የግብፅ እና ሱዳን መገናኛ ብዙሃንን ያነጋገረው የጠ/ሚ ዐቢይ ንግግር

የፎቶው ባለመብት, @AbiyAhmedAli
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሚቀጥለው ዓመት ኢትዮጵያ ቢያንስ 100 መካከለኛና አነስተኛ ግድቦችን መገንባት ትጀምራለች ማለታቸውን ተከትሎ የግብፅ እና የሱዳን መገናኛ ብዙሃን በጉዳዩ ሰፊ ዘገባ ሠርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሚቀጥለው ዓመት ኢትዮጵያ ቢያንስ 100 መካከለኛና አነስተኛ ግድቦችን የመገንባት እቅድ እንዳላት የተናገሩት በኢትዮ-ጂቡቲ የምዕራፍ አንድ አዳማ-አዋሽ የመንገድ ግንባታ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ላይ ነው።
"ቢያንስ ከ100 በላይ ግድቦችን የመስራት እቅድ አለን። ውሃ ላይ አበክረን ካልሠራን፣ ውሃን እንደ ትልቅ ሀብትና እንደ ልማት መግቢያ በር አድርገን ካልወሰድን አጠቃላይ የምናስበውን ብልጽግና ማረጋገጥ ስለሚያስቸግር የመንግሥት ትኩረት ትናንሽና መካከለኛ ግድቦች በመሥራት ውሃን ማቆየት ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።
የግድቦች ግንባታ ዓላማ በዓመት ሦስት ጊዜ ማምረት እንዲቻል መሆኑን ጠቅላይ ሚንስትሩ አስረድተዋል። ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው በትክክል በየትኞቹ አካባቢዎችና የውሃ አካላት ላይ ግድቦቹ እንደሚገነቡ ያሉት ነገር የለም።
ይህን ተከትሎ በርካታ የግብፅ እና የመካከለኛው ምሥራቅ መገናኛ ብዙሃን በጉዳዩ ላይ ዘገባ ሰርተዋል።
መገናኛ ብዙሃኑ ምን አሉ?
'አህራም ኦንላይን' ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ኢትዮጵያ ከ100 በላይ ግድቦችን የመገንባት እቅድ አላት ማለታቸውን ግብፅ 'ለዓለም አቀፍ ሕግጋትን ቁብ አለመስጠት ነው' ብላለች ሲል ዘግቧል።
ቃል አቀባዩ፤ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ንግግር ድንበር ተሻጋሪ የውሃ አካላት ሕጎችን የተላለፈ እና የታችኛው ተፋሰስ አገራት መብትን ያላከበረ ነው ስለማለታቸው አሃራም ኦላይን አስነብቧል።
በተመሳሳይ 'አረብ ኒውስ' የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ አህመድ ሃፌዝ የጠቅላይ ሚንስትሩ ንግግር ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ ምክንያታዊ ፍላጎት እንደሌላት የሚያሳይ ነው በማለት አጣጥለዋል።
'ኢጂፕት ኢንዲፐንደንት' መረጃውን ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳገኘው በመጥቀስ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገራቸው ላይ ለሚደርሱ ማንኛውም አይነት ጫናዎች መልስ የምትሰጠውና ጫናዎቹን መቋቋም የምትችለው ግድቦችን በመገንባት ነው ስለማለታቸው ዘግቧል።
'ኢጂፕት ኢንዲፐንደንት'፤ ኢትዮጵያ እየገነባች ያላችው የሕዳሴ ግድብ የውሃ ድርሻዬን ያሳንስብኛል በማለት ግብፅ እንደምትሰጋ አስታውሷል።
'ሱዳን ትሪቢዩን' በበኩሉ ጠቅላይ ሚንስትሩ በቀጣይ በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ከ100 በላይ ግድቦችን የመገንባት እቅድ አላት ማለታቸውን ከዘገበ በኋላ፤ በትግራዩ ግጭት ኢትዮጵያ ከምዕራባውያኑ አገራት ከፍተኛ ጫና እየደረሰባት ይገኛል ብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንገድ ግንባታ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር "መንግሥት ባለፉት ዓመታት በጤና፣ በትምህርት፣ በመንገድ ግንባታ ሰፋፊ ፕሮጀክቶችን እንዳሠራ ሁሉ የሚቀጥለው ዓመት ዋናው እቅዳችን ትናንሽና መካከለኛ ግድቦች በየክልሉ ማስፋፋት ነው" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, @AbiyAhmedAli
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ የኢትዮጵያ-ጅቡቲ የትራንስፖርት ኮሪደር አካል የሆነውን የአዳማ-አዋሽ ምዕራፍ አንድ 60 ኪሎ ሜትር የፍጥነት መንገድ ግንባታ በይፋ ሲያስጀምሩ፤ ኢትዮጵያን በአራቱም አቅጣጫ ከሚገኙ ጎረቤት አገራት መንገድን ጨምሮ በሁሉም መስክ ለማስተሳሰር በትኩረት እየተሠራ ስለመሆኑ ፕሮጀክቱ ጉልህ ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ "ቀን ከሌት እየሠራ የአባቱን ሀብት የሚያበዛ ወጣት ትፈልጋለች" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ወቅቱ "የልማት ስኬትን በማረጋገጥ ወደ ለውጥ የምንሸጋገርበት በመሆኑ እጅ ለእጅ ተያይዘን ለሥራ እንነሳ" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የመንገዱ የግንባታ ወጪ ከአፍሪካ ልማት ባንክ በብድር በተገኘ 6.6 ቢሊዮን ብር የተጀመረ ሲሆን ሁለተኛው ምዕራፍ (70 ኪሎ ሜትር) ጨረታ ወጥቶ በሂደት ላይ መሆኑ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ከ10 ዓመታት በፊት የታላቁ ሕዳሴ ግድብን መገንባት ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ በተለይ ደግሞ ከግብፅ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች መግባባት ላይ መድረስ ሳትችል ቀርታለች።

ስለ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አንዳንድ እውነታዎች
ግብፅ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሐሳብ ከቀረበበት ጊዜ ጀምሮ ሕልውናዋ ላይ ከፍተኛ ስጋት የሚፈጥር መሆኑን በመግለጽ የግንባታው እና ውሃ ሙሌቱ የግብፅ ይሁንታ ላይ ተመስርቶ መሆን አለበት ስትል ቆይታለች።
ኢትዮጵያ ደግሞ ከአባይ ወንዝ 80 በመቶ ድርሻ እንዳላት በመግለጽ በሚሊዮኖች ለሚቆጠረው ሕዝቧ የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ ዓላማዬ ነው ትላለች።
ባለፈው ዓመት ሐምሌ ላይ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ደረጃ የዉሃ ሙሌት መጀመሩን የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ ገልጸው ነበር። በያዝነው ዓመትም የክረምቱን ወር ተከትሎ የሙሌት ሥራው እንደሚቀጥል ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት የሕዳሴ ግድቡ ግንባታ 80 በመቶ መድርሱን ስትገልጽ ግብፅ በበኩሏ የግድቡ የቀጣዩ ክረምት ሙሊት የጎላ ተጽዕኖ አያደርስብኝም ብላ ነበር።
የግድቡ ተደራዳሪዎች ቴክኒክ ቡድን አባል በለጠ ብርሃኑ (ዶ/ር) ለብሔራዊ ጣቢያው በሰጡት አስተያየት፤ የግድቡ የሲቪል ግንባታ 91.8፣ የኤሌክትሮ መካኒካል ግንባታው 54.5 በመቶ እንዲሁም የሃይድሮሊክ ስትራክቸር ሥራው ደግሞ 55.2 በመቶ መድረሱን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የሕዳሴ ግድቡን የውሃ ሙሌት እጀምራለሁ ባለው ጊዜ መሠረት ባለፈው ዓመት ሙሌቱን ማከናወን ጀምሯል። በዚህም መሠረት ግድቡ 4.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ድረስ ውሃ እንደያዘ ይገመታል።
ግንባታው ሲጠናቀቅ 1,800 ሜትር ርዝመት እና ከ145 እስከ 170 ሜትር የመጨረሻ ከፍታ የሚኖረው ሲሆን አጠቃላይ የሚይዘው የውሃ መጠንም 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር እንደሆነ ተገልጿል።
የሕዳሴ ግድቡ በመጪው ክረምት ውሃ ከመያዝ በተጨማሪ በተየዘው ዓመት መገበደጃ ላይ ቅድመ ኃይል እንደሚያመነጭም የግድቡ ተደራዳሪዎች ቴክኒክ ቡድን አባል የሆኑት በለጠ ብርሃኑ (ዶ/ር) ገልጸዋል።













