የዓለም አቀፍ የምግብ ዋጋ በፍጥነት እየናረ መሆኑን ተመድ አስታወቀ

ሩዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ባለፉት አሥር ዓመታት ባልታየ ሁኔታ ወርሃዊ የምግብ ዋጋ በፍጥነት እየናረ መምጣቱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ።

ዓለም አቀፍ የምግብ ገበያን የዳሰሰው ድርጅቱ እንዳለው፤ የምግብ ዋጋ ለ12 ተከታታይ ወራት ጨምሯል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለው የምርት መስተጓጎል፣ የሠራተኛ እጥረትና የትራንስፖርት መቋረጥ አምራቾች ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።

የምግብ ዋጋ አሁንም ካለው በላይ እንደሚጨምር ተሰግቷል። ለምግብ የሚወጣው ወጪ መናሩ የዓለም ምጣኔ ሀብት እንዲያገገም የሚደረገውን ጥረት እንዳያሰናክልም ተፈርቷል።

የተባበሩት ድርጅት የምግብና ግብርና ተቋም (ፋኦ) የሥጋ፣ የስኳር፣ የወተት ተዋጽኦ፣ የቅባት እህሎችና ጥራጥሬዎችን ዋጋ ይዳስሳል።

በተሠራው ጥናት መሠረት አጠቃላይ የምግብ ዋጋ እአአ በጥቅምት 2011 ከተመዘገበው አሁን ጨምሯል።

የምግብ ዋጋ ለምን ጨመረ?

የምግብ ዋጋ ግንቦት ላይ 39.7% ጨምሯል። ይህም ከጥቅምት 2010 ወዲህ የተመዘገበ ከፍተኛ ወርሀዊ ዋጋ ነው።

ድርጅቱ የዳሰሳቸው አምስት የምግብ አይነቶች ባጠቃላይ ጭማሪ አሳይተዋል። በዚህ መሠረት የዓለም የምግብ ዋጋ ከመስከረም 2011 ወዲህ ባልታየ ሁኔታ ነው የናረው።

ለጭማሬው ምክንያት ከተባሉ አንዱ በአገራት ያለው የፍላጎት ለውጥ ነው። የምርት መጠን መቀነስም ተጠቅሷል።

በወረርሽኙ ሳቢያ እንቅስቃሴ መገታቱ ምርት እንዲቀንስና የምግብ ዋጋ እንዲጨምር አድርጓል።

ተንታኞች እንደሚሉት ፍላጎት ጨምሮ አቅርቦት ሲቀንስ ከፍተኛ የዋጋ መናር ይከሰታል። አገራት የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት የጣሉት የእንቅስቃሴ ገደብ ሲነሳ ምጣኔ ሀብታቸው መናጋቱም አይቀሬ ነው።

በሌላ በኩል ቶሎ የሚያገግሙ ዘርፎች አሉ።

በፋኦ ትንበያ መሠረት፤ የእህል ምርት በዚህ ዓመት ጨምሮ የዋጋ መናርን ሊያረግብ ይችላል።

የዋጋ ንረት ምንድን ነው?

የዋጋ ንረት የሚባለው ለምርትና አገልግሎት የሚከፈለው ገንዘብ ሲጨምር ነው።

የቤት ኪራይና የመጓጓዣ ወጪን ጨምሮ የዋጋ ንረት ተጽዕኖ የማያሳድርበት ዘርፍ አይኖርም።

አንድ ሰው ጤናማ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ እንዳይኖረው የዋጋ ንረት ያግዳል። መግዛት የሚቻለውን መገልገያ አይነትና መጠንም ይወስናል።

የዋጋ ንረት የተጋነነ በማይሆንባቸው አጋጣሚዎች ሸማቾች በአፋጣኝ ምርት እንዲገዙና ድርጅቶችም የሠራተኞቻቸውን ደመወዝ እንዲጨምሩ ያደርጋል። ይህም ለምጣኔ ሀብት እድገት አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

ያልተጠበቀና የተጋነነ የዋጋ ንረት ደግሞ በተቃራኒው ኪስ ይጎዳል።

የብዙ አገራት ብሔራዊ ባንኮች ከ2% እስከ 2.5% የዋጋ ንረት ሊከሰት እንደሚችል ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።