ግብጽ ከየትኞቹ የአባይ ተፋሰስ አገራት ጋር ወታደራዊ ስምምነት ተፈራረመች?

የፎቶው ባለመብት, Kenya Defence Forces
ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለው ግዙፉ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከአባይ ወንዝ የምታገኘውን የውሃ መጠን ይቀንስብኛል በማለት ስጋቷን ስትገልጽ የቆየችው ግብጽ ጥቅሟን ለማስጠብቅ የተለያዩ ጥረቶችን ስታደርግ ቆይታለች።
ለዓመታት ሲካሄድ የቆየውን የመጨረሻ ስምምነት ሳይደረስበት በእንጥልጥል የቆየው ግድቡን የሚመለከተው ድርድር ሳይቋጭ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ለማካሄድ ተቃርባለች።
በዚህ ጊዜ ሁሉ ግብጽ የአባይ ተፋሰስ አገራትን ከጎኗ ለማሰለፍ የተለያዩ ጥረቶችን ስታደርግ ቆይታለች።
ከዚህ አንጻር ግብጽ በኢትዮጵያ ዙሪያ ከሚገኙ አገራትና ከአባይ ተፋሰስ አገራት ጋር በተለያዩ መስኮች ያላትን ትብብር ለማጠናከርና አዳዲስ ስምምነቶች ላይ ለመድረስ በከፍተኛ ባለሥልጣናቷ የሚመሩ ልዑካንን ስታሰማራ ቆይታለች።
ግብጽ ከአገራቱ ጋር ካደረገቻቸው ስምምነቶች መካከል የወታደራዊ ትብብር ስምምነቶች ተጠቃሾች ናቸው። በዚህም በተለይ ከአባይ ተፋሰስ አገራት ጋር በተለያየ ደረጃ የሚገለጽ ወታደራዊ ስምምነቶችን አድርጋለች።
ለመሆኑ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ዙሪያ ውዝግቡት ውስጥ በሚገኙበት ወቅት ግብጽ ከየትኞቹ የተፋሰሱ አገራት ጋር ወታደራዊ ስምምነት ተፈራረመች?

ሱዳን
ባለፈው መጋቢት ወር የግብጽ ጦር ዋና አዛዥ ሌፍተናንት ጄኔራል ሞሐመድ ፋሪድ ወደ ካርቱም አቅንተው አገራቸውን በመወከል ከሱዳን ጋር ወታደራዊ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ግብጽ "ከሱዳን ጋር በሁሉም መስኮች በተለይም በወታደራዊ እና በደኅንነት መስኮች ግንኙነቷን ለማጠናከር እንደምትፈልግ" አመልክተው፤ ሱዳን እና ግብጽ የጋራ ፈተናዎች እንዲሁም የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት እንደሚገጥማቸው ፋሪድ በወቅቱ አስታውቀዋል።
በተጨማሪም ከሱዳን ጋር ከወታደራዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን በሙሉ ለማሟላት ካይሮ ዝግጁ መሆኗን በመግለጽ የወታደራዊ ትብብሩን ደረጃም "ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታውቅ" ብለውታል።
የሱዳኑ አቻቸው ሌፍተናት ጄኔራል ሞሐመድ ኦትማን አል ሁሴን "የስምምነቱ ዓላማ የሁለቱ አገራት ብሔራዊ ደኅንነትን ማስከበር እና በልምድ እና በዕውቀት የደረጀ ኃይል ለመገንባት ነው" በማለት፤ ሁሴን በአስቸጋሪ ጊዜያት ግብጽ ከሱዳን ጎን በመቆየቷ አመስግነዋል።
ግብጽ እና ሱዳን በቅርቡ "የአባይ ንስሮች 1" እና "የአባይ ንስሮች 2" የተባሉ የጋራ ወታደራዊ ልምምዶችን አካሂደዋል። ከሰሞኑም የስድስት ቀን የጋራ ወታደራዊ ልምምድ አካሂደው ማጠናቀቃቸውን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ኬንያ
ኬንያ ከግብጽ ጋር በመከላከያ ትብብር ላይ የቴክኒክ ስምምነት ከቀናት በፊት ነበር የደረሰችው።
የኬንያ መከላከያ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ የመከላከያ ሚኒስትሯ ሞኒካ ጁማ እና የግብጹ ዋና አዛዥ ሌፍተናንት ጄኔራል ሞሐመድ ፋሪድ ሄጋዚ ተገናኝተው ስምምነቱን መፈራረማቸውን አመልክቷል።
ሚኒስትሩ "በሁለትዮሽ የመከላከያ ውይይት ወቅት አገራቱ በጋራ ተጠቃሚነት ጉዳዮች ላይ አጋርነታቸውን የበለጠ ለማሳደግ የሚያስችል የመከላከያ የቴክኒክ ስምምነት ተፈራረሙ" ብሏል።
ስምምነቱ ምን ምን ጉዳዮችን እንደሚይዝ ግን ተጨማሪ መረጃ ይፋ አልተደረገም።
ጂቡቲ
ግብጽ እና ኬንያ ከስምምነት ከደረሱ ከቀናት በኋላ ጂቡቲ የደረሱት ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል-ሲሲ፤ ጂቡቲ ነጻነቷን ካወጀች በኋላ አገሪቱን የጎበኙ የመጀመሪያው የግብጽ ፕሬዝዳንት ሆነዋል።
አል-ሲሲ እና የጂቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጉሌህ የሕዳሴው ግድብ አካባቢያዊ መረጋጋትን ለማስጠበቅ እና የሁሉንም ወገኖች ጥቅም ለማስከበር የሚያስችል ፍትሃዊ ስምምነት ላይ እንዲደረስ እንደሚፈልጉ መመካከራቸው ተገልጿል።
አል-ሲሲ ከጉሌህ ጋር ያደረጉትን ውይይት "ገንቢና ፍሬያማ" ሲሉ ያወደሱ ሲሆን ሁለቱም መሪዎች የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ ትብብርን ማሻሻል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን አብራርተዋል።
ሁለቱም መሪዎች በአፍሪካ ቀንድ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ስላላቸው "ስትራቴጂያዊ አጋርነት" አፅንኦት ሰጥተዋል።
ከቀናት በፊትም ሁለት የግብጽ ወታደራዊ አውሮፕላኖች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የህክምና እርዳታዎችን ጭነው ጂቡቲ ደርሰዋልም ተብሏል።
ጂቡቲ የአባይ ተፋሰስ አገር ባትሆንም ከፍተኛ መጠን ያለው የኢትዮጵያ ወጪና ገቢ ንግድና ምርቶች የሚተላለፉባት ቁልፍ አገር መሆኗ ይታወቃል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዲሞክራቲክ ኮንጎ
ግብጽ ከተለያዩ የናይል ተፋሰስ አገራት ጋር ካደረገችው ወታደራዊ ስምምነት በተቃራኒ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር በኢንቨስትመንት ላይ ያተኮረ ስምምነት ደርሳለች።
የኮንጎ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ትሺከዲ የካቲት 2 ቀን የካይሮ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት የግብጽ እና የኮንጎ መንግሥታት የመሠረተ ልማት፣ የኃይል እና የመጠጥ ውሃን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ስምምነቶችን ተፈራርመዋል።
የኮንጎ መንግሥትም በማዕከላዊ ኮንጎ ውስጥ በሳንቡሩ ጠቅላይ ግዛት በሉቢ ወንዝ ላይ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ማዕከል ለመገንባት ከግብጽ ኩባንያዎች ጋር ከስምምነት ደርሷል።
ፌሊክስ ትሺከዲ የግብጽ ኩባንያዎች በኮንጎ በተለይም በግንባታ፣ በኢነርጂ እና በመሠረተ ልማት ዘርፎች የሚጫወቱትን ሚና አወድሰዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከግብጹ አቻቸው ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር የካቲት 2 ቀን ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት በኮንጎ የግብጽ ኢንቨስትመንቶችን እና የንግድ ልውውጥን ለማሳደግ ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡
ሩዋንዳ
የግብጽ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ሌፍተናንት ጄኔራል ሞሐመድ ፋሪድ እአአ ከግንቦት 27 እስከ 29 ድረስ በሩዋንዳ ጉብኝት አድርገው ነበር።
ጉብኝቱን ተከትሎም ግንቦት 29 በተሰጠው መግለጫ ሌፍተናል ጄኔራል ሞሐመድ ፋሪድ እና የልዑካን ቡድናቸው በሩዋንዳ መከላከያ ሠራዊት ዋና መሥሪያ ቤት ከመከላከያ አዛዡ ጄኔራል ጄን ቦኮ ካዙራ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸው ተነግሯል።
በውይይቶቹ ቀደም ሲል የነበሩትን ወታደራዊ ትብብሮች በማጎልበት ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ተገልጾ ነበር።
ሩዋንዳ እና ግብጽ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እና በኢኮኖሚ እና በንግድ፣ እንዲሁም በመከላከያ እና በደኅንነት የጋራ ጥቅሞችን ለማጎልበት በሚያስችሉ መንገዶች ላይ ሲሠሩ ቆይተዋል ተብሏል።
ሩዋንዳ ከዚህ ቀደም ተማሪዎቿን ለወታደራዊ ትምህርት ወደ ግብጽ ስትልክ ቆይታለች።
ደቡብ ሱዳን
ግብጽ ከደቡብ ሱዳን ጋር በወታደራዊ መስክ በቅርቡ ስለደረሰችው ስምምነት ምንም መረጃ ማግኘት አልተቻለም።
ይልቁንም ደቡብ ሱዳን ከአንድ ዓመት በፊት በድንበሯ ውስጥ ግብጽ ወታደራዊ ካምፕ ለማቋቋም ያቀረበችውን ጥያቄ አጸደቀች መባሉን አስተባብላለች።
የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴሩ ለአናዱሉ የዜና ወኪል በወቅቱ "እንደዚህ ዓይነት ነገር የለም" ብለው ነበር።
"በደቡብ ሱዳን ግዛት ውስጥ ለግብጽ ወታደራዊ ሥፍራ ቅንጣት መሬት ለመመደብ ከስምምነት አልተደረሰም።"
ግብጽ በፓጋክ ወታደራዊ ካምፕ ለመገንባት ያቀረበችውን ጥያቄ የደቡብ ሱዳን መንግሥት ስለመስማማቱ በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ በስፋት ተነግሮ የነበረ ቢሆንም ደቡብ ሱዳን ጉዳዩን አስተባብላለች።
ፓጋክ በደቡብ ሱዳን የላይኛው ናይል ግዛት ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ የሚገኝ ከተማ ነው።
ቡሩንዲ
የግብጽ እና የቡሩንዲ መከላከያ ኃላፊዎች ከወራት በፊት ካይሮ ተገናኝተው በስልጠና እና የጋራ ልምምድ መስኮች ትብብርን የሚያካትት ወታደራዊ ስምምነት ተፈራርመዋል።
የትብብር ስምምነቱ ሁለቱ አገራት ባለሙያዎችን ለመለዋወጥ የሚያስችላቸው ነው ተብሏል። ይህም በሁለቱ አገራት ሠራዊት መካከል የጋራ መግባባት በሚፈጥሩ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን መተባበር የሚያንፀባርቅ መሆኑን የግብጽ ጦር ኃይል ቃል አቀባይ ማስታወቃቸውን ኢጅፕት ቱዴይ ዘግቦ ነበር።
የቡሩንዲ ጦር ኃይሎች አዛዥ ፕራይም ኒዮንጋቦ በግብጽ ይፋዊ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን ስለሁለትዮሽ ትብብር ከግብጽ ጦር ዋና አዛዥ ሞሐመድ ፋሪድ ጋር ተገናኝተው መክረዋል።
ፋሪድ እና ኒዮንጋቦ በሁለቱ አገራት መካከል በተለያዩ መስኮች ወታደራዊ ትብብርን ስለማሳደግ መወያየታቸው በወቅቱ ተነግሯል።
ታንዛንያ
ታንዛንያ እና ግብጽ በወታደራዊ መስክ ያላቸውን ትብብር ለማሳደግ የሚያግዝ ውይይት ያደረጉት ከዓመት በፊት ነበር።
የታንዛኒያ የመከላከያ እና ብሔራዊ አገልግሎት ሚኒስትር ሁሴን ምዊኒ አገራቸው ከግብጽ ጋር በተለያዩ መስኮች ግንኙነቷን ለማጠናከር ፍላጎት አንዳላት በወቅቱ ገልጸው ነበር።
ሚንስትሩ ከግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል-ሲሲ ጋር የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር ሞሐመድ ዛኪ እና በግብጽ የታንዛኒያ አምባሳደር በተገኙበት ውይይት ማድረጋቸው ተዘግቧል።
ምዊኒ በሁለቱ አገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች መካከል በተለይም ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ትብበራቸውን ለማሳደግ ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል።
በተጨማሪም ታንዛኒያ የግብጽ የታደራዊ ማምረቻ ኩባንያዎችን የቴክኖሎጂ እና የሰው አቅም የመጠቀም ፍላጎት እንዳላት አመልክተዋል።
ፕሬዚዳንት ሲሲ በበኩላቸው ከታንዛኒያ ጋር የተደረገውን ወታደራዊ ትብብርን በደስታ እንደተቀበሉ በወቅቱ ገልጸዋል።
ኡጋንዳ
ግብጽ እና ኡጋንዳ በወታደራዊ መረጃ ማጋራት ዙሪያ የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረሙት ከሁለት ወራት በፊት ነው።
በኡጋንዳ ወታደራዊ የደኅንንት ኃላፊ አቤል ካንዲሆ እና በግብጹ ወታደራዊ ደኅንነት ጄኔራል ሳሜህ ሳበር ኤል-ደግዊ የተፈረመው ስምምነት ሁለቱ አገራት "ሽብርተኝነትን መዋጋትን" ጨምሮ መረጃዎችን መለዋወጥን ያካትታል ተብሏል።
ሳሜህ ሳበር ኤል-ደግዊ በወቅቱ "ኡጋንዳ እና ግብጽ አባይን የሚጋሩ በመሆናቸው በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ትብብር የማይቀር ነው ምክንያቱም ኡጋንዳውያንን የሚነካው ነገር በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ግብጽን ይነካል" ብለው ነበር።












