ኮሮናቫይረስ፡ ስለኮቪድ-19 ክትባት ማወቅ ያለብን ወሳኝ ነጥቦች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ብዙ አገራት ሩጫ ላይ ናቸው፡፡ መጀመርያ ክትባቱን እጃቸው ለማስገባት ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ቶሎ ብለው ለሕዝባቸው ለማደል፡፡
በተለይ ያደጉት አገራት ትንፋሽ አጥሯቸዋል፡፡ ለድል ጓጉተዋል፡፡ ኮሮና የሚባል ጠላት ምጣኔ ሀብታቸውን ብቻ ሳይሆን ሕዝባቸውን እየጨረሰ ነው፡፡
ፖለቲከኞች በዚህ ጦርነት ውጤት ካላመጡ ሕዝባቸው አንቅሮ ይተፋቸዋል፡፡ ለክትባት ‹መስገብገባቸው› ከዚህ የሚመነጭ ነው፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ‹እንተሳሰብ እንጂ ጎበዝ› የሚል ይዘት ያለው መግለጫ ለማውጣት የተገደደውም ለዚሁ ነው፡፡
ድሀ አገራት ለጊዜው የበይ ተመልካች ሆነዋል፡፡
ቢሆንም ግን ክትባቱ ወደነሱም እየመጣ ነው፡፡
ዓለም አንድ መንደር በሆነችበት ሁኔታ እንዴት ነው አንድ አገር ሕዝቡን ብቻ ስላስከተበ ከስጋት ነጻ የሚሆነው?
እስራኤል 9 ሚሊዮን ሕዝቧን ለማስከተብ የጀመረችው ፈጣን እርምጃ እስከአሁን ግማሽ ሚሊዮን ሕዝቧን አዳርሷል፡፡
ሆኖም ግን ወረርሽኙ ጋብ አላለም፡፡ ገና ከአሁኑ ለምን የሚሉ ጥያቄዎች መነሳት ጀምረዋል፡፡
ውጤት ለማየት ግን ጊዜ ይፈልጋል፡፡
ክትባቱን አንድ ሰው በተወጋበት ቅጽበት ለኮቪድ ተህዋሲ ራሱን ተከላካይ ያደርጋል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡
የሚከተሉት ነጥቦችን መረዳት ለክትባቱ ይበልጥ እናድናውቅ ይረዳል፡፡
ክትባት ምንድነው?
ክትባት ማለት ለአንድ ኢንፌክሽን፣ በሽታ ወይም ተህዋሲ ሰውነታችን እንዲከላከል ሰራዊት የሚያዘጋጅ ጠብታ ነው፡፡
ክትባት በይዘቱ ሙትት ያለ፣ ወይም የተዳከመ የተህዋሲ ቅንጣትን የያዘ ሊሆን ይችላል፡፡
ይህም ማለት በሽታውን፣ ተህዋሲውን ራሱ ነው የምንወጋው ማለት ነው፡፡
ወይም ደግሞ በሽታው በሽታ እንዳያስከትል በሚያስችል ደረጃ ራሱን ለሰውነታችን ብቻ እንዲያጋልጥ አድርጎ ማንነቱን ማሳጣት ማለት ነው፡፡
በዚህ ሂደት የሰውነታችን በሽታ ተከላካይ ሰራዊት ለጠላት ኃይል እንዳያሸረግድ፣ እጅ እንዳይሰጥ፣ እንዲነቃ፣ የማንቃት ትጥቅና ስንቅን የማቀበል ያህል ነው የክትባቱ ሁነኛ ተግባር፡፡

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ክትባት ለሕመም አያጋልጥም፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ሰዎችን ሊያዳክማቸው፣ ወይም መጠነኛ የጎንዮሽ ጉዳት ሊያደርስባቸው ይችላል፡፡
ከነዚህም ምልክቶች መሀል ክንድ ላይ ቁስለት ወይም ደግሞ ጊዝያዊ ትኩሳት የተለመዱ ናቸው፡፡ የጎንዮሽ ጉዳቱ ተፈርቶ መቼስ ከሞት ጋር የሚፋጠጥ አይኖርም፡፡
መልካሙ ዜና ከክትባት በኋላ ለተህዋሲ የማይበገር ሰው መሆን መቻሉ ላይ ነው፡፡
ክትባት ከመድኃኒትም በላይ የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡ መድኃኒት የተከሰተን በሽታ ለማጥፋት ነው ቀን ተሌት የሚተጋው፣ ክትባት ግን በሽታውን መጀመርያውኑ ያመክናል፡፡
ሲዲሲ ክትባቶች ችግር የለባቸውም ባይባልም ትሩፋታቸው ከችግራቸው እጅግ የበዛ ነው ይላል፡፡
ክትባቶች ከመሰራጨታቸው በፊት በእንሰሳት ላይ ይሞከራሉ፣ በቤተ ሙከራ ይሞከራሉ፣ በጥቂት ሰዎች ይሞከራሉ፣ በብዙ ሰዎች ይሞከራሉ፤ በጊዜ ሂደት ይጠናሉ፡፡
ይህን ሁሉ ሂደት እንዲያልፉ የሚደረጉት የሰው ልጅ ላይ የሚያደርጉትን ጉዳት በትክክልና በይበልጥ ለመረዳት ነው፡፡ ኮቪድ ጊዜ አልሰጥ በማለቱ ግን ይህ ረዥምና ዓመታትን የሚወስድ የሕክምና ምርመራ ሒደት እንዲያጥር ሆኗል፡፡ የስጋቱ ምንጭም ይኸው ነው፡፡
ክትባቶች አስጊ አይደሉምን?
ክትባቶች የተጀመሩት በ10ኛው ክፍለ ዘመን በቻይናዊያን እንደሆነ ይነገራል፡፡
ነገር ግን እስከ 1796 ዓ/ም የአሁኑን ሳይንሳዊ ቅርጽ አልያዘም፡፡
ኤድዋርድ ጀነር ፈንጣጣ ላይ ሲመራመር የተወሰነ የፈንጣጣ ቅንጣት ሰውነትን የመከላከል አቅም አንቅቶ በተሻለ እንደሚያዘጋጅ ተረዳ፡፡
ይህንኑ አረጋገጠና ከ2 ዓመት በኋላ ግኝቱን አሳተመው፡፡ ከዚህ በኋላ በላቲን ቫካ የሚለው ቃል (ትርጉሙ ላም ማለት ነው) ቫክሲን ወደሚል ቃል ተለወጠና ክትባት የዓለም መድኅን ሆነ፡፡
የሰው ልጅ ከፈጠራቸው ድንቅ የሕክምና ግኝቶች ውስጥ ክትባት ዋናው ነው፡፡
ክትባት ባይኖር ኖሮ በዓመት 3 ሚሊዮን ሕዝብ እንደ ቅጠል ይረግፍ ነበር፡፡ የዓለም ሕዝብ ቁጥር ምናልባት አሁን ካለው ግማሽ ሊሆን ይችልም ነበር፡፡
20 የሚሆኑ በሽታዎችን ቀጥ አድርጎ ያቆማቸው ክትባት ነው ይላል የዓለም ጤና ድርጅት፡፡
ክትባቶችን እንዴት ነው አንዱን ከሌላው የምናወዳድረው?
ፋይዘር ባዮንቴክ እና ሞደርና ሁለቱም አሰራራቸው ከተህዋሲው የተወሰነ የጄኔቲክ ኮድ በመቅዳት የተቀመሙ ናቸው፡፡
ይህም ማለት ደካማና ሙትት ያለ አንቲጀን ወስዶ ክትባት ከመስራት ይልቅ ሰውነታችንን በጄኔቲክ ኮድ አማካኝነት በተህዋሲው የላይኛው ክፍል የሚገኙ በሽታ አምጪ ተህዋስ ክፍሎችን እንዲያውቅና እነሱን ድምጥማጣቸውን የሚያጠፋ ፕሮቲን እንዲያመርት ነው ያደረጉት፡፡
የኦክስፎርዱ አስትራዜኒካ ትንሽ አሰራሩ ይለያል፡፡
ሳይንቲስቶች ይህን ክትባት የቀመሙት ትንሽ የተለወጠ ቺምፓንዚን የሚያጠቃ የጉንፋን ተህዋሲን በቤተሙከራ አዘጋጅተው ከዚያ የኮቪድ 19 የጄኔቲክ ኮድ ላይ ጨመሩት፡፡
በውጤት ደረጃ ሁሉም ተቀራራቢ ናቸው፡፡ አሜሪካና ብሪታኒያ ፈቅደዋቸዋል፡፡
ሜክሲኮ፣ ቺሌ፣ ኮስታሪካ ፋይዘርን ለሕዝባቸው እየሰጡ ነው፡፡ ብራዚል ደግሞ ለአስትራዜኒካ እና ለሲኖቫክ ፍቃድ ሰጥታ ሕዝቧን እየከተበችው ነው፡፡
ሌሎች የኮቪድ ክትባቶች አሉ?
ከአስትራዜኒካና ሞደርና እንዲሁም ፋይዘር ሌላ ክትባቶች አሉ፡፡
ለምሳሌ የቻይናው ሲኖቫክ የሚያመርተው ኮሮናቫክ አለ፡፡ በቻይና፣ በሲንጋፖር፣ በማሊዢያ፣ በኢንዱኒዢያ፣ በፍሊፒንስ ተግባር ላይ ውሏል፡፡
ሕንድ ደግሞ ኮቫክሲን የሚባል ባራት ባዮቴክ የሰራው አገር በቀል ክትባት ጀምራለች፡፡
ሩሲያ ስፑትኒክ የሚባል የራሷን ክትባት ለሕዝቧ እየሰጠች ነው፡፡ በአርጀንቲና 300ሺህ የስፑትኒክ ቅንጣት ለሕዝብ እየተከፋፈለ ነው፡፡
የአፍሪካ ኅብረት 270 ሚሊዮን ቅንጣት ደርሶታል፡፡ ክትባቱ ፋይዘር፣ አስትራዜኔካ እና ጆንሰን ጆንሰንን ያካተተ ነው፡፡
ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ገና ሙከራውን ያላገባደደ ክትባት ነው፡፡
ይህ 270 ሚሊዮን ቅንጣት ባለፈው ከተሰጠ 600 ሚሊዮን ቅንጣት ተጨማሪ መሆኑ ነው፡፡ ይህን የሚያስተባብረው ኮቫክስ ዓለም አቀፍ የትብብር ጥምረት ነው፡፡ ይህ ጥምረት ለድሀ አገራት ክትባቱ እንዲደርስ ከዓለም ጤና ድርጅትና ከቫክሲን አሊያንስ ጋር በጥምረት የሚሰራ ነው፡፡
ክትባቱን መውሰድ ይኖርብናል?
ክትባቱን ግዴታ ያደረገ አገር እስከአሁን የለም፡፡
ነገር ግን ክትባቱን መውሰድ ካለመውሰድ እጅጉኑ ይመከራል፡፡
አንዳንድ ሰዎች ግን በጤና ምክንያት ክትባቱን ባይወስዱ የሚመከሩ ይኖራሉ፡፡
ሲዲሲ ክትባቱን ወስዶ ኮቪድን ማቆም ይቻላል ሲል አትስጉ የሚል መልእክት አስተላልፏል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ይህ ተህዋሲን ለማሽመድመድ የዓለም 70 ከመቶ ሕዝብ መከተብ ይኖርበታል ብሏል፡፡ ይህም ማለት ድርጅቱ ሕዝብ ክትባቱን እንዲወስድ እያበረታታ ነው፡፡
ብዙ ሰዎች ይህ ክትባት እንዲቀመም የሄደበት መንገድና ፍጥነት ያሳስባቸዋል፡፡
ይህ ተገቢ አይደለም አይባልም፡፡ ነገር ግን ሂደቱ እንዲፈጥን የሆነው ከፈጠረው አደጋ በመነሳት ነው፡፡ አሜሪካ 400 ሺህ ዜጎቿን አጥታለች፡፡ በርካታ አገራት በሺ የሚቆጠር ዜጎችን አጥተው ሚሊዮኖች በሞት ስጋት ላይ ናቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ ክትባቱ እንዲፈጥን አለማድረግ አይቻልም፡፡
ያም ሆኖ ሳይንሳዊ ሂደቶች እንዳይጣሱ ሁሉን አቀፍ ጥረት መደረጉን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡
በአጭሩ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ክትባቱን ሲወስዱ የወል ተህዋሲ የመከላከል አቅም ይፈጠራል፡፡ ያን ጊዜ ብቻ ዓለም ወደነበረችበት ጤና ትመለሳለች፡፡


















