የአሜሪካ መንግሥት 'ከዚህ በኋላ ከጋዜጠኞች በድብቅ መረጃ አልወስድም' ብሏል

የአሜሪካ ፍትህ ሚኒስቴር ቢሮ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካ ፍትህ ሚኒስቴር ከዚህ በፊት ለረዥም ጊዜያት ተግባር ላይ ይውል የነበረውን ከጋዜጠኞች ላይ በድብቅ መረጃ የመውሰድ ሥራን እንደሚያቆም አስታወቀ።

አሜሪካ ሪፐብሊካንም ይሁን ዴሞክራት ገዥ በነበራት ጊዜ ይህ ተግባር የተለመደ ነበር።

ሪፖርተሮች ድብቅ መረጃን በተለመከተ ምርመራ በሚደረግላቸው ጊዜ መረጃቸው እንዲቀመጥ ይደረግ ነበር።

የጆ ባይደን አስተዳደር ግን ይህ ጉዳይ በተለይ በያዝነው ዓመት ከፍተኛ ትችት እየገጠመው ስለመጣ እንዲቀር ወስኗል።

ፕሬዝደንት ባይደን ይህን ልማድ 'ስህተት' ሲሉ ገልፀውታል።

በሪፐንሊካኑ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ዘመን የፍትህ ሚኒስቴር ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ከሚሠሩ ሪፖርተሮች መረጃ መውሰዱን የሚያሳዩ መረጃዎች ከሰሞኑ መውጣት ጀምረዋል።

ከእነዚህ የጋዜጠኞቻቸው መረጃ ከተወሰደ መገናኛ ብዙሃን መካከል ሲኤንኤን እና ዋሺንግተን ፖስት ይገኙበታል።

ይህ ድርጊት ጆ ባይደን ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ባሉት ጥቂት ቀናትም እንደቀጠለ መረጃዎች አመላክተዋል።

የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ አስተዳዳሪዎች የአራት ሪፖርተሮቻቸውን መረጃ መወሰድ ይፋ ከማድረግ ታግደዋል።

አሁን የፍትህ ሚኒስቴር በተለያዩ ፕሬዝደንቶች አገልግሎት ላይ ይውል የነበረውን ይህን ልማድ ከዚህ በኋላ ጥቅም ላይ አይውልም ብሏል።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አንተኒ ኮሊ የፍትህ መሥሪያ ቤቱ ከሁሉም ወገን ያለውን ቅሬታ ካደመጠ በኋላ ከዚህ ውሳኔ ላይ ደርሷል ብለዋል።

ቃል አቀባዩ አክለው ይህ የሆነው ከፕሬዝደንቱ በመጣ ትዕዛዝ መሠረት መሆኑን ጠቁመዋል።

ሲኤንኤን እንደሚለው ግን ቅዳሜ ዕለት ይፋ የሆነው እርምጃን የተመለከተ ይፋ መመሪያ አልወጣም።

ይህ ማለት አሠራሩ በሌላ መሥሪያ ቤት በኩል ሊቀጥል እንደሚችል ጥርጣሬ አለ ሲል ሲኤንኤን ዘግቧል።