ኮሮናቫይረስ፡ ሙሽሮቹ ኮቪድን ሽሽት ሰማይ ላይ ድል ያለ ሠርግ ደገሱ

የህንድ ሙሽሮች በአውሮፕላን ሰርግ

ሕንዳዊያን ሙሽሮች ቻርተርድ አውሮፕላን ተጠቅመው በሰማይ ላይ ድል ያለ ሠርግ ደግሰው መነጋገርያ ሆነዋል፡፡

በዚህ የሰማይ ላይ የሠርግ ሥነ ሥርዓት 160 እንግዶች ተጠርተው በልተው፣ ጠጥተው ጨፍረው ተበትነዋል ተብሏል፡፡

ሙሽሮቹ ሠርጋቸውን በሰማይ ለማድረግ የተገደዱት በሕንድ ኮሮና ወረርሽኝ በመዛመቱ ይህን ተከትሎ የወጣው ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደቡ ሊያፈናፍናቸው ባለመቻሉ ነው፡፡

በማኅበራዊ የትስስር ገጾች በአያሌው በተጋራው የሠርግ ድግስ ምሥል ላይ እንደታየው እንግዶች በቻርተርድ አውሮፕላን ውስጥ በተጨናነቀ ሁኔታ ሲስተናገዱ ነበር፡፡

ሙሽሮቹ ከሕንድ የታሚል ናዱ ግዛት የመጡ ናቸው፡፡ ቻርተርድ አውሮፕላኑም የተነሳው ከዚያው ነው፡፡

ታሚል ናዱ ግዛት የእንቅስቃሴ ገደቦችን የጣለች ሲሆን ማንኛውም የሕዝብ ስብስብ ከ50 ሰው እንዳይበልጥ የሚያስገደድ ደንብ አውጥታለች፡፡

ይህን የሰማይ ላይ ሠርግ ተከትሎ የሕንድ አቪየሽን ባለሥልጣን አዲስ ምርመራ ጀምሯል፡፡

የሕንድ አቪየሽን ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ለታይምስ ኢንዲያ ጋዜጣ እንደተናገሩት ሠርጉ የተደረገው በስፓይስጄት አውሮፕላን በረራ ውስጥ ነው፡፡

የስፓይስጄት ቃል አቀባይ ለኢንዲያ ኤክስፕረስ እንደተናገሩት ደግሞ ቦይንግ 737 አውሮፕላን ተሳፋሪዎች በአንድ የጉዞ ወኪል የተመዘገቡ ሰዎች ኢሆኑ ከማዱራይ ወደ ባንግሎር እንደሚሄዱ ተደርጎ ነው ትኬት የተቆረጠላቸው፡፡

ቃል አቀባዩ ጨምረው እንዳሉት ተሳፋሪዎቹ በኮቪድ ጥንቃቄ ዙርያ መመርያዎች በግልጽ እንደተብራሩላቸውና ይህን የሚቃረን ተግባርም ሆነ ሠርግ አውሮፕላኑ ላይ እንዲደግሱ አልተፈቀደላቸውም ነበር፡፡

ሕንድ 2ኛ ዙር የኮቪድ ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ እያናወጻት ሲሆን ትናንት በወጣ መረጃ በወረርሽኙ 300ሺህ ዜጎች መሞታቸው ተዘግቧል፡፡

የጤና ባለሙያዎች ግን በሕንድ በኮቪድና ተያያዥ የጤና ውስብስቦች ውስጥ የሞቱ ዜጎች አንድ ሚሊዮን ሊደርሱ ይችላሉ ይላሉ፡፡

ሆስፒታሎችና አስክሬን ማቃጠያዎች ከሚችሉት በላይ ተገልጋይ በመምጣቱ ከፍተኛ ቀውስ ገጥሟቸዋል፡፡

ሕንድ በኮቪድ ተህዋሲ የተያዙ ከ40 ሚሊዮን ዜጎች በላይ ተመዝግበውባታል፡፡

አስክሬኖች ከመብዛታቸው የተነሳ 24 ሰዓት አስክሬንን የማስወገድ ሥራ ሲደረግ ነበር፡፡

ይህም ሟቾችን በተገቢው ሥነ ሥርዓት ግብአተ መሬታቸውን ለመፈጸም ባለማስቻሉ ሬሳዎች በወንዝ ዳርቻ ተጥለው መታየታቸው ሲዘገብ ቆይቷል፡፡

አስክሬንን የማቃጠል ሥነ ሥርዓትን ለማካሄድ ወጪው የናረባቸው ሕንዳዊያን የሟች ቤተሰብ ሬሳዎችን በየወዘንዙ ለመጣል እንደተገደዱም ተስተውሏል፡፡

ይህም የሟቾች ቁጥር በአግባቡ እንዳይቆጠር እንዳደረገና በሕንድ የሟቾች ቁጥር መንግሥት ይፋ ካደረገው አሐዝ በብዙ እጥፍ ሊሆን እንደሚችል ያረጋገጠ ነው፡፡

በሕንድ ለሳምንታት ያህል በቀን በተህዋሲው የሚሞቱ ሰዎች ዕለታዊ አሐዝ በሺዎች የሚቆጠር ሆኖ ቆይቷል፡፡