ኬንያ የሶማሊያ የሰብዓዊ እርዳታ በረራዎችን አግዳለሁ ስትል አስጠነቀቀች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኬንያ የሰብዓዊ እርዳታ ተልዕኮ ያላቸውን ጨምሮ ማንኛውንም ከሶማሊያ የሚደረጉ ማንኛውንም በራራዎችን እንደምታግድ አስጠንቅቃለች።
የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴ የሰብዓዊ ተልዕኮ ያላቸው በረራዎች ለማይሆን ተግባር ውለዋል ሲል ለዲፕሎማቶች በፃፈው ደብዳቤ አስታውቋል።
ኬንያ የሶማሊያን የንግድ በረራዎች ብታግድም ነገር ግን ለሰብዓዊ ተልዕኮ የሚውሉ በረራዎችን ከማገድ ታቅባ ነበር። ነገር ግን በአሁኑ ደብዳቤ መሰረት ሰብዓዊ ተልዕኮ ያላቸው በረራዎች ለፖለቲካ ጉዳዮች መጠቀሚያ ሆነዋል ብላለች።
ኬንያ በቅርቡ ከጎረቤት አገር ሶማሊያ የሚመጡ በረራዎችን ያገደች ሲሆን እግዱ ተግባራዊ አይሆንባቸውም ተብለው የነበሩት ለአስቸኳይ ህክምና የሚደረጉ በረራዎችና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰብዓዊ ተልዕኮዎችን ነበር።
የሰብዓዊ እርዳታ በረራዎች ለሰብዓዊ አገልግሎት ብቻ መዋል አለባቸው በማለት ያስጠነቀቀችው ኬንያ ካለበለዚያ ግን እነዚህንም በረራዎችን በማገድ ሙሉ በሙሉ እግዱ ተፈፃሚ ይሆናል ብላለለች።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ማንኛውም የሰብዓዊ እርዳታ በረራዎች መጀመሪያ ፈቃድ ሊያገኙ እንደሚገባና የሚያጓጉዟቸውን ግለሰቦችም ሆነ ቁሳቁሶች ዝርዝርም ማሳወቅ አለባች።
ከጊዜ ወደጊዜ ግንኙነታቸው እየሻከረ የመጣው ኬንያና ሶማሊያ በተለይም አገራቱ የሚያወዛግባቸው ጉዳይ መነሻ የሆነው በባህር ላይ አዋሳኝ የሆነው ስፍራ ነው።
ሶማሊያ ጉዳዩ በአለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት እንዲፈታ በማለትም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤቱ የወሰደችው በአውሮፓውያኑ 2014 ነው።
በቅርቡ ደግሞ ኬንያ ራስ ገዝ አስተዳደር የሆነችውን የጁባላንድ አስተዳዳሪዎችን በመርዳት በውስጥ ጉዳዬ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ጣልቃ እየገባች ነው ስትል ሶማሊያ ግንኙነቷን ያቆመችው በህዳር ወር ነበር።
በግንቦት ወር በኳታር አሸማጋይነት የሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተሻሽሏል ቢባልም ኬንያ በሳምንቱ ከሶማሊያ የሚደረጉ በረራዎችን እንዳገደች አስታወቀች።
ኬንያ እንደምትለው ከሶማሊያ ጋር የምትጋራው የበረራ መስመር ዝግ መሆኑን ያስታወቀች ሲሆን ይህም ሁኔታ የሁለቱንም አገራት ግንኙነትም ወደ ባላንጣነት ቀይሯል ተብሏል።












