አሜሪካዊው የቀድሞ ፓይለት በበረራ ላይ ነውረኛ ድርጊት መፈፀሙን አመነ

ሳውዝ ዌስት አውሮፕላኖች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቀድሞ የአሜሪካ አየር መንገድ አብራሪ በአየር ላይ ነውረኛና አፀያፊ የሚባሉ ድርጊቶችን መፈፀሙን አምኗል።

ይህም የተከሰተው ባለፈው አመት ሲበር በነበረበት ወቅት ነው ተብሏል።

የ60 አመቱ ማይክል ሃክ በአብራሪዎች ክፍል ውስጥ እርቃኑን ለሴት ረዳት አብራሪ እንዳሳየና በላፕቶፑም ላይ የወሲብ ፊልሞችን ይመለከት እንደነበር አቃቤ ህግ በክሱ አስረድቷል።

በሜሪላንድ የሚገኙ ዳኛ ለዚህ ጥፋቱ 5 ሺህ ዶላርና የአንድ አመት የስራ እግድ ጥለውበታል።

ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘበት ከፊላደልፊያ አለም አቀፍ አየር መንገድ ወደ ኦርላንዶ በሚያደርገው በረራ ላይ ሲሆን ወቅቱም ባለፈው አመት ነሐሴ ነበር።

በረራው ከፍታ ላይ ደርሶ በተመሳሳይ ፍጥነት መብረር ሲጀምር ከፓይለት ወንበሩ ተነስቶ የወሲብ ፊልሞች በላፕቶፑ ላይ መመልከት መጀመሩ ተገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ ሴት ረዳት አብራሪ ስራዋን እየሰራች በነበረችበት ወቅትም እርቃኑን ማሳየቱን ተገልጿል።

ፓይለቱና ይህች ረዳት አብራሪ ከዚህ ቀደም እውቅና እንደሌላቸው የፌደራል አቃቤ ህግ ባወጣው መግለጫ አትቷል።

የአሜሪካ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ረዳት ኃላፊ ሚካኤል ከኒንግሃም እንደገለፁት "ፓይለቱ ምንም ያነሳሳው ምን ረዳት አብራሪዋ ለእንዲህ አይነት አፀያፊ ባህርይ መጋለጧ ተገቢ አልነበረም" ብለዋል።

ግለሰቡ የተከሰሰበትን በህዝብ መገልገያ ቦታዎች ላይ አፀያፊና ነውረኛ ተግባራት መፈፀሙን አምኗል።

ግለሰቡ ላሳየው ያልተገባ ባህርይ ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን ሁኔታውንም የፈፀመው ከአንድ ፓይለት ጋር በቀልድ መወራረዳቸውን ተከትሎ እንደሆነ ተናግሯል።

ሃክ በሳውዝ ዌስት አየር መንገድ ለ27 አመታት ያህል በፓይለትነት የሰራ ሲሆን ባለፈው አመት ነሐሴ ወር ላይ ነው በጡረታ የተሰናበተው።