በርካቶች የሚበለጽጉበት የኢንተርኔት ማጭበርበሪያ ዘዴዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአፍሪካ ጋዜጠኞች ለቢቢሲ በሚልኩት ሳምንታዊ ደብዳቤ በርካታ ጉዳዮች ይዳስሳሉ። በዚህ ሳምንት ኬንያዊው ጋዜጠኛ ዋሂጋ ምዋራ በክሪፕቶከረንሲ ስለሚፈጸሙ ማጭበርበሮች የሚከተለውን ጽፏል።

ከዚህ በፊት ከማላውቀው ዶክተር የስልክ ጥሪ ደረሰኝ። ደዋዩም ኬንያዊ የሆነ ቢሊየነርን ስለ በቢትኮይን ጉዳይ ቃለ-መጠይቅ አድርጌለት እንደሆነ ጠየቀኝ።
ወዲያው በበይነ መረብ አጭበርባሪዎች እጅ መውደቁ ገባኝ። ትንሽ ሀሳብ ገባኝ፤ ምክንያቱም ላለፉት ሁለት ዓመታት አንድ ኬንያዊ ቢሊየነርን በማነጋገር ክሪፕቶከረንሲ ላይ ዘገባ እንደሰራሁና ሰዎች እንዲጠቀሙት ስመክር እንደነበር የሚገልጹ በርካታ የሐሰት ማስታወቂያዎችን ተመልክቻለሁ።
ምንም እንኳን ባገኘሁት አጋጠሚና በሁሉም የማህበራዊ ትስስር ገጾቼ በኩል ኬንያውያን የዚህ ማጭበርበር ሰለባ እንዳይሆኑ በተደጋጋሚ መልዕክቴን ባስተላልፈም አጭበርባሪዎቹ የድረ-ገጽ አድራሻቸውን በመቀየርና ሌሎች እውነት የሚመስሉ ማሳሳቻዎችን በመጠቀም ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ኢላማ አድርገው እየሰሩ ይገኛሉ።
በርካቶችም በቀላሉ ከችግራቸው ለመላቀቅ አልያም በድፍረት ትርፍ ካገኘን በማለት ወደእነዚህ አጭበርባሪዎች ይሄዳሉ አልያም አጭበርባሪዎቹ ወደነሱ እንዲመጡ ይፈቅዱላቸዋል።
በቅርቡ በርካቶችን ካጭበረበሩ አሰራሮች መካከል ‘አማዞን ዌብ ወርከር አፍሪካ’ የተሰኘው መተግበሪያ ነው። አጭበርባሪዎቹ ይህ ድርጅት የአሜሪካው አማዞን እህት ኩባንያ እንደሆነ በማስመሰልና ሰዎች በቀላሉ በስልካቸውእንዲሁም በበይነ መረብ በኩል እንደ ላፕቶፕ በመሳሰሉ በማንኛውም መገልገያዎች እንዲያገኙት አድርገዋል።
ነገር ግን ይህ ድረ-ገጽ ከአሜሪካው አማዞን ጋር ምንም ግንኙነት የለውም።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በዚሁ መተግበሪያ ላይ ገንዘባቸውን ፈሰስ ያደረጉ ኬንያውያን መተግበሪያው ከበይነ መረብ ላይ መሰረዙን አስተዋሉ። አንዳንዶች በሺዎች የሚቆጠሩ ዶላሮችን ያስቀመጡ ሲሆን መተግበሪያው ሊሰረዝ እንደሆነ አልያም ገንዘባቸውን ቀድመው እንዲያወጡ የተነገራቸው ነገር አልነበረም። በዚህም ምክንያት ገንዘባቸው የትእንደገባ እንኳን አያውቁም።
ይህ መተግበሪያ በዋነኛነት ሲንቀሳቀስ የነበረው ደንበኞች ወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዲጠቀሙት እንዲያደርጉና ባመጡት ሰው ልክ ገንዘብ ይከፈላቸዋል በሚል ነው። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ደንበኞች ገንዘባቸውን በዚህ መተግበሪያ በኩል የሚያስቀምጡ ከሆነ በወራት ውስጥ ከወለድና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች ትርፍ እንደሚያገኙ ተገልጾ ነበር።
ልክ መተግበሪያው በድንገት ሲጠፋ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኬንያውያን በማህበራዊ ሚዲያ በኩል ስጋታቸውን ሲገልጹ የነበረ ሲሆን አብዛኛዎቹ ያጋሩት ታሪክ ተመሳሳይ ነበር። ሁሉም መተግበሪያውን መጠቀም የጀመሩት በሚያውቋቸው ሰዎች ገፋፊነት እንደሆነና ገንዘባቸውን እንዴት ማስመለስ እንደሚችሉ ሲጠይቁ ነበር።
ነገር ግን መጨረሻ ላይ የኬንያ ባለስልጣናት አንድ ጥሩ ዜና ይዘው ብቅ አሉ። ከዚህ ‘አማዞን ዌብ ወርከር አፍሪካ’ ከተሰኘው የማጭበርበሪያ ስርአት ጋር በተያያዘ 50 ዓመት አሜሪካዊት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታወቁ።
ፖሊስም ተጠርጣሪዋ ተመሳሳይ ተግባር ከሚፈጽም ትልቅ የወንጀለኞች ቡድን አባል መሆኗን በመግለጽ በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርና የበይነ መረብ ማጭበርበር ክስ እንደሚቀርብባት ገልጿል።
በኬንያ ያለው ከፍተኛ ስራ አጥነት ምናልባት ለዚህ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ያለ ይመስለኛል።
ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በፊት የኬንያ ስታቲስቲክስ ቢሮ ባወጣው መረጃ መሰረት በአውሮፓውያን 2020 የካቲት ወርላይ 40 በመቶ የሚሆኑት የአገሬው ወጣቶች ሥራ አጥ ነበሩ። ሶስተኛ ዙር የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ አገሪቱን እያጠቃ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ደግሞ የስራ አጦች ቁጥር ከተጠቀሰውም በላይ ከፍ ሊል እንደሚችል መገመት ከባድ አይደለም።
በቅርብ ወራት ደግሞ ብዙ አይነት የማጭበርበር መንገዶች ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው። የሚሸጡ መሬቶች፣ በጣም አስገራሚ የግብርና ኢንቨስትመንቶች፣ የቤት ሽያጭ፣ የበይነ መረብ ግብይትና በቅርቡ ደግሞ ክሪፕቶከረንሲ ሰዎችን ለማጭበርበር በተደጋጋሚ የሚጠቀሱ ነገሮች እየሆኑ መጥተዋል።
ክሪፕቶከረንሲዎችን በመጠቀም የሚከናወነው ማጭበርበር፤ ደንበኞች መጀመሪያ ላይ የቻሉትን ያክል ገንዘባቸውን ፈሰስ ያደርጉና በምላሹ ደግሞ ትርፍ ይሰጣችኋል በሚል ነው።
ከዛ በኋላ ደንበኞች ሌሎች ሰዎችን ወደዚህ አሰራር ማምጣት ካልቻሉ ትርፋቸው እየቀነሰ ይመጣል። እንዲህ አይነት አሰራር በመከተል ደንበኞች ሌሎች በርካታ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን እንዲያስገቡ ያደርጋል። ነገር ግን እንዚህ ደንበኞች በትክክል አሰራሩ እንዴት እንደሆነ አይነገራቸውም።
በዚህ ምክንያት ከላይ ያሉትና መጀመሪያ አካባቢ ገንዘባቸውን ፈሰስ ያደረጉት ደንበኞች በተለያዩ ምክንያቶች አልያም ትርፉ አላዋጣም ብሏቸው ጥለው ሲወጡ ከስራቸው ያሉ በርካቶችን ገንዘብ ይዘው ነው የሚሄዱት።
በቅርቡ በተሰራ ጥናት ኬንያ ውስጥ ብቻ የሚገኙ ኢንቨስተሮች በዚህ የክሪፕቶከረንሲ ማጭበርበር ምክንያት እስከ 25 ሚሊየን ዶላር እንደከሰሩ ተገልጿል። ገንዘባቸውንም መልሰው አላገኙም።
በአንድ ወቅት ወደ 30 ሺህ ዶላር በዚሁ አሰራር የተጭበረበረ ግለሰብ የማነጋገር እድል አጋጥሞኝ ነበር። በሚያስገርም ሁኔታ የተሻለና አዋጭ የሚመስል እድል ካገኘ በተመሳሳይ መልኩ ኢንቨስት ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ነግሮኛል።
እንዲህ አይነት አመለካከት ያላቸው ሰዎች ባሉበት ሁኔታ እነዚህ አጭበርባሪዎች ይጠፋሉ ብሎ ማሰብ ደግሞ ከባድነው።












