊሲ' ያለችውን ተግባራዊ እንደምታደርግም አሜሪካ አስታውቃለች። ይህ ፖሊሲ ምንን ያካትታል? ለዲፕሎማቱ ቢቢሲ ያቀረበላቸው ጥያቄ ነው።

እሳቸውም በምላሹ የትኛውም እርምጃ በሕዝብ ላይ ጥፋት የሚፈፀምበት የቴክኖሎጂ ግብአት ላይ ከሚደረግ ቁጥጥር ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይናገራሉ።

ሰፋ ያለ ይዘት ያለው ይህ ፖሊሲ የኮምፒውተር ቴክኖሎጂን ጨምሮ፣ ሶፍትዌሮች፣ ክትትልና ቁጥጥር የሚደረግባቸው ቁሳቁሶችና ረቀቅ ያሉ ወታደራዊ ቴክኖሎጂን ያካትታል።

በተጨማሪም ከዚህ ቀደም የተለገሱ በአሜሪካ የተሰሩ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን መጠገን አስፈልጎ መለዋወጫ ቢያስፈልግ በዚህ እቀባ መሰረት ኢትዮጵያ ይሄንን ማካሄድ አትችልም ይላሉ።

የሁለቱ አገራት ግንኙነት መበላሸት

ኢትዮጵያና አሜሪካ ከመቶ ዓመታት በላይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን በሊግ ኦፍ ኔሽንም ሆነ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምስረታ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል የሚሉት ዶክተር ዮናስ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ኢንዱስትሪዎችና ተቋማት ከአሜሪካ ጋር ትስስር አላቸው ይላሉ።

የሁለትዮሽ አጋርነታቸውም ነፀብራቅ የሚባሉት በትምህርት ተቋማት እንዲሁም የአሜሪካ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የነበራትን ሚና እንደ ምሳሌ በማንሳት አሜሪካ ለዘመናት የኢትዮጵያ የልማት አጋር ሆና ቀጥላለች ይላሉ።

ለዚያም ነው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማዕቀቡን የሁለቱን አገራት ታሪካዊ ግንኙነት የማይመጥንና የመቶ ሃያ ዓመታቱንም ግንኙነት "በዜሮ ያባዛው" ያለው።

በአገራቱ መካከል ያለውን ታሪካዊ ዳራ በምንመለከትበት ወቅት ሻክሮ የነበረው ደርግ ኢትዮጵያን ያስተዳድር በነበረ ወቅት ነበር። ኢህአዴግ ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ ግን ግንኙነታቸው ጠንካራ የሚባል እንደሆነ ይነገራል።

ዲፕሎማቱም አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ እንዲህ አይነት እርምጃ ወስዳ አታውቅም ይላሉ። በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል የተወሰነ ውጥረት የነበረው የኢትዮ-ኤርትራን ጦርነት ተከትሎ በአሜሪካ የቀረበው የተባበሩት መንግሥታት የጦር መሳሪያ ማዕቀብ በሁለቱ አገራት መጣሉን ተከትሎ እንደሆነ ያወሳሉ።

አሜሪካ በማንኛውም በኩል ከኢትዮጵያ ጋር የነበራትን አጋርነት አልተወችም የሚሉት ዶክተር ዮናስ ይህ እቀባ "ማስደንገጥ የለበትም" ይላሉ። ለምሳሌ ያህልም ኢህአዴግ በ2002 ምርጫ መቶ በመቶ አሸንፌያለሁ ብሎ የፓርላማ ወንበሩን ከተቆጣጠረ በኋላ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ነው ብለው ማፅደቃቸውን በማውሳት ነው።

"ይህ ሁኔታ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ያሳዘነ ነበር" ይላሉ። በአፍሪካ ውስጥ "ኢትዮጵያ የአፍሪካ ፖለቲካ መዲና ናት" የሚሉት ዶክተር ዮናስ "ኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት እቀባም አሜሪካንም ሆነ ኢትዮጵያን ይጎዳል" ይላሉ።

በተለይም ኢትዮጵያ የራሷን አፀፋዊ እርምጃዎች የምትወስድ ከሆነ ሁኔታዎች ሊጋጋሉና ቀጣናው የአሸባሪዎች መፈንጫ ሊሆን እንደሚችል ምሁራዊ እይታቸውን ይሰጣሉ።

በተለይም በቀጣናው የደኅንነት ስጋት ቢፈጠር ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የአፍሪካ ቀንድም ሆነ ወደ ሌሎች አካካቢዎች አንደሚዛመትና ጉዳቱም ሰፋ ያለ መልክ ሊኖረው እንደሚችል በአፅንኦት ያስረዳሉ።

"በነገራችን ላይ የደኅንነትና የሰላም ጥናት ድንበር አይከፋፍልም። አንድ አካባቢ ያለው የደኅንነት ሁኔታ ከተጎዳ መላው ዓለም ነው የሚጎዳው። ለምሳሌ ከዓመታት በፊት በአሜሪካ ላይ ተፈጸመው የመስከረም 11ዱን ጥቃት ብንወስድ፤ ባደጉም ይሁን ባላደጉ አገራት ውስጥ ከፍተኛ ትርምስ ነው የፈጠረው" የሚሉት ዶክተር ዮናስ የአንድ አገር ደኅንነት ወይም ሰላም የሚባል የለም በማለት የአገራቱ እጣ ፈንታ በከፍተኛ ሁኔታ የተሳሰረ እንደሆነ ይተነትናሉ።

ዲፕሎማቱም በበኩላቸው ማዕቀቡ ኢትዮጵያ ከምዕራቡ ዓለም ጋር በነበራትን ግንኙነት ላይ ስትራቴጂያዊ ለውጥ እንደሚያመጣ ጠቁመው፤ ይህም ሁኔታ አሜሪካ በቀጣናው ላይ ያላትን ስትራቴጂያዊ ፍላጎቶችም ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እንደሚያደርስ አልደበቁም።

በተለይም ኢትዮጵያ በውስጧ ሰላም ካልሰፈነባትና አጋርነቷ ከቀረ አሜሪካ በቀይ ባሕር ዙሪያ ደኅንነትንም ሆነ መረጋጋት ለማምጣትም እንዲሁም ተፅእኖ ለመፍጠር ፈተና እንደሚሆንባት ያስረዳሉ።

የአሜሪካ ስጋት ምንድን ነው?

በትግራይ ካለው ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ጥቃትና አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ችግር በተጨማሪ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ባወጣው መግለጫ፤ በትግራይ ክልል እንዲሁም በአገሪቱ ላይ የተጋረጡት የሉዓላዊነት፣ ብሔራዊ አንድነትና የግዛት ጉዳይ ከፍተኛ ስጋት አሳድሮብኛል ይላል።

የኢትዮጵያና የኤርትራ ወታደሮች ጨምሮ ሌሎች ታጣቂዎች እርዳታ እንዳይደርስ እክል መፍጠር፣ በክልሉ ውስጥ ያሉ ግድያዎች፣ በአስገዳጅ ሁኔታ መፈናቀል፣ መዋቅራዊ የሆነ ወሲባዊ ጥቃት፣ ሆስፒታሎችና የህክምና ተቋማት መውደም አሜሪካ እንዳሳሰባት ትገልጻለች።

እንዲሁም የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ቀጥለዋል የምትለው አሜሪካ ተደጋጋሚ ጉትጎታዎችን ባደርግም ለቀውሱ ፖለቲካዊም ሆነ ሰላማዊ መፍትሄ መምጣት አልተቻለም ትላለች። በዚህም ምክንያት የወሰደችው እርምጃ አስፈላጊ ነው ትላለች።

ዶክተር ዮናስ በበኩላቸው ሁለቱንም አገራት ይጎዳል ያሉት ይህን ማዕቀብ በተሳሳተና በደንብ ባልተጠና መረጃ ላይ ተመስርቶ የተወሰደ ነው ይላሉ።

ምሁሩ በአውሮፓውያኑ 2003 አሜሪካ ኢራቅን መውረሯን እንደ ምሳሌ በማንሳትም በወቅቱ አሜሪካ ምክንያት ያደረገችው ኢራቅ ጅምላ ጨራሽ መሳሪያ አላት የበሚል ነበር። ነገር ግን መሳሪያው አለመኖሩ የታወቀው ኢራቅ ከፈራረሰችና ከዘገዬ በኋላ መሆኑን ታሪክን ያጣቅሳሉ። በተመሳሳይም አፍጋኒስታንን በማንሳት ከቀደመ ስህተት መማርና ማገናዘብ እንደሚገባ ያወሳሉ።

"በስሜት የሚደረጉ ነገሮች የሚያሳዝኑ ይሆናሉ። በዚህ ትብብር ወቅት ኢትዮጵያን በግድ አንበረክካታለሁ ብሎ ማሰቡ በተለይም በጣም ካደጉ አገራት የሚጠበቅም አልነበረም። በተለይም የኢትዮጵያና የአሜሪካ ግንኙነት ረዥም ዘመናት ያስቆጠረ ከመሆኑ አንፃር። ይሄንን በድጋሚ ያጤኑታል ብዬ አስባለሁ" ይላሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥትም በተለይም አሜሪካ ከምታወጣቸው መግለጫዎች ጋር በተያያዘ በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብተው ጫና ለመሞከር የሚሞክሩ መንግሥታት ተቀባይነት አይኖረውም ሲል መደመጡ ይታወሳል፟።

ከዚህም በተጨማሪ በትግራይ ክልል ቀውስና ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ምዕራባውያን እንዲሁም አሜሪካ ከፍተኛ ጫና እያሳደረች ነው ያሉ ተቃውሟቸውን በአዲስ አበባ እንዲሁም በሌሎች አገራት በበይነ መረብ አሰምተዋል።

የኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን የውሃ ሚኒስትሮች እንዲሁም የሕግ እና የውሃ ጉዳይ የቴክኒክ ባለሞያዎች በዋሽንግተን ዲሲ ሲደራደሩ በነበረበት ወቅት፤ በዓመታት የተራዘመ ድርቅ እንዲሁም በተራዘመ ዓመታት አነስተኛ የውሃ ፍሰት ላይም መሰረታዊ መግባባት ተደርሷል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ያለምንም ውጤት መቋረጡ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ዋሽንግተን ሲካሄድ የነበረውንም ድርድር ያቋረጠችበት ምክንያት በግብጽ ፍላጎት ታዛቢ እንዲሆኑ የገቡት አሜሪካና የዓለም ባንክ ለግብጽ ከመወገን አልፈው የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን ላይ ጫና ለማሳደር ሞክረዋል በማለት ኢትዮጵያ መውቀሷ የሚታወስ ነው።

አሜሪካ፣ የዓለም ባንክ ከግብጽ ጎን ቆመው ነበር በተባለው በዚህ ድርድር ላይ ከመጀመሪያው ሙሌት በኋላ ኢትዮጵያ ለምትጠቀመው ውሃ ለግብጽ የተጠራቀመ የውሃ ጉድለት ማካካሻ እንድትሰጥ የሚያስገድድ እንደሆነም ተገልጾ ነበር።

ከዚህም ጋር በተያያዘ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሕዳሴ ግድቡ ድርድር ምክንያት ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን 100 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደማይሰጥ ገልፀው ነበር።

ከዚህም ጋር ተያይዞ የአሜሪካ የአሁኑ ማዕቀብ የትግራይ ግጭት ብቻ አይደለም የሕዳሴ ግድብም ነው የሚሉ አልታጡም።

ነገር ግን የአትላንቲክ ካውንስሉ ካሜሩን ሀድሰን በበኩላቸው "የአሜሪካ ዋነኛ ስጋት በትግራይ ያለው ጦርነት እንዲሁም በአገሪቱ ያለው አለመረጋጋት አገሪቷን አንዳይበታትናት የሚል ፍራቻ ነው" ይላሉ።

ምንም እንኳን የተጣለው ማዕቀብ አገሪቱን የበለጠ እንዳያዳክማት አሜሪካ ብትሰጋም "በትግራይ ውስት እየተፈፀመ ካለው የመብት ጥሰት ክብደት አንፃር ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ሆና አግኝታዋለች" ይላሉ።

እቀባው ጣልቃ ገብነት ወይስ?

ዲፕሎማቱ ጠንከር ያለ እርምጃ ቢሉም ለዶክተር ዮናስ በአገራት ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ መግባትና በጉልበት ለመፍታት መሞከር "ጊዜ ያለፈበት የፖለቲካ አካሄድ ነው" ይላሉ።

"ሁላችንም እንደ መረብ የተያያዝን ዓለም ላይ ስለምንኖር አንዱ ሌላውን ገፍትሮ፣ አንዱ የሌላው የበላይ፣ አዛዥና ናዛዥ ሆኖ፤ ሌላኛው ታዛዥ ሎሌ ወይም ባርያ ሆኖ ለመኖር ጊዜው አልፏል" የሚሉት ዶክተር ዮናስ "21ኛው ክፍለ ዘመን አገራት ችግሮቻቸውን በአንድነት ተባብረው የሚፈቱበት ዘመን እንጂ አንዱ ሌላኛውን አስፈራርቶ ችግር ሊፈታ አይችልም" ይላሉ።

ይህንንም ከግምት ውስጥ በማስገባት ለዘመናት የቆየው ግንኙነት እንዳይበላሽና ዘላቂው ጥቅም እንዲጠበቅ ውሳኔው መጤን አለበት በማለትም ምክር ይለግሳሉ።

"አሜሪካ ለራሷም ጥቅም ለራሷም ክብር ሲባል የወሰደችውን አቋም እንደገና ማጤንና መገምገም አለባት" በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ለመሆኑ አሜሪካ ኢትዮጵያ እቀባውን የጣለችውም ሆነ ምክር ቤቱ ያሳለፈው ውሳኔ አገሪቷ ምን እንድታደርግ የሚጠይቅ ነው?

ጥሰቶችን በገለልተኛ አካላት ተጣርተው ጥፋተኞቹ ተጠያቂ እንዲሆኑ፣ ሰላማዊ ዜጎች እንዲጠበቁ፣ የሰብዓዊ ድጋፎች ያለምንም እክል እንዲደርሱ እንዲሁም የኤርትራ መንግሥትም ሠራዊቱን በአስቸኳይ ከክልሉ እንዲያስወጣና ዓለም አቀፍ እውቅና ወዳለው የኤርትራ ግዛት እንዲመለሱ የሚጠይቅ ነው።

ግጭቱ እስካልቆመና ሰብዓዊ እርዳታዎችን ማቅረብ ካልተቻለ ያለው የምግብ ደኅንነት ስጋት ወደ ረሃብ ይቀየራል ይላል። የትግራይን ቀውስ ማስቆም የማይችሉ ከሆነ ከአሜሪካም ሆነ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሌሎች እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል የሚለው የአሜሪካ ሐሳብ በኢትዮጵያ ላለው ቀውስ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲመጣ አገራቸው እንደምትሰራ ዘርዝሯል።

ኢትዮጵያ በበኩሏ በክልሉ ተፈፀሙ የተባሉ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ከአለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመመርመር ተጠያቂ ለማድረግ እየሰራች እንደሆነና በተመሳሳይም የሰብዓዊ እርዳታም ባልተገደበ ሁኔታ እርዳታ እንዲቀርብ እየሰራሁ ነው ብላለች። ነገር ግን ያላት አቅም ውስን መሆኑንም አስታውቃለች።

ኢትዮጵያ ባወጣችው በዚሁ መግለጫ ላይ አሜሪካ በዋነኝነት ስለምትጠቅሰው የኤርትራ ሠራዊት መውጣት ጉዳይ የተጠቀሰ የለም። ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ መንግሥት የኤርትራ ወታደሮች በቅርቡ እንደሚወጡ አስታውቆ ነበር።

አሜሪካ የምታወጣው መግለጫዎችን በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ነው እያለ ሲወቅስ የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት እቀባውን ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቃል አቀባዩ በኩል በሰጠው መግለጫ "የኢትዮጵያ ነፃነትና ሉዓላዊነት በገንዘብ የማይቀየር ቀይ መስመር ነው" ብሎታል።

በተለይም በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑት ኃይሎች ወደ ድርድር መምጣት አለባቸው የሚለው ጥረት በመንግሥት በኩል ፍፁም ተቀባይነት እንደሌለው በተደጋጋሚ ተገልጿል።

እቀባውንም ተከትሎ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ "ሽብርተኛ ተብሎ ከተሰየመው ህወሓት ጋር ድርድር ማድረግ እንደማይቻል ከግንዛቤ ሊገባ ይገባል" በማለት ቡድኑ መልሶ እንዲያንሰራራ የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ አሉታዊ ውጤት የሚኖረውና የማይሳካ መሆኑ ተጠቅሷል።

ዶክተር ዮናስም በበኩላቸው ከህወሓት ጋር ጦርነት ከመጀመሩ በፊት በተለያዩ አካላት ወደ ድርድር ለማምጣት እንዲሁም በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ከፍተኛ ጥረት መደረጉን አስታውሰው በወቅቱ አሜሪካም የራሷን ድርሻ መጫወት ትችል ነበር ይላሉ።

"የኢትዮጵያ ምክር ቤት ተሰብስቦ ህወሓትን በሽብርተኝነት ከፈረጀው በኋላ እንደገና ህወሓትን ከዚያ ውስጥ ለማውጣትና እንደ መንግሥት ሁለቱን እኩል አድርጎ ለድርድር ግቡ ማለት ቅንነት ያለው አይመስለኝም" ብለዋል።

የአሜሪካ መንግሥት በአገሪቱ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት "ሽብርተኛ ቡድን" ተብሎ የተሰየመውን ህወሓት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በእኩል የመመልከት ዝንባሌ እንዳስቀየመው አስፍሯል።