ኮቪድ፡ በቪየትናም አዲስ የዩኬ እና ሕንድ ቅይጥ የኮቪድ ዝርያ መገኘቱን የጤና ባለሥልጣናት አስታወቁ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በደቡብ ምስራቅ እስያ የምትገኘው ቪየትናም በዩናይትድ ኪንግደምና በሕንድ የተገኘው የኮቪድ-19 ዝርያ ቅይጥ ባህርያትን የያዘ ነው የተባለ ቫይረስ ማግኘቷን አስታወቀች።
የአገሪቷ ባለሥልጣናት እንዳሉት ቫይረሱ በአየር ላይ በፍጥነት የሚተላለፍ ነው።
የቪየትናም ጤና ሚኒስተር ንጉየን ታንህ ቅዳሜ ዕለት መገኘቱ የተረጋገጠው አዲሱ የኮቪድ ዝርያ እጅግ አደገኛ ነው ብለዋል።
ቫይረስ ሁል ጊዜም ቢሆን ራሱን የመለወጥ ጠባይ ያለው ሲሆን አብዛኞቹ ጉዳት የሚያስከትሉ አይደሉም። ይሁን እንጅ አንዳንዶቹ ቫይረሶች በፍጥነት ተላላፊ ይሆናሉ።
እአአ ጥር 2020 ኮቪድ-19 ለመጀመሪያ ጊዜ ከተገኘበት ጊዜ አንስቶ በሺዎች የሚቆጠሩ ልውጥ ዝርያዎች ተገኝተዋል።
ሚኒስትሩ ንጉየን "ቪየትናም መጀመሪያ በሕንድ ከዚያም በዩናይትድ ኪንግደም የተገኘውን የኮቪድ-19 ዝርያ የተለያዩ ባሕርያትን የቀላቀለ አዲስ ዝርያ አግኝታለች" ሲሉ በአንድ የመንግሥት ስብሰባ ላይ መናገራቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
አዲሱ የቫይረስ ዝርያ ቀድሞ ከነበረው ዝርያ በተለይ በአየር የበለጠ ተላላፊ ነው ብለዋል ሚኒስትሩ።
ቫይረሱ ሊገኝ የቻለውም አዲስ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ላይ ምርመራ ከተደረገ በኋላ መሆኑን ሚኒስትሩን ጠቅሶ የኦንላይን ጋዜጣው ቪኤንኤክስፕረስ አስነብቧል።
ለአዲሱ ዝርያ በቅርቡ መለያ ( ኮድ) እንደሚሰጠውም ሚኒስትሩ አክለዋል።
ቢ.1.617.2 የሚል መለያ የተሰጠውና ባለፈው ጥቅምት ወር ለመጀመሪያ ጊዜ በሕንድ የተገኘው ዝርያ በዩናይትድ ኪንግደም ከተገኘው 'ኬንት' ቫይረስ የበለጠ ተላላፊ ነው።
እንደ ባለሙያዎች ከሆነ በዩናይትድ ኪንግደም የተገኘው ኬንት የተሰኘው ቫይረስ ቢ.1.1.7 በሚል መለያም ይታወቃል።
እንደ ፋይዘር እና አስትራዜንካ ያሉ ክትባቶች ሁለቱንም ዶዝ መውሰድ የሕንዱን የቫይረስ ዝርያ መከላከል እንደሚችል ጥናቶች ጠቁመዋል። ነገር ግን አንዱን ዶዝ ብቻ መውሰድ የመከላከል አቅሙ እንዲቀንስ ያደርገዋል።
እስካሁን ድረስ አዲስ የሚገኙ የኮሮናቫይረስ ዝርያዎች በበርካታ ሰዎች ዘንድ ከፍተኛ የሆነ ህመም ማስከተላቸውን የሚያሳይ ማስረጃ የለም።
ነባሩ የቫይረስ ዝርያ አደጋው በተለይ እድሜያቸው በገፋ ወይም ተጓዳኝ በሽታዎች ባሉባቸው ሰዎች ላይ ይጠናል።
ነገር ግን ቫይረሱ ተላላፊ እና አደገኛ ሲሆን ባልተከተቡ ሕዝቦች ላይ ከፍተኛ ሞት ሊያስከትል ይችላል።
በቪየትናም በቅርቡ በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍ ብሏል። አገሪቷ ወረርሽኙ ከጀመረ አንስቶ ከ6 ሺህ 700 በላይ ሰዎች በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ግማሽ ያህሉ የተመዘገበው ከሚያዝያ ወር ወዲህ ነው።
እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ እስካሁን ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ አገሪቷ የመዘገበችው ሞት 47 ነው።












