ቤላሩስ አውሮፕላን አስገድዳ በማሳረፍ የያዘችው ጋዜጠኛ ማን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከሰሞኑ የአውሮፓ ህብረት የቤላሩስ አየር መንገድ በአውሮፓ ሰማይ ላይ እንዳይበር ማዕቀብ ጥሏል።
የ27 አባላቱ ህብረት ለዚህ መነሻ የሆነው ቤላሩስ ጋዜጠኛውን ሮማን ፕሮታሴቪችን ለመያዝ በሚል የተሳፈረበትን አውሮፕላን አቅጣጫ ቀይሮ በመዲናው ሚኒስክ ተገዶ እንዲያርፍ መደረጉን ተከትሎ ነው።
የመንግሥት ጠለፋ የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ድርጊት የቤላሩስ መንግሥት የጦር አውሮፕላን በመላክም ነው አውሮፕላኑ ተገዶ እንዲያርፍ ያደረገው።
ለመሆኑ መንግሥት የጦር አውሮፕላኑን ልኮ ያሳረፈው ጋዜጠኛ ማን ነው?
የ26 አመቱ ሮማን ፕሮታሴቪች በአሁኑ ወቅት በሚኒስክ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ነው ያለው።
ሮማን እስከ ህዳር ወር ድረስ እንደሱ ተቃዋሚ በሆነው ስቴፓን ፑቲሎ በተመሰረተውና በቴሌግራም በሚሰራጨው የተቃዋሚው ኔክስታ ቻናል አዘጋጅ ነበር።
ኔክስታና ኔክስታ ላይቭ የተባሉት ሚዲያዎች የጎዳና ላይ ተቃውሞዎችን በማዘጋጀት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል። ከፍተኛ ቁጥጥርና ክትትል ከመንግሥት ቢደረግባቸውም ሁለት ሚሊዮን ተከታይ አላቸው።
ሮማን በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ክሶች ይጠብቁታል ተብሏል።
እሱና ስቴፓን በቤላሩስ መንግሥት በሽብር ድርጊቶች የተሳተፉ በሚል የስም ዝርዝራቸው ባለፈው አመት ወጥቶ ነበር። በአገሪቱ ውስጥ ህዝባዊ አለመረጋጋት ማነሳሳት እስከ አስራ አምስት አመት ድረስ እስር ያስቀጣል።
ሬናናይር በተባለው የአውሮፕላን መንገድ ተሳፍሮ እየበረረ እያለ አውሮፕላኑ አቅጣጫውን ወደ ሚኒስክ ሲያደርግ ሮማን ተደናገጠ ትላለች ሞኒካ ሲምኪየኔ የተባለችና አብራ ተሳፍራ የነበረች መንገደኛ።
"ወደ መንገደኞቹም ዞሮ የሞት ቅጣት ይጠብቀኛል ብሎ ተናገረ" ብላለች ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል።
የ23 አመቷ የሮማን የሴት ጓደኛ ሶፊያ ሳፔጋም አውሮፕላኑ በሚኒስክ እንዲያርፍ ከተገደደ በኋላ በቁጥጥር ስር ውላለች።
ዜግነቷ ሩሲያዊ ሲሆን በሉውቴንያ በሚገኘው የአውሮፓ ሂውማኒቲስ ዩኑቨርስቲ የህግ ተማሪ ናት።
ትንሽ ሰራተኛ ያለው ኔክስታ የተመሰረተው በፖላንድ ሲሆን በጎረቤት አገር ሉውቴንያ ካሉ የቤላሩስ ተቃዋሚዎችም ጋር በቅርበት ይሰራል።
የቤላሩስ ተቃዋሚ መሪ ሲቬትላና ቲካኖቭስካያ የሚኖሩት በሉውቴንያ ነው። ሉውቴንያ የኔቶ እንዲሁም አውሮፓ ህብረት አባል አገር ናት።
በባለፈው አመት የተነሱ ከፍተኛ ተቃውሞዎችን ተከትሎ በቤላሩስ ነፃ ሚዲያና የተቃውሞ ድረገፆች ተዘግተዋል። በዚህ ሁኔታ ደግሞ ለቤላሩስ አማራጭ መቃወሚያ መንገድ እንዲሁም ዜናዎችን ማስተላለፊያ መንገድ የሆነው ቴሌግራም ነው።
ኔክስታ ላይቭ ወይም ኔክታ ተብሎ የሚጠራው ሚዲያ በቤላሩስ ቋንቋ "አንድ ሰው" የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን በኔክስታ ቻናሎች ውስጥ በርካታ ተከታዮች አሉት።
ኔክስታ ላይቭ ከሚያወጧቸው ፖስቶች መካከል የፖሊስ ጭካኔን የሚያሳዩ ፎቶዎችና ቪዲዮዎች እንዲሁም የተቃውሞ ሰልፎችና ስራ ማቆም አድማዎችን በተመለከተ መረጃ ያስተላልፋል።
አምና ነሐሴ ወር በተደረገው ምርጫ ፕሬዚዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ አሸንፌያለሁ ማለታቸውን ተከትሎ ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል ቤላሩስ በተቃውሞ እየተናጠች ነበር።
ጨቋኝ ናቸው የሚባሉት ፕሬዚዳንት አሌክሳንደር ለባለፉት 27 አመታት ቤላሩስን አስተዳድረዋል። የአገሪቱ መሰረተ ልማቶችም በመንግሥት ቁጥጥር ስር ያሉ ሲሆን ከፍተኛ የሆነ ክትትል እንዲሁም ጥሰቶች እንደሚፈፀምም ይነገራል።

የፎቶው ባለመብት, t.me/nexta_live
ሮማን እንዳለው የኔክስታ ፕሮጀክት ከውጭ አገራት ድጋፍ የለውም ገንዘቡን የሚያገኘው ከማስታወቂያዎች ገቢ ነው።
መስራቹ ስቴፓን ፑቲሎ ይህንን ሚዲያ ያቋቋመው በአውሮፓውያኑ 2015 በዩቲዩብ ቻናልነት ነበር። በኋላም ነው ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው መረጃዎችን ወደማስተላለፍ የተሸጋገረው።
በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ ያለው ሮማን ቤላሞቫ ለሚባል የቴሌግራም ቻናል ይሰራል። የቤላሞቫ ጦማሪ ኢጎር ሎሲክ ባለፈው አመት ሰኔ ወር ላይ መታሰሩን ተከትሎ ነው ሮማን በዚህ ሚዲያ ላይ መፃፍ የጀመረው።
አንዳንድ ተችዎች ኔክስታ የሚያቀርባቸው መረጃዎች ያልተረጋገጡ ናቸው ይላሉ። ለምሳሌም ያህል በአንድ ወቅት የሩሲያ ልዩ ኃይል ቤላሩስ መግባታቸውን የሚያሳይ መረጃ ፅፎ የነበረ ሲሆን በኋላም ስህተት ነው በሚል ከቻናሉ እንደተወገደ ቢቢሲ ሞኒተሪንግ ዘግቧል።
ባለፈው አመት ነሐሴ ወር ላይ ተቃውሞው በከፍተኛ ሁኔታ በተጋጋለበት ወቅት ኔክስታ በሰዓት ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ መልዕክቶች ከቤላሩስ ዜጎች ይደርሰው እንደነበር ሮማን ለቢቢሲ በአንድ ወቅት ተናግሯል።
ኔክስታ የተቃውሞ ማዕከል ወይስ ሚዲያ ነው ተብሎ ሮማን ከቢቢሲ ሩሲያ ጥያቄ በቀረበለት ወቅት "ይሄንን ነን ማለት አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን በዋነኝነት የቤላሩስ ዜጎች የሆንን በአገራችን አምባገነንነት እንዳይሰፍን የምንፈልግና በነፃነት አገራችን ተመልሰን መኖር የምንፈልግ ነን" ብሎ ነበር።
ከሁለት አመት በፊት ከቤላሩስ የወጣው ሮማን በባለፈው አመትም የፖላንድ ዜግነት ለማግኘት ጥያቄ አቅርቧል።
በባለፈው አመትም ቤተሰቦቹንም ወደ ፖላንድ አምጥቷል። አባቱ ዲሚትሩ በቤላሩስ የጦር አካዳሚ ውስጥ መምህርና ተጠባባቂ የጦር ኃላፊ ናቸው።
ሮማን የፕሬዚዳንት አሌክሳንደርን አገዛዝ መቃወም የጀመረው በአውሮፓውያኑ 2011 ሲሆን በወቅቱም የተቃውሞ ሰልፍ ተሳትፈሃል ተብሎ ከትምህርት ቤት ተባሮ ነበር።
በኋላም በቤላሩስ የመንግሥት ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት ትምህርቱን ለመከታተል ቢገባም ከዚያም ተባሯል።
ሮማን ወደ ፖላንድ የሄደው ሌላኛው ተቃዋሚ ቭላድሚር ቹዴንስቶቭ መታሰሩን ተከትሎ ነው።
"በቁጥጥር ስር መዋሉን የሰማሁት የመጀመሪያ ሰው እኔ ነኝ። መረጃውንም ያጋራሁት እንዲሁም በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችም ስለ እሱ እስር ተቃውሜ ተናግሬያለሁ" ብሏል።












