ምርጫ 2013፡ መራጮችን ከፓርቲዎች የሚያገናኘው መተግበሪያ ምን ይዞ መጣ?

የዋርካ አርማ

የፎቶው ባለመብት, WARKA

በ1997ቱ ምርጫ ብዙዎች በጉጉት የተመለከቷቸውን የምርጫ ክርክሮች በማዘጋጀት የሚታወቀው ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ ከሁለት ተቋማት ጋር በመተባበር መራጮችን ከፓርቲዎች የሚያገኛኝ ዋርካ የተሰኘ መተግበሪያ አስተዋውቋል።

የጀርመኑ የተራድኦ ድርጅት ፍሬድሪክ ኤበርት እስቲፍቱንግ እና አይስ አዲስ በቴክኖሎጂ የተሳተፉበት ይህ የመረጃ መተግበሪያ 19 ብሔራዊ ፓርቲዎችን ያቀፈ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

የፕሮጀክቱ ባለቤት ኢንተር አፍሪካ ከጊዜ ውሱንነት የተነሳ ክልላዊ ፓርቲዎችን ማካተት አለመቻሉን ተናግሯል።

የተቋሙ የኮሚኒኬሽን አማካሪ ሰይፉ በኩረ ጽዮን (ዶ/ር) ለቢቢሲ እንደተናገሩት የዲጂታል የመረጃ ማዕከሉ የፓርቲዎችን ማኒፌስቶ፣ ፕሮግራም ብሎም አቋሞቻቸውን በቀላሉ በአንድ ቦታ ተደራሽ እንዲሆን ያደርጋል።

እስካሁን ድረስ የሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች መረጃ ማካተት መቻሉን ብሎም የሦስት ፓርቲ መረጃዎችን በቅርቡ እንደሚያካትት ሰይፉ ተናግረዋል።

በድረ ገፁ ላይ እንደተጠቀሰውም የምርጫ ቀን ሁለት ሳምንት እስከሚቀረው ድረስ ፓርቲዎች ምላሻቸውን ማስገባት እንደሚችሉ ይገልጻል።

ዋርካ የሚለው ስያሜ የተመረጠው በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚታወቅ ዛፍ ስለሆነ እንደሆነ ሰይፉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። 'ዋርካ' በሶማልኛ ቋንቋ ዜና የሚል ትርጉም የያዘ መሆኑም ተጨማሪ ምክንያት እንደሆነ ገልፀዋል።

የዚህ መተግበሪያ አላማ ከጊዜ ወደ ጊዜ የብዙዎች የመረጃ ማግኛ እየሆነ በመጣው የስማርት ስልክ ላይ በቀላሉ የፓርቲዎችን አቋም ማቅረብ መሆኑን ተቋሙ ለቢቢሲ ገልጿል።

መተግበሪያው እንዴት ይሰራል?

የዋርካ መተግበሪያ ካሉት አንኳር ግልጋሎቶች መካከል የተጠቃሚውን አቋም እና ፍላጎት በቀላሉ ከፓርቲዎች ጋር ማወዳደሩ ነው።

በዋርካ የተዘጋጁት 25 መጠይቆች እስማማለሁ፣ አልስማማም ወይም ገለልተኛ ነኝ የሚሉ የመልስ አማራጮች አሏቸው።

ከጥያቄዎቹ መካከልም "አሁን ያለው ብሔር- ተኮር የፌደራል አደረጃጀት ሊቀጥል ይገባል ወይ፣ አገር አቀፍ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ሊቀመጥ ይገባል ወይ፣ የመገንጠል መብት ከሕገ መንግስቱ ይውጣ ወይ እና አዲስ አበባ ራሷን የቻለች ክልል ትሁን ወይ" የሚሉት ይገኙበታል።

ከመሬት ባለቤትነት፣ የፌደራል የሥራ ቋንቋ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥራ ዘመን ገደብ እና የጽንስ ማቋረጥን የሚመለከቱ ጥያቄዎችም ተካተውበታል።

ተጠቃሚው ጥያቄዎቹን መልሶ ሲያበቃ አቋሙን ከሚፈልገው የፖለቲካ ፓርቲ ጋር የሚያነፃፅር ሲሆን መተግበሪያው የበለጠ ከተጠቃሚው መልሶች ጋር የሚቀራረቡ ፓርቲዎችን በመቶኛ ያስቀምጣል።

እንዲሁም በ25ቱም ጥያቄዎች ላይ ፓርቲዎቹ የየራሳቸውን አቋም ያስረዳሉ።

በአንድሮይድ መተግበሪያው እና ድረ ገፅ ላይ የፓርቲዎቹን ፕሮግራም የያዘው ዋርካ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ሕጎችን በተመለከተ ከምርጫ ቦርድ የመረጃ ቋት ጋር የሚያገናኙ ማስፈንጠሪዎችን ይዟል።

መተግበሪያው ውስጥ የተካተቱ ፓርቲዎች ገና የተሟላ መረጃ የላቸውም። ኢንተር አፍሪካ እነዚህን መረጃዎች ከፓርቲዎቹ ለመሰብሰብ ፈተና እንደሆነበት ሰይፉ (ዶ/ር) ተናግረዋል። አገልግሎቱ ለሕዝብ ይፋ ከተደረገ ገና አንድ ወር እንዳለሞላውም ጨምረው ገልፀዋል።

ከምርጫ በኋላ ግልጋሎቱ ይቀጥላል?

መተግበሪያው ካሉት መልኮች መካከል የፖለቲካ ፓርቲዎችን የማወያየት እና ከመራጮች ጋር የሚገናኙበት ዘዴ ሆኖ ማስቀጠል የፕሮጀክቱ አካል እንደሆነ ሰይፉ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

ይህም ከምርጫ በኋላም የሚቀጥል እንደሆ ያስረዳሉ።

ፓርቲዎችን ገፅ ለገፅ የሚያገናኙ መድረኮችን ማዘጋጅት እና ከዚያ የሚገኙ ግብአቶችን ወደ መተግበሪያው ለማምጣት ማሰቡን ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ ገልጿል።

እንዲሁም ፓርቲዎቹ ከምርጫ በኋላ ምን አሉ ወይም ምን ሰሩ የሚለውን በመከታተል በመተግበሪያው ላይ እንደሚያካትት አመልክቷል።

መተግበሪያው ከፊታችን ላለው ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ የመረጃ ምንጭ ለመሆን ከታሰበው ጊዜ በላይ መጓተቱን ገልፀው ለዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች በወቅቱ መረጃዎችን አለማቅረባቸው ምክንያት ነው ብሏል።

አገልግሎቱ በኢንተርኔት ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑ በምርጫው ሰሞን የአገልግሎት መቋረጥ እንደስጋት የተያዘ መሆኑን ሰይፉ (ዶ/ር)ገልፀዋል።

"ኢንተርኔት እንደማይቋረጥ ተስፋ እናደርጋለን። ይህ ግን የመንግሥት ውሳኔ ነው" ብለዋል።

መተግበሪያው እስከአሁን በአማርኛ ቋንቋ ብቻ መረጃዎችን የሚያቀርብ ሲሆን በቀጣይ በተለያዩ የአገር ውስጥ ቋንቋዎች አማራጮችን ለማስፋት እቅድ መያዙን ሰይፉ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

ለፕሮጀክቱ የወጣውን ወጪ በተመለከተ ግልፅ የተደረገ መረጃ የለም።