የጣልያኗ ደሴት አሸዋ በሰረቁ ቱሪስቶች ላይ የ3 ሺህ ዩሮ ቅጣት ጣለች

የሳርዲና ደሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የጣልያኗ ደሴት ሳርዲና የባህር ዳርቻ አሸዋ በሚሰርቁ ቱሪስቶች በመማረሯ ቅጣት መጣሏን አስታውቃለች።

ከደሴቲቱ አሸዋና ዛጎሎችን የወሰዱ በርካታ ቱሪስቶች እያንዳንዳቸው 3 ሺህ ዩሮ ቅጣት እንዲከፍሉ መወሰኑንም የአገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል።

ባለስልጣናቱ በያዝነው ሳምንት ቅዳሜ 100 ኪሎ ግራም የሚሆን አሸዋ 41 ቱሪስቶች በተለያያ ጊዜ መስረቃቸውን ሪፖርት አድርገዋል።

የሳርዲና ነጭ አሸዋ እንደ ብርቅዬ የሚታይ ሲሆን አሸዋውንም አፍሶ መውሰድ በፍፁም የተከለከለ ነው።

የሳርዲናን አሸዋ፣ ድንጋይና ዛጎሎች መሸጥ ህገ ወጥ የተደረገው ከአራት አመታት በፊት ነበር።

ምንም እንኳን ቅጣቱ ከበድ ያለ ቢመስልም ለአመታት ያህል የደሴቲቱ ነዋሪዎች አንጡራ የተፈጥሮ ኃብታችን እየተዘረፈ ነው ሲሉ በርካታ ጊዜ እሮሮዋቸውን ያሰሙ ነበር።

በርካታ ቱሪስቶች በተለይም ከአውሮፓ የሚመጡት አሸዋውን በጠርሙስ በመውሰድ በበይነ መረብ አማካኝነት በጨረታ ይሸጡታል።

ከዚህም ጋር ተያየይዞ የተቀናጀ ምርመራ የተከፈተ ሲሆን በዚህም የአየር መንገድ ሰራተኞችና ጦሩ በመታበበር አየር ማረፊያዎችና በድንበር ኬላዎች ላይ ጠበቅ ያለ ፍተሻ እያደረጉ ይገኛሉ።

እንዲሁም በተለያዩ ድረገፆች ላይ የሚደረጉ ህገወጥ ሽያጮችም ላይ ክትትል እየተደረገ መሆኑ ተዘግቧል።

በዚህም ሳምንት በጠርሙስ ውስጥ አሸዋ ይዘው ሊወጡ የነበሩ ቱሪስቶች በአየር መንገድ ላይ በነበረ ፍተሻ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል ተብሏል።

ፖሊስ በቅርብ እንዳስታወቀው ከሜዲትራንያን ደሴቶች የተገኙ አሸዋዎችን በህገ ወጥ መንገድ ለመሸጥ የሚደረጉ የኢንተርኔት ማስታወቂያዎችን አግኝቻለሁ ብሏል። ለአሸዋዎቹ የተተመነውም ዋጋ በጣም ከፍተኛ ነው ተብሏል።

ከካርዲና ተወስዶ በአየር ማረፊያው በቁጥጥር ስር የዋለው አሸዋ

የፎቶው ባለመብት, Sardegna rubata e depredata

አሸዋውን ዘርፈዋል ተብለው ቅጣት እንዲከፍሉ የተባሉትም ቱሪስቶች ጉዳይ በደሴቲቱ አገዛዝ ህግ መስረት ተፈፃሚ ይሆናል ተብሏል።

ፖሊስ እንዳስታወቀውም በዚህ አመት ብቻ 13 ሺህ ዪሮ ቅጣት መሰብሰብ እንደቻሉና አሸዋውም ከተወሰደበት ቦታ መመለስ እንደተቻለም ተጎልጿል።