ኮሮናቫይረስ ፡ “በ90 ዓመታችን ፍቅር ጀምረን የኮቪድ-19 ክትባት ተሰጠን”

ሊሊ አቦት እና ትሬቨር ሂስት የተዋወቁት ሲደንሱ ነው

የፎቶው ባለመብት, PISHDAAD MODARESSI CHAHARDEHI

የምስሉ መግለጫ, ሊሊ አቦት እና ትሬቨር ሂስት የተዋወቁት ሲደንሱ ነው

ሊሊ አቦት እና ትሬቨር ሂስት የተዋወቁት ሲደንሱ ነው።

ከ30 ዓመት በፊት ብራድፎርድ በተባለ የዳንሰኞች ስብስብ ውስጥ ነበር መጀመሪያ የተዋወቁት።

ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ክትባት ከተሰጣቸው ሰዎች መካከል እነዚህ በ90 ዓመታቸው የፍቅር ግንኙነት የጀመሩት ጥንዶች ይገኙበታል።

ከ30 ዓመት በፊት ከተዋወቁ በኋላ ጥሩ ጓደኛሞች ሆኑ። ሊሊ ከቀድሞው ባለቤታቸው ዊልፍ ጋር፣ ትሬቨርም ከያኔው ባለቤታቸው ሪታ ጋር በየግዛቱ ይዞሩ ነበር።

የትሬቨር ባለቤት ከስድስት ዓመት በፊት አረፉ። የሊሊ ባለቤትም ከ14 ዓመት በፊት በሞት ተለዩ።

ትሬቨር እና ሊሊ ፍቅር የጀመሩት የትዳር አጋሮቻቸውን በሞት ከተነጠቁ በኋላ ነው።

በዚህ ዓመት መባቻ ላይ ሁለቱም 90 ዓመት ሞላቸው። ጓደኞቻቸው ለምን አትጋቡም? እያሉ ይጠይቋቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።

"ሁለታችንም ትዳር መስርተን ነበር። ስለዚህ መጋባት አንፈልግም አልኳቸው" ይላሉ ሊሊ።

ትሬቨር የሦስት ልጆች አባት፣ ሊሊ ደግሞ የሁለት ልጆች እናት ናቸው።

ሊሊ ትሬቨርን በስድስት ቀን በእድሜ ይበልጡታል። ሊሊ አያት፣ ትሬቨር ደግሞ ቅድመ አያት ሆነዋል።

ኮሮናቫይረስ ከተከሰተ በኋላ ዩናይትድ ኪንግደም እንቅስቃሴ ላይ ገደብ ጥላ ነበር።

በዚያ ወቅት ሊሊ እና ትሬቨር በእግር ይንሸራሸሩ ነበር። አንድ ቀን ግን ሊሊ ወድቀው ጎናቸው ላይ ስብራት ገጠማቸው።

ትሬቨር አብረዋቸው ለመኖር የወሰኑት ያኔ ነው። ሐሳቡን የትሬቨርም የሊሊም ልጆች ደግፈውታል።

"መውደቄ አስፈርቶኝ ነበር። 'በየቀኑ ማታ ወደ ቤት ከምትሄድ አብረኸኝ ኑር' አልኩት። በጣም የምንጣጣም ሰዎች ስለሆንን አብሮ ለመኖር ተስማማን" ይላሉ ሊሊ።

የኮሮናቫይረስ ክትባት በቅድሚያ የተሰጠው ለአረጋውያን እና ለጤና ባለሙያዎች ነው። 70 በመቶው ሕዝብ ክትባት ካገኘ የጋርዮሽ በሽታን የመከላከል አቅም (ኸርድ ኢሚውኒቲ) እንደሚዳብር ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ብራድፎርድ ውስጥ ክትባቱን ካገኙ መካከል ሊሊ እና ትሬቨር ይገኙበታል።

ጥንዶቹ ሲከተቡ በቦታው የነበሩት ፕሮፌሰር ጆን ራይት ከዚህ ቀደም በኤችአይቪ፣ በኢቦላና በሌሎችም በሽታዎች ላይ ሠርተዋል።

ብራድፎርድ ውስጥ ክትባቱን ካገኙ መካከል ሊሊ እና ትሬቨር ይገኙበታል

የፎቶው ባለመብት, PISHDAAD MODARESSI CHAHARDEHI

የምስሉ መግለጫ, ብራድፎርድ ውስጥ ክትባቱን ካገኙ መካከል ሊሊ እና ትሬቨር ይገኙበታል

አረጋውያን ለቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚጋለጡ በመጀመሪያ በ80ዎቹ እድሜ ክልል ያሉ ከዚያም በ70ዎቹ እድሜ ክልል ያሉ ክትባት እንደሚሰጣቸው ይናገራሉ።

በአረጋውያን እንክብካቤ መስጫ የሚኖሩና የጤና ባለሙያዎችም ቅድሚያ ከሚሰጣቸው መካከል ናቸው።

እሳቸው በሚሠሩበት ሆስፒታል በየሳምንቱ 195 የፋይዘር ክትባት ብልቃጥ ይደርሳል። በየሳምንቱ 975 ሰዎች ይከትባሉ።

በቀጣይ በየሳምንቱ ክትባት የሚሰጣቸውን ሰዎች ቁጥር ወደ 1,170 ከዚያም ወደ 2,340 የማሳደግ እቅድ አላቸው።

"የማይከተቡ ሰዎች ሞኝ ናቸው"

ሊሊ ዘጠኝ እህቶችና ወንድሞች አሏቸው።

በ14 ዓመታቸው ከትምህርት ቤት ከወጡ በኋላ ልብስ ሰፊ ጋር ይሠራ የነበረውን ዊልፍ ተዋወቁ። በፍቅር ወድቀውም ትዳር መሠረቱ።

እአአ በ1960ዎቹ የፈንጣጣ ወረርሽኝ ሲከሰት፤ እሳቸው በሚኖሩበት ከተማ ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች ክትባት እንደተሰጣቸው ያስታውሳሉ።

"ያኔ ከባድ ጊዜ ነበር። ክትባት ግን ነገሩን አረጋጋው" ይላሉ።

አሁንም የኮሮናቫይረስ ክትባት ሲወስዱ የፈንጣጣ ወረርሽኝ ጊዜ ነው ትዝ ያላቸው።

"የማይከተቡ ሰዎች ሞኝ ናቸው ብዬ አስባለሁ" ይላሉ ሊሊ።

ትሬቨርም የፈንጣጣ ክትባት ሲሰጣቸው ያስታውሳሉ። የ2020ው የኮሮናቫይረስ ክትባት ግን የተሻለ ነው ብለው ያምናሉ።

"በዚህ ጊዜ ክትባት ለመውሰድ የተሰለፍኩት ከዳንስ ቡድን ጓደኞቼ ጋር ዘና እያልኩ ነበር" ሲሉ ይገልጹታል።

በቅርቡ ወደ ዳንስ እንደሚመለሱ ተስፋ ያደርጋሉ።

ባለሙያዎች እንደሚሉት ግን ይህ ተስፋ በቅርቡ እውን የሚሆን አይመስልም።

ክትባቱ በመጀመሪያ ደረጃ የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም ቢያዳብርም፤ የቫይረሱ ስርጭት ይገታል ማለት ግን አይደለም።

እናም ሊሊ እና ትሬዘቨር ሁለተኛውን ዙር ክትባት ካገኙ በኋላም ለበሽታው የመጋለጥ እድል ሊኖራቸው ይችላል።

ከጉንፋን ጋር የተያያዙ በሽታዎች ክትባት አረጋውያን ላይ የሚፈጥረው በሽታን የመከላከል አቅም ለረዥም ጊዜ አይቆይም።

ፕሮፌሰር ጆን "የሆነው ሆኖ ሊሊ እና ትሬቨር በቅርቡ ዳንስ እንደሚጀምሩ ተስፋ አለኝ" ይላሉ።

የጋርዮሽ በሽታን የመከላከል አቅም ዳብሮ፣ ቫይረሱ የሚያስከትለው ጉዳት ቀንሶ የሚያዮበት ቀን ብዙም እንደማይርቅም ያምናሉ።