በኢትዮጵያ ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት ወሰዱ

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Health
ኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ መከላከያ መስጠት በጀመረች በሁለት ወራት ውስጥ ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ክትባት መስጠቷ ታወቀ።
በአፍሪካ በርካታ ሰዎች በኮሮናቫይረስ ከተያዙባቸው አምስት አገራት መካከል አንዱ የሆነችው ኢትዮጵያ የበሽታውን መከላከያ ክትባት መስጠት መጋቢት 04/2013 ዓ.ም ነበር የጀመረችው።
ከሁለት ወራት በፊት በኢትዮጵያ በቀዳሚነት ለህክምና ባለሙያዎች መሰጠት የጀመረው የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት እስከ ትናንት ድረስ ለ1 ሚሊየን 801 ሺህ 175 ሰዎች ደርሷል።
የአገሪቱ የጤና ሚኒስቴር ባወጣው ቅደም ተከተል መሠረት ክትባቱ ለበሽታው በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ ለሆኑና በበሽታው ቢያዙ ከባድ ጉዳት ሊደርስባቸው ለሚችሉ ሰዎች ነው ክትባቱ በቀዳሚነት እንዲሰጥ የተደረገው።
በዚህም መሠረት የጤና ባለሙያዎች፣ ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ ለሆኑና ዕድሜያቸው ከ50 እስከ 60 ሆኖ ተጓዳኝ ህመም ላለባቸው ሰዎች ቅድሚያ በመስጠት ክትባቱ እየተሰጠ መሆኑም ተገልጿል።
ኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት መስጠት ዘመቻዋን የጀመረችው ኮቫክስ ከተሰኘውና የኮቪድ-19 ክትባት ለደሃ አገራት እንዲደርስ ከተመሰረተው ዓለም አቀፍ የድጋፍ ጥምረት ባገኘችው 2.2 ሚሊዮን ብልቃጥ የአስትራዜኒካ ክትባት ነበር።
በአገሪቱ በአገልግሎት ላይ እንዲውል ከአስትራዜንካ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ፍቃድ የተሰጠው የኮሮናቫይረስ ክትባት የቻይናው የሲኖፋርም የተባለው ይገኝበታል።
በኢትዮጵያ ከተለያዩ ምንጮች እስከ መጪው ዓመት ኅዳር 2014 ዓ.ም ድረስ 20 ሚሊዮን ክትባት በማስገባት በመላዋ አገሪቱ ተሰራጭቶ ለሕዝቡ እንዲዳረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ቀደም ሲል ተነግሯል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ መሠረት ለክትባቱ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ባለሙያዎችና የሕብረተሰብ ክፍሎች የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባቱን ማግኘታቸው የተገለጸ ሲሆን፤ የክትባቱ ሥርጭት ወደ ቀሪው ሕዝብ እንዲደርስ እየተደረገ ነው ተብሏል።
የኮሮናቫይረስ ክትባት የመጀመሪያው ዙር ከተሰጠ በኋላ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ሁለተኛው ክትባት የሚሰጥ ሲሆን፤ የመጀመሪያውን ክትባት የወሰዱ ሰዎች ሁለተኛውን ክትባት መውሰድ ይጠበቅባቸዋል።
የአፍሪካ በሽታዎች መቆጣጠሪያ ማዕከል መረጃ እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ 2.5 ሚሊዮን ብልቃጥ የአስትራዜኒካና የሲኖፋርም ክትባቶችን ያገኘች ሲሆን ይህም ከአጠቃላይ ሕዝቧ 1.09 በመቶውን ብቻ የሚሸፍን ነው።
ኢትዮጵያ ከናይጄሪያ ቀጥላ በአፍሪካ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላት ስትሆን በበሽታው የተያዙ በርካታ ሰዎች ካሉባቸው የአህጉሪቱ አምስት አገራት መካከልም ትገኛለች።
በዚህም ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከሞሮኖና ከቱኒዚያ ቀጥላ በአፍሪካ በርካታ በበሽታው የተያዙ ሰዎች የተገኙባት አገር ናት።
ወረርሽኙ በኢትዮጵያ ውስጥ መገኘቱ ከታወቀበት ከመጋቢት 2012 ዓ.ም አንስቶ አስከ ትናንት ቅዳሜ ግንቦት 21/2013 ዓ.ም ድረስ በኢትዮጵያ ከ2.7 ሚሊዮን በላይ የኮሮናቫይረስ ምርመራዎች የተደረጉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም ከ271 ሺህ በላይ ሰዎች ላይ በሽታው ተገኝቷል።
በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ አብዛኞቹ ማለትም ከ230 ሺህ የሚበልጡት ከበሽታው ማገገመቻው የተነገረ ሲሆን 4 ሺህ 143 ሰዎች ደግሞ በበሽታው ሰበብ ለህልፈት መዳረጋቸውን የጤና ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ተቋም መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያ የበሽታውን መስፋፋት ለመቆጣጠር ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ ካልጣሉ የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ስትሆን፤ ነገር ግን በርካታ ታማሚዎች ከተገኘባቸው አገራት መካከል ትገኛለች።
በተጨማሪም ካላት የሕዝብ ብዛት አንጻር ቁጥሩ ዝቅተኛ ነው ቢባልም ከአህጉሪቱ አገራት መካከል በርካታ ክትባት አግኝታለች። አስካሁንም 1,801,175 ሰዎች የወረርሽኙን መከላከያ ክትባት ማግኘታቸው ተነግሯል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽን በዓለም ዙሪያ ከተስፋፋበት ጊዜ ጀምሮ ከ169 ሚሊዮን 598 ሺህ በላይ ሰዎች በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም 3 ሚሊዮን 526 ሺህ በላይ ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል።
በሽታው ዓለምን ካዳረሰ ከአንድ ዓመት በኋላ በሽታውን ይከላከላሉ የተባሉ በርካታ ክትባቶች ይፋ ደርገው ጥቅም ላይ እየዋሉ ሲሆን አስካሁን ድረስ ከ1 ቢሊየን 834 ሚሊዮን ሰዎች በላይ ተከትበዋል።













