የቻይና ዩኒቨርስቲ በሃንጋሪ ይከፈታል መባሉን በመቃወም በርካቶች ጎዳና ላይ ወጡ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በሃንጋሪ መዲና ቡዳፔስት የቻይና ዩኒቨርስቲ ይከፈታል መባሉን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ የአገሬው ነዋሪዎች ተቃውሟቸውን በጎዳና ላይ አሰምተዋል።
ይህንን የቻይና ዩኒቨርስቲ ፕሮጀክት እየተቃወሙ ያሉት አካላት እንደ መከራከሪያነትም የሚያነሱት አገሪቷ ለከፍተኛ ትምህርት የምትመድበውን በጀት ይቀንሰዋል እንዲሁም የቻይና ኮሚዩኒስት ባለስልጣናትን ጫናም በአገሪቷ ላይ ከፍ ያደርገዋል የሚል ነው።
ከቀኝ ክንፍ የሚመደቡት የሃንጋሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን ከቻይና ባለስልጣናት ጋር ጥብቅ ቁርኝት አላቸው።
በዚሁ በያዝነውም ወር የአውሮፓ ህብረት ቻይና በሆንክ ኮንግ ላይ ወቀሳን ያዘለ መግለጫ ለማውጣት ቢሞክርም ሃንጋሪ እንዲታገድ አድርጋዋለች።
የቻይና ፉዳን ዩኒቨርስቲ በሃንጋሪም ቅርንጫፍ የመክፈቱን ዕቅድ የታቀወሙ በርካቶች በጎዳናዎች ላይ የታዩ ሲሆን ወደ ፓርላማው ህንፃም አምርተዋል።
" ቪክቶር ኦርባንና የቀኝ ክንፍ ፓርቲ አባላቱ ራሳቸውን ፀረ-ኮሚዩኒስት ነን በማለት ይናገራሉ። ተግባራቸው ግን የሚያሳየው ኮሚዩኒስቶቹ ጓደኞቻቸው ናቸው" በማለት ስዞንጃ ራዲስክ የተባለ ለተቃውሞ የወጣ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግሯል።
ሌላኛው ፓትሪክ የተባለ ለተቃውሞ የወጣ ተማሪ በበኩሉ መንግሥት ለፉዳን ዩኒቨርስቲ ፕሮጀክት የሚያወጣውን ገንዘብ "የራሳችንን ዩኒቨርስቲዎች ለማሻሻል ብንጠቀምበት የተሻለ ነው" በማለት ለሮይተርስ ተናግሯል።
በቡዳፔስት ይገነባል የተባለው የፉዳን ዩኒቨርስቲ 1.8 ቢሊዮን ዶላር ያስወጣል ተብሎ ዕቅድ ተይዞለታል። ይህም ማለት መንገትሥት ከሁለት አመት በፊት በአጠቃላይ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያወጣውን ገንዘብ ይበልጣል ተብሏል።
ከዚህ ወጪ 1.5 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነው ወጪ ከቻይና ባንክ በብድር የሚገኘ መሆኑንንም ዲሬክት36 የተባለ የአገሪቱ የምርምር ዘገባ አገኘሁት ያለውን ሪፖርት ጠቅሶ አስፍሯል።
ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን የቡዳፔስት ከንቲባ ጌርግሊ ካርክሶኒ ተቃውመውታል።በዚህ ሳምንት በቻይና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠቂ ለሆኑም ጎዳናዎች እሰይማለሁ ብለዋል።
ፉዳን ዩኒቨርስቲ በቻይና ውስጥ ስመ ጥር ከሆኑ የትምህርት ተቋማት አንዱ ነው። በቡዳፔስት የሚገኘው ቅርንጫፍ ከሁለት አመታት በኋላ ይጠናቀቃል የተባለ ሲሆን በአውሮፓ ህብረት አባላት አገራትም የመጀመሪያው ነው።












