በቡርኪናፋሶ በደረሰ ጥቃት ከ130 በላይ የአንዲት መንደር ነዋሪዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በቡርኪናፋሶ በደረሰ ጥቃት ከ130 በላይ የአንዲት ነዋሪዎች መገደላቸው ተገልጿል።
በሰሜን የአገሪቷ ግዛት የደረሰው ይህ ጥቃት በታጣቂዎች የተፈፀመ ሲሆን መንግሥትም እስካሁን ከደረሱት ከፍተኛው ነው ብሏል።
ሶልሃን የተባለችውን መንደር ታጣቂዎች ከበው በርካታ ቤቶችንና የአካባቢውንም ገበያ በአንድ ምሽት አቃጥለዋል።
ለዚህ ጥቃት ኃላፊነቱን የወሰደ አካል ባይኖርም በድንበር አካባቢ ፅንፈኛ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ ጥቃት ያደርሳሉ ይባላል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ኃላፊ ጥቃቱን "አሰቃቂ" ሲሉ በከፍተኛ ሁኔታ እንዳሳዘናቸውም አስታውቀዋል።
ኃላፊው አንቶኒዮ ጉተሬዝ "ይህንን አሰቃቂና አፀያፊ ጥቃት እናወግዛለን። ጥቃቱም ፍንትው አድርጎ ያሳየን አገራት የበርካቶችን ህይወት እየቀጠፈ ያለውን ፅንፈኝነት ለመዋጋት በሚያደርጉት ጥረት አለም አቀፉ ማህበረሰብ ከፍተኛ ርብርብና ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ ነው" በማለት በቃለ አቀባያቸው በኩል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የቡርኪናፋሶ ፕሬዚዳንት ሮች ካባሬ በዚህ ጥቃት ህይወታቸውን ላጡት የሶስት ቀን ኃዘን ያወጁ ሲሆን በትዊተር ገፃቸውም ባስተላለፉት መልዕክት "አነዚህ የጥፋት ኢላማዎችን ለመቋቋም በአንድነት መቆም አለብን" ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ አክለውም የነዚህን ንፁኃን ህይወት የቀጠፉትን ታጣቂዎቸም በቁጥጥር ስር ለማዋል የፀጥታ ኃይሎች መሰማራታቸውን ነው።
በያዝነው ሳምንት አርብ እንዲሁ በደረሰ ሌላ ጥቃት 14 ሰዎች በአንዲት መንደር ውስጥ ተገድለዋል።
ጥቃቱ የደረሰው ታዳርያት በምትባል መንደር ሲሆን አሁን ጥቃቱ ከተፈፀመባት ሶልሃን በ150 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።
በባለፈው ወር እንዲሁ በምስራቅ ቡርኪናፋሶ 30 ሰዎች ተገድለዋል።
አገሪቷ ከፍተኛ የሆነ የፀጥታና ደህንንነት ችግር የገጠማት ሲሆን ልክ እንደ ሌሎች ጎረቤቶቿ አገራትም የታጠቁ ቡድኖች መንደሮችን ከበው የንፁኃንን ዜጎች ይቀጥፋሉ እንዲሁም ሰዎችን ይጠልፋሉ።
ይህንንም ለመግታት በሚል መንግሥት ከፍተኛ የሆነ ወታደራዊ ዘመቻ በግንቦት ወር ቢጀምርም የንፁኃንን ዜጎች ህይወት ከመቀጠፍ አልታደጉትም። በባለፉት ሁለት አመታት በደረሱ ጥቃቶች ከሚሊዮን በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል።












