ምርጫ 2013፡ “ከዘንድሮ ምርጫ በመውጣታችን አይቆጨንም”

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ ፓርቲያቸው ከዘንድሮ ምርጫ በመውጣት 'አይቆጨንም' ሲሉ ተናገሩ።
ከተማሪዎች ንቅናቄ ጀምሮ ከ50 ዓመት በላይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ ሲያደርጉ የቆዩት ፕሮፌሰር መረራ፤ ፓርቲያቸው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ከስድስተኛው አገራዊ ምርጫ 'በመንግሥት ተጽዕኖ መውጣቱን' ይናገራሉ።
ፕሮፌሰር መረራ፣ ፓርቲያቸው ከምርጫው ስለወጣበት መንገድ እና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያሳለፉትን ጉዞ በተመለከተ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
"ከዚህ በፊት ሲደረጉ የነበሩ ድርድሮች መግባባት መፍጠር አልቻሉም"
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ከምርጫ ለመውጣት ከመወሰኑ በፊት ላለፉት ሶስት ዓመታት፣ ከገዢው ፓርቲ እና ከተለያዩ አካላት ጋር ድርድር ሲያደርግ እንደነበር ፕሮፌሰር መረራ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከእነዚህ ድርድሮች መካከል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ መሐመድ የተገኙበት ድርድር እንደነበር የሚያስታውሱት ፕሮፌሰሩ፣ ይኹን እንጂ ሲደረጉ የነበሩት ድርድሮች፣ አገራዊ መግባባትን መፍጠር አልቻሉም ብለዋል።
"መንግሥት . . .በአገሪቷ ውስጥ የሚደረጉ ለውጦች በበላይነት እንዲመራ ነው የሚፈልገው። እርሱን አትንኩብን ነው የሚሉት። ይህችን አገር ቀጥለን እኛ ነን መምራት ያለብን ከሚለው ሕልማቸው መውጣት አልቻሉም፤ እኛ ደግሞ የታሰርንበት፣ ስቃይ ያየንበት፣ ትልቅ ዋጋ የከፈልንበት፣ የኦሮሞ ልጆች ደማቸው የፈሰሰበት ይህንን ስርዓት መለወጥ ነው ፍላጎታችን።"
አገር በሚመራው ፓርቲ እና በኦፌኮ መካከል የተፈጠረው ልዩነት የፓርቲያቸው አባላት እንዲታሰሩ እና ቢሯቸው እንዲዘጋ ምክንያት መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።
"ለምርጫ የሚያስፈልግ ከቀድሞ የተለየ ነገር የለም። የተሻሻለ ነገር የለም" ያሉት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፤ ምርጫ ሠላም ማምጣት፣ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲወለድ ማድረግ፣ እንዲሁም መልካም አስተዳደር ሠፍኖ የሕዝብ ስሜት የአገሪቷን ኢኮኖሚ ወደ ማሳደግ መሄድ አለበት ብለዋል።
ስድስተኛ አገር አቀፍ ምርጫ ይህንን ሶስት ነገሮችን እስከ አላሳካ ድረስ ከዚህ በፊት ሲደረግ ከነበረው ምርጫ ምንም ልዩነት የለውም ይላሉ።
በዚህም ምክንያት ፓርቲያቸው በዚህ ዓመት ምርጫ ላይ ባለመሳተፉ እንደማይቆጫቸው ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የብልጽግና ፓርቲ ከስድስተኛ አገር አቀፍ ምርጫ ለመውጣት ፓርቲዎች ያቀረቡትን ምክንያት መሰረተ ቢስ ነው ማለቱ ይታወሳል።
"ከፖለቲካ ለመውጣት ምንም ሃሳብ የለኝም"
ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ ከሶስት ዓመት በፊት ከእስር ሲፈቱ፣ ከፖለቲካ ራሳቸውን ማግለል ይፈልጉ እንደነበር የተናገሩ ቢሆንም፣ አሁን ግን ከፖለቲካ ለመውጣት ምንም ዓይነት ፍላጎት እንደሌላቸው አረጋግጠዋል።
"ከፖለቲካ ለመውጣት ተስፋ መቁረጥ አለብህ፤ ሁለተኛ ደግሞ በቃኝ ከዚህ በኋላ ምንም ትልቅ ለውጥ ማምጣት አልችልም የምትል እና ወደ ሌላ ማስተላለፍ እፈልጋለሁ የሚል ደረጃ ላይ መድረስ አለብህ፤ አሁን ሳየው እዚያ ደረጃ ላይ መድረስ አልቻልኩም።"
አሁን ራሳቸውን ከፖለቲካ ማግለል እንደማይፈልጉ የሚናገሩት ፕሮፌሰር መረራ "የዚህች አገር ትግል መሃል መንገድ ላይ ነው" ያለው ይላሉ።
"ወንዝ አልተሻገረም፤ አሁን የምንለያይበት ጊዜ አይደለም"
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ እንደነበራቸው ፓርቲያቸውም ለኦሮሚያ ክልልም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ መልካም አስተዋጽኦ ሲያበረክት እንደነበረ ፕሮፌሰር መረራ ተናግረው። "እንደ ታጋይ ምንም አልልም፤ ይህን ያህል ዓመት በትግል ውስጥ የቆየሁበትን ጊዜ ሳስበው የሚቆጨኝ ነገር የለም። ለምን ይህን ያህል ዓመት ትግል ውስጥ ቆየሁ ብዬ ሳስብ የሚቆጨኝ ነገር የለም፤ የቻልኩትን ያህል ሳበረክት ነው እስካሁን የመጣሁት"
ግማሽ ምዕተ ዓመት ያስቆጠረው የፕሮፌሰር መረራ የፖለቲካ ትግል ጉዞ፣ ወንዝ እንዳልተሻገረ ይናገራሉ።
"ታጋይ ትግሉን ወንዝ ማሻገር ይኖርበታል፤ ትግሉ ግን አልተሻገረም፤ ምኞት፣ ተስፋ፣ ሕልም ከወንዙ ባሻገር ነው " ይላሉ።
በዚህን ሰዓት ፓርቲያቸው ኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ የአቅሙን ያህል እየተንቀሳቀሰ እንዳለ ተናግረዋል።
ስለ ኦሮሚያ ሪፐብሊክ መገንባት እና ዲሞክራቲክ ኢትዮጵያ መፍጠር
ከዚህ በፊት በኦሮሞ ምሁራን መካከል ሪፐብሊክ ኦሮሚያን ወይንም ዲሞክራቲክ ኢትዮጵያን መገንባት አልያም ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር እንደ አገር መቀጠል የሚለው ሃሳብ ልዩነት ሲፈጥር ነበር።
አሁንም እነዚህ ሃሳቦች ከተለያየ አቅጣጫ ይደመጣሉ።
እነዚህ በኦሮሞ ምሁራን መካከል የሚታዩ የተለያዩ ሃሳቦች የሕዝቡን ፍላጎት ሲጎዳ ነበር አሁንም እየጎዳ ነው የሚሉት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና አሁን ግን ልዩነቶቹ እየጠበቡ መጥተዋል ይላሉ።
"እንደ ቀድሞው የተራራቁ አይደሉም። የኦሮሞ ሕዝብ እና የኦሮሞ ምሁራን በሁለቱም መንገድ የኦሮሞ ሕዝብ ነጻ እስከወጣ ድረስ በሁለቱም መንገድ ሃሳቡን መውሰድ የተዘጋጁ ነው የሚመስለኝ" ይላሉ።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ መመለስን በማንሳት፣ "በዚህች አገር ውስጥ እየተገነባ ያለውን የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ እንሳተፋለን ብለው ነው የመጡት፤ ሃሳቦች እየተቀራረቡ መጥተው ነበር። መንግሥት በሩን ባይዘጋ ኖሮ ብዙ ርቀቶች መሄድ ይቻል ነበር" ሲሉ ይናገራሉ።
ፕሮፌሰር መረራ ማን ናቸው?
እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1948 በምዕራብ ሸዋ ዞን ቶኬ ኩታዬ የተወለዱት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በፖለቲካ ውስጥ አስርት ዓመታት ቆይተዋል።
ፕሮፌሰር መረራ በአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግሥት ተማሪዎች ንቅናቄ ላይ ከተሳተፉበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በፖለቲካ ውስጥ ጎልህ ድርሻ አላቸው።
ወደ ኋላ ላይ መኢሶን ተቀላቅለው በደርግ ዘመን ሰባት ዓመት ታስረዋል።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ግብጽ ከሚገኘው አሜሪካ ዩኒቨርስቲ ፖለቲካ ሳይንስ አግኝተዋል።
እንዲሁም ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ኔዘርላንድስ ተምረዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለበርካታ አመታት በመምህርነት ያገለገሉት ፕሮፌሰር መረራ የኢትዮጵያ ፖለቲካን የተመለከቱ መጽሐፍት እና ጥናቶች አሳትመዋል።
በተጨማሪም የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ እና የኦሮሞ ሕዝብ ኮንግረስን አሁን ደግሞ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ በሊቀመንበርነት መርተዋል።
ፕሮፌሰር መረራ በ1997 ዓ.ም የተካሄደው ምርጫን አሸንፈው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመግባት ለአምስት ዓመታት ማገልገላቸው ይታወሳል።












