ምርጫ 2013፡ የምርጫው መራዘም የቆሰቆሳቸው ስጋቶች

መራጮች ሲመዘገቡ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, 36 ሚሊዮን መራጮች ተመዝግበዋል

በኢትዮጵያ 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ በተወሰኑ ሳምንታት መገፋት አገሪቱ ውስጥ ሌላ የፖለቲካ ትኩሳት ይፈጥር ይሆን የሚል ስጋት ቆስቁሷል።

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ከበርካታ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር ተሰብስበው ነበር።

ምርጫ በማስፈጸሙ ሂደት፣ በተለይም ከመራጮች ምዝገባ ጋር ተያይዞ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎችን በማሰልጠንና ድምጽ መስጫ ካርዶችን በወቅቱ በማዘጋጀት በኩል ወዘተ ፈተናዎች እንደሚኖሩ በስብሰባው ላይ ተነስቷል።

ብርቱካን ሚደቅሳ ምርጫው ምናልባት በተያዘለት ዕለት ግንቦት 28 እንደማይካሄድ ጠቁመው፤ ምናልባት በሁለትና በሦስት ሳምንታት ሊገፋ እንደሚችል አብራርተዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎችም ምክረ ሐሳባቸውን እንዲያስገቡ ጋብዘዋል።

ይህ ምርጫ በመጀመርያ ሊካሄድ ታስቦ የነበረው ባለፈው ዓመት ነሐሴ ላይ ነበር። በአንድ ዓመት እንዲገፋ ያደረገው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስጋት እንደነበር ይታወሳል።

ምርጫው በድጋሚ ሊራዘም ይችል ይሆን?

በምርጫ ቦርድ በተጠራው ስብሰባ ላይ ቦርዱድ የገጠመውን የሎጂስቲክ ፈተና ለፓርቲ ተወካዮች አስረድቷል። በተለይም የመራጮች ምዝገባ እና የምርጫ ቁሳቁሶችን የማዳረስ ተግዳሮቶች ተጠቅሰዋል።

አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች በበኩላቸው የፌዴራል መንግሥት በአገሪቱ እዚህም እዚያም በሚፈጠሩ የጸጥታ ስጋቶች መወጠሩን አንስተው፤ በምርጫው ወቅት የጸጥታ ኃይሎች በመላው አገሪቱ ደኅንነት ለማስጠበቅ ብዙ ቦታ መሸፈን ፈተና ሊሆንባቸው እንደሚችል ጠቁመዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች የተቆሰቆሱ ብሔር ተኮር ግጭቶች የምርጫ ቁሳቁሶችን እንደልብ ወደ በርካታ ቦታዎች ለማድረስ ፈታኝ አድርጎታል።

በሰኔ ወር የሚጀምረው የዝናብ ወቅት በሐምሌና በነሐሴ መጠኑን ጨምሮ እየተስፋፋ ይሄዳል። በዚህ ወቅት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ምርጫ ማካሄድ እንዴት አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ያነሱ የፓርቲ ተወካዮችም ነበሩ።

ሌሎች ደግሞ ምርጫው በአዲሱ ዓመት ወደ መስከረም ቢሻገር የተሻለ እንደሚሆን ያስገነዘቡም ነበሩ። ነገር ግን ያ ሌላ የፖለቲካ ምስቅልቅል የሚፈጠር ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም አዲስ መንግሥት ተመሥርቶ ሥራ የሚጀምርበት ወር ስለሚሆን።

የምርጫ ቅስቀሳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲ ብልጽግና ቅስቀሳ ሲያካሂድ

በምርጫው መራዘም ማን ምን አለ?

የምርጫው መራዘም ሐሳብ እምብዛምም በአገሪቱ የተለየ ስሜት የፈጠረ አይመስልም።

አንዳንዶች ምርጫው በሁለትና ሦስት ሳምንታት መገፋቱ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ለማስፈጸም እንዴት የተሻለ ሁኔታ ሊፈጥርለት እንደሚችል አልታይ ብሏቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በበኩላቸው ምርጫ ቦርድ ነጻ ሆኖ እየሰራ እንደሆነ ካሰመሩበት በኋላ ምርጫውን በማራዘሙ ሐሳብ እንደተስማሙ በትዊተር ሰሌዳቸው ጽፈዋል።

"ለኢትዮጵያ ሕዝብ ላረጋግጥ የምፈልገው በምንችለው ሁሉ ካለፉት ምርጫዎች የተሻለ፣ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ እየሰራን እንደሆነ ነው" ብለዋል።

ጨምረውም ምርጫው በቀጣይ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ እንደሚካሄድና ከብዙዎች ግምት በተለየ መልኩም የመራጮች ምዝገባ በጥሩ ሁኔታ መካሄዱን ተናግረዋል።

ነገር ግን አንዳንድ ቡድኖች መንግሥት ከብሔራዊ ምርጫው በፊት ብሔራዊ ንግግርና መግባባትን እንዲያስቀድም ይጠይቃሉ።

በትግራይ ያለው ቀውስና በሌሎች አካባቢዎችም እየጋመ ያለው የብሔር ግጭት ብሔራዊ ምርጫ ሳይሆን ብሔራዊ ምክክር እንደሚያስፈልግ ማሳያ ናቸው ይላሉ እነዚህ ወገኖች።

እነዚህ ወገኖች መንግሥት የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት ለብሔራዊ እርቅ ራሱን ማዘጋጀት አለበትም ይላሉ።

ምርጫው ከትግራይ ግጭት ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?

ባለፈው ዓመት ነሐሴ ላይ ሊካሄድ የነበረው ምርጫ መራዘም ማዕከላዊው መንግሥት በወቅቱ በትግራይ ከነበሩት አመራሮች ጋር ፍጥጫ ውስጥ እንደከተተው አይዘነጋም።

የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሥልጣን መልቀቅን ተከትሎ ወደ ሥልጣን የመጡት ዐቢይ አህመድ ምርጫው በወረርሽኙ ምክንያት መራዘሙ የግድ እንደሆነ አስምረውበት ነበር።

ይህ ውሳኔ ታዲያ በወቅቱ የህወሓት ሰዎችን አበሳጭቶ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩንም የሥልጣን ጊዜያቸውን በሕገወጥ መንገድ ለማራዘም እየሞከሩ ነው ሲሉ ከሰዋቸውም ነበር።

በመጨረሻም ዐቢይ አህመድ ከመስከረም 30 በኋላ ሕገወጥ መሪ ናቸው እስከማለት ደርሰው እንደነበር ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ ህወሓት በትግራይ የራሱን የተናጥል ምርጫ ለማድረግ ደፋ ቀና ማለት ጀመረ። ምርጫውም ተካሄዶ ህወሓት በከፍተኛ ድምጽ መመረጡን ገለጸ።

ይህ በትግራይ የተደረገው ምርጫ ህወሓትን ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር ከፍተኛ ቅራኔ ውስጥ ከተተው።

ሁለት ወራትን ቆይቶ የህወሓት ኃይሎች የሰሜን ዕዝ ላይ ድንገተኛ ጥቃት ከፈቱ። ይህም የማዕከላዊው መንግሥት ወታደራዊ እርምጃ እንዲወስድ አስገደደው።

በዚህ መልኩ የተቆሰቆሰው ጦርነት አሁን ሰባተኛ ወሩን ይዟል። ሺዎችን ለሞትና ለመፈናቀል ዳርጓል።

የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎች በዚህ ጦርነት የተፈጸሙ በርካታ አሰቃቂ ኢሰብአዊ ድርጊቶችን ሪፖርት አድርገዋል።

ይህም ግድያን፣ አስገድዶ መድፈርንና ሌሎች ኢሰብአዊ ድርጊቶችን የሚጨምር ነው። አንዳንዶቹ ኢሰብአዊ ድርጊቶች ማዕከላዊውን መንግሥት ለማገዝ ወደ ጦርነት በገባው የኤርትራ ሠራዊት የተፈጸሙ ናቸው።

የሰብአዊ ድግፍ ሰጪዎች የምግብና መድኃኒት እርዳታዎች ወደ ተጎጂዎች እንዳይደርሱ ሆነዋል ሲሉ ተደጋጋሚ ክስ ያቀርባሉ።

ለምርጫው ምን ያህል ሰዎች ተመዘገቡ?

110 ሚሊዮን ሕዝብ ባላት ኢትዮጵያ ባለፈው ሳምንት በተጠናቀቀው የምርጫ ምዝገባ በትንሹ 36 ሚሊዮን ዜጎች ተመዝግበዋል።

ይህ አሃዝ ይጠበቅ ከነበረውና ይመዘገባል ተብሎ ተተንብዮ ከነበረው ሕዝብ ቢያንስ በ10 ሚሊዮን ያነሰ ነው። ነገር ግን ቁጥሩ በፈረንጆች 2015 ከተደረገው ምርጫ ጋር ተቀራራቢ ነው።

በኦሮሚያ 15 ሚሊዮን ሕዝብ ለመራጭነት መመዝገቡ ያልተዋጠላቸው ሰዎች አሉ። ምክንያቱም በዚህ ክልል ዋንኛ የሚባሉ ተቃዋሚዎች በማይሳተፉበት ሁኔታና ዋንኛው የፖለቲካ ተቀናቃኝ አቶ ጃዋር መሐመድ እስር ቤት ባሉበት ሁኔታ ይህን ያህል ቁጥር ያለው ሕዝብ በክልሉ ለምርጫ ሊመዘገብ አይችልም ብለው የሚከራከሩ አሉ።

ቀደም ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር በምርጫው ዙሪያ የሚደረጉ ዝግጅቶችን በተመለከተ ሲሰነዘሩ የነበሩ ትችቶችን ገሸሽ ማድረጉ ይታወሳል።

የአውሮፓ ሕብረት ተወካዮቹን እንደማይልክ ከገለጸ በኋላ መንግሥት ውሳኔያቸውን እምብዛም ተጽእኖ የሌለው እንደሆነ በመግለጽ ነበር ያጣጣለው።