ሽብርተኛ በተባሉት ቡድኖች አባላት ንብረትና ገንዘብ ላይ እገዳ ተጣለ

የደህንነት ተቋማት

የፎቶው ባለመብት, Federal Police, END, NISS, INSA

የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሪቱ ምክር ቤት ሽብርተኛ ተብለው የተሰየሙ ቡድኖች አባላትና ደጋፊዎች ናቸው ባላቸው ላይ የንብረት እገዳ መጣሉን አስታወቀ።

ከተለያዩ የአገሪቱ የጸጥታ አካላት የተወጣጣው የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል እንደገለጸው 19 የህወሓት አመራር አባላት በአዲስ አበባ የሚገኙ ቋሚ ንብረት መታገዱን እንዲሁም መንግሥት ሸኔ እያለ የሚጠራው ቡድንን ይደግፋሉ የተባሉ 141 ግለሰቦች ገንዘብ እንዲታገድ መደረጉን አመልክቷል።

ግብረ ኃይሉ በአሁኑ ጊዜ ከህወሓት ጋር ተሰልፈዋል ያላቸው እነዚህ ግለሰቦች፤ ቀደም ሲል ከፍተኛ ሃብት በመመዝበር በአዲስ አበባና በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ንብረቶችን እንዳሏቸው ጠቅሶ፤ በፈፀሙት የአገር ክህደት ወንጀል የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ እንደወጣባቸው ገልጿል።

ግለሰቦቹ በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች የገነቧቸውን የመኖሪያ ህንፃዎችና ያቋቋሟቸውን የንግድ ድርጅቶች በቤተሶቦቻቸውና በወኪሎቻቻው አማካኝነት በማከራየት የሚገኘውን ገቢ "የጦር መሣሪያዎችና ጥይቶች ግዢ እንደሚውል" አመልክቷል።

ግብረ ኃይሉ ጨምሮም ንብረቶቹን በመሸጥም ሃብት ለማሸሽ ጥረት እንደተደረገ ጠቅሶ በዚህም ሳቢያ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል በማቅረብ እግዱ በፍርድ ቤት በኩል እንዲፈጸም መደረጉ ተገልጿል።

ንብረታቸው ላይ እገታ ከተጣለባቸው 19 የህወሓት አመራርና አባላት መካከል ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ፣ ሌተናል ጀነራል ፍስሐ ኪዳኑ፣ ሜጀር ጀነራል አበበ ተ/ሐይማኖት፣ ሜጀር ጀነራል ሀልፎም እጅጉ፣ ሜጀር ጀነራል ተስፋዬ ግደይ፣ ብርጋዴር ጀነራል ኃይለሥላሴ ግርማይ፣ ብርጋዴር ጀነራል ምግበ ኃይለ፣ ብርጋዴር ጀነራል ተኽላይ አሸብር ይገኙባቸዋል።

በተጨማሪም በአንዳንድ የኦሮሚያ ክፍሎች ውስጥ እንደሚንቀሳቀስ የሚነገረውና መንግሥት ሸኔ የሚለውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራውን ቡድን በገንዘብ ሲደግፉ ነበሩ የተባሉ 141 ተጠርጣሪ ግለሰቦች የገንዘብ ዝውውራቸው እንዲታገደ መደረጉንም ግብረ ኃይሉ ገልጿል።

በትግራይ ውስጥ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ ከክልሉ አስተዳዳሪነት የተወገደው ህወሓት እና በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከሚፈጸሙ ጥቃቶች ጀርባ ይገኛል የተባለው 'ሸኔ' ከጥቂት ሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ቡድኖች ተብለው መሰየማቸው ይታወሳል።