ግዙፉን ስጋ አምራች ያጠቃው የሩስያው መረጃ መዝባሪ ነው ሲል ኤፍቢአይ ወቀሰ

የዓለማች ግዙፉ ስጋ አቅራቢ ድርጅት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የሩስያ የሳይበር ጥቃት ቡድን የዓለማች ግዙፉ ስጋ አቅራቢ ድርጅት ላይ ጥቃት አድርሷል ሲል ኤፍቢአይ ወቅሷል።

የአሜሪካው የፌዴራል ወንጀል ምርመራ ድርጅት ኤፍቢአይ የሩስያው ሳይበር አጥቂ ቡድን ይዞ ለፍርድ ለማቅረብ እየሠራ መሀኑን ይፋ አድርጓል።

ጄቢኤስ የተሰኘው ስጋ አቅራቢ ድርጅት ባፈለው ቅዳሜና እሁድ በደረሰበት ጥቃት ምክንያቱ በአሜሪካ፣ ካናዳና አውስትራሊያ የሚገኙ የተወሰኑ ቅርንጫፎቹ ተዘግተው ነበር።

ሬቪል አሊያም ደግሞ ሶዲኖኮቢ በመባል የሚታወቀው ቡድን በዓለማችን ካሉ ግዙፍ የበይነ መረብ መረጃ መዝባሪዎች መካከል አንዱ ነው።

"ስጋ አቅራቢው ድርጅት ላይ የደረሰው ጥቃት ከሬቪል ጋር ተያያዥነት ያለው ነው። እነዚህን ሰዎች ይዞ ለፍርድ ለማቅረብ እየተጋን ነው" ይላል ኤፍቢአይ የለቀቀው መግለጫ።

ዋይት ሃውስ ረቡዕ ዕለት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ከሩስያ አቻቸው ቭላዲሚር ፑቲን ጋር ሲገናኙ የሳይበር ጥቃት ጉዳይን እንደሚያነሱ አስታውቋል።

"ኃላፊነት የሚሰማቸው ሃገራት የሳይበር ጥቃትን አይደግፉም" ብለዋል ፕሬስ ሴክሬታሪዋ ጄን ሳኪ።

ፑቲንና ባይደን ከሁለት ሳምንታት በኋላ ይገናኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ጄቢኤስ አሜሪካ ውስጥ አምስት ግዙፍ ስጋ ማምረቻዎች አሉት። በጥቃቱ ምክንያት ስራ ያቆመው ድርጅት ሐሙስ ዕለት እንቅስቃሴ እጀምራለሁ ብሏል።

ጥቃት እንደደረሰበት እሁድ ይፋ ያደረገው ኩባንያው ለመረጃ መዝባሪዎቹ ገንዘብ ይክፈል አይክፈል ያለው ነገር የለም።

ራንሰምዌር የሳይበር ጥቃት ዓይነት ነው። መረጃ ጠላፊዎች ወደ ድርጅቶች ኮምፒውተር ሰርስረው ይገቡና መረጃዎችን ይዘጋሉ አሊያም ሰዎች ኮምፒውተሮቻቸውን እንዳይጠቀሙ ያደርጋሉ።

ጠላፊዎቹ ብዙ ጊዜ ይህን የሚያደርጉት ገንዘብ ፍለጋ ስለሆን እስኪከፈላቸው ድረስ ኮምፒውተሮች እንደተቆለፉ ይቆያሉ።

በፈረንጆቹ 1953 ብራዚል ውስጥ የተቋቋመው ጄቢኤስ በ15 ሃገራት 150 ስጋ ማምረቻዎች አሉት።

በዓለም አቀፍ ደረጃ 150 ሺህ ሠራተኞች የሚያስተዳድረው ግዙፉ ድርጅት ለአሜሪካ አንድ ሶስተኛ የበሬ ስጋ፤ እንዲሁም አንድ አምስተኛ የአሳማ ስጋ ያቀርባል።

ሬቪል የተሰኘው የበይነ መረብ መረጃ መዝባሪ ቡድን ከዚህ ስጋ አምራች አልፎ ቴክሳስ ውስጥ ያሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን አጥቅቶ ነበር።

ባለፈው ወር በደቡብ ምስራቅ አሜሪካ ነዳጅ በማቅረብ የሚታወቀው ድርጅት ከሩስያ ጋር ግንኙነት ባለው ሌላ መረጃ መዝባሪ ቡድን ጥቃት ደርሶበት ነበር።

ነዳጅ አቅራቢው ድርጅት ለመረጃ መዝባሪው ቡድን 4.4 ሚሊዮን ዶላር እንደከፈለ አስታውቋል።

የአሜሪካ መንግሥት ድርጅቶች ለመረጃ መዝባሪዎች ድንቡሎ እንዳይከፍሉ በተደጋጋሚ ያስጠነቅቃል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ክፍያው መዝባሪዎችን ያበረታታል የሚል ነው።