ኮሮናቫይረስ፡ የኦክስፎርዱን የክትባት ምርምር የሚመሩት ሣራ ጊልበርት ማን ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, University of Oxford, John Cairns
ለኮቪድ-19 ክትባት ለማግኘት ቀን ከሌት የሚለፉት በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የሚሠሩት ፕሮፌሰር ሣራ ጊልበርት “በጣም፣ በጣም በፍጥነት መሥራት አለብን” ይላሉ።
በቫይረሱ ከ16 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሲያዙ፤ የሟቾች ቁጥር ደግሞ ከ650 ሺህ አልፏል።
ፕሮፌሰር ሣራ የሚመሩት ቡድን 300 ተመራማሪዎች የያዘ ነው። በመደበኛ ሂደት አምስት ዓመት ሊወስድ የሚችለውን የክትባት ምርምር በአራት ወር ተስፋ ሰጪ ከሚባል ደረጃ ላይ እንዳደረሱት ይናገራሉ።
የክትባቱ የመጀመሪያ ደረጃ ውጤታቸው አበረታች ነው። ክትባቱ ሰዎች ላይ ሲሞከር በሽታውን መከላከል እንደሚችልም ታይቷል።
"ይህ ማለት ክትባቱ ከዓመቱ ማገባደጃ በፊት ጥቅም ላይ ይውላል ማለት ባይሆንም፤ ከመቼውም በላይ በሽታውን ለመከላከል መቃረባችንን ይጠቁማል።"
ሃያ ሁለት ተስፋ ሰጪ ክትባቶች በሙከራ ላይ ይገኛሉ። ሌሎች 100 በመጀመሪያ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሙከራዎችም አሉ።
ሣራ ጊልበርት ማናቸው?
ፕሮፌሰር ሣራ በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የሚመሩት ምርምር የእንግሊዝና ስዊዘርላንድ ጥምረት ከሆነው መድኃኒት አምራች ድርጅት አስትራዜንካ ጋር በጋራ ይሠራል። ክትባቱ በ1,077 ሰዎች ላይ ሙከራ ተደርጎበታል።
ሙከራ የተደረገባቸው በጎ ፍቃደኞች አንቲቦዲስ [ጸረ እንግዳ አካላት] እና ቲ ሴልስን [በሽታ ለመከላከል ከፍተኛ ሚና ያለው ህዋስ] በማምረት በሽታ የመከላከል አቅም ማዳበራቸው ምርምራቸውን ውጤታማ አስብሎታል።
ይህ ውጤት ይፋ ሲደረግ፤ ፕ/ር ሣራ በአንዴ ታዋቂ ሆነዋል።
ግኝታቸው ምን ያህል በሽታውን ለመከላከል ተቃርበናል? ለሚለው ምላሽ ለመስጠት ገና ቢሆንም፤ ውጤቱ እጅግ ተስፋ ሰጪ ነው።

የፎቶው ባለመብት, University of Oxford, John Cairns
የፕ/ር ሣራን ውጤት ተከትሎ በርካታ መገናኛ ብዙሃን ቃለ መጠይቅ እናድርግልዎት ማለታቸው አልቀረም። ፕሮፌሰሯ ግን አደባባይ ወጥቶ ምስክርነት ከመስጠት ይልቅ በምስጢር መሥራትን መርጠዋል።
በእርግጥ ፕ/ር ሣራ በክትባት ተመራማሪዎች ዘንድ የተከበሩ ሙያተኛ ናቸው።
ከሁለት አስርታት በላይ በቤተ ሙከራ ሲመራመሩ፣ ክትባት ሲፈጥሩና ለምርምራቸው ድጋፍ ሲያሰባስቡ ነበር።
ወጣቷ ሳይንቲስት
ፕ/ር ሣራ የ17 ዓመት ታዳጊ ሳሉ የሕክምና ምርምር ማድረግ እንደሚፈልጉ ቢያውቁም፤ ከምን መጀመር እንዳለባቸው አልተረዱም ነበር።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙት በሥነ ሕይወት ነው። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በባዮኬምስትሪ። ከዚያ በባዩቴክኖሎጂ ምርምር መሥራት ቀጥለዋል።
ስለመድኃኒት ዝግጅት የተማሩትም በዚህ ምርምር ወቅት ነው።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 1994 ላይ በጀነቲክስ፣ በሆስት ፓራሳይትስ እና በወባ ምርምር ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ተቀብሏቸዋል።
ምርምራቸው ወደ ክትባት መፍጠርም አምርቷል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እናትና ሳይንቲስት
ፕ/ር ሣራ በ1998 በአንድ ጊዜ ሦስት ልጆች ወልደዋል። ብዙም ሳይቆዩ ልጆቻቸውን በወለዱ በዓመቱም ዩኒቨርስቲ ማስተማር ጀመሩ።
“የግል ሕይወትና ሥራን ማጣጣም ይከብዳል። የሚደግፍ ሰው ከሌለ የሚሳካ አይመስልም። ለሦስት ልጆቼ ሞግዚት የምከፍለው ከደሞዜ በላይ ነበር” ይላሉ ፕሮፌሰሯ።
አጋራቸው ሥራውን አቁሞ ልጆቻቸውን ለማሳደግ ቢወስንም ቀላል አልነበረም።
“የእናትነት የእረፍት ፍቃድ የነበረኝ 18 ሳምንት ብቻ ነበር። ከሦስት ጨቅላ ልጆች ጋር ነገሮች ከባድ ነበሩ” ሲሉ ያለፉበትን ጊዜ ያስታውሳሉ።
ሳይንቲስት የመሆን ጥሩው ነገር ሁልጊዜም ረዥም ሰዓት መሥራት ግዴታ አለመሆኑ ነው ይላሉ ፕሮፌሰሯ።
የጉንፋን ክትባት የጀመሩት 'ዌልካም ትረስት' በተባለ የለንደን ምርምር ማዕከል ነው። ለምርምር ያገኙት ገንዘብ ለራሳቸው ምርምር መነሻ ሆኗል።
ሦስቱ ልጆቻቻው ሲያድጉ ነገሮች እየቀለሉ መምጣታቸውን ፕ/ር ሣራ ይናገራሉ።
ተስፋ ሰጪው ምርምር
አሁን የቤተ ሙከራ ኃላፊ የሆኑት ፕ/ር ሣራ፤ ልጆቻቸው 21 ዓመት ሆኗቸዋል። ልጆቹ እንደእናታቸው ለመሆን ባዮኬምስትሪ እያጠኑ ይገኛሉ።
ለኮቪድ-19 ክትባት ለማግኘት የሚያደርጉትን ምርምር ልጆቻቸው በንቃት እንደሚከታተሉ ይናገራሉ።
ሦስቱ ልጆቻቸው በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ እየተካሄደ ባለው የኮሮናቫይረስ ክትባት ምርምር ውስጥ በጎ ፍቃደኛ ከሆኑ ሰዎች መካከል ይገኙበታል።
“ከ18 ዓመት እስከ 55 ዓመት የሆኑ ጤናማ ሰዎች በሽታውን የመከላከል አቅም እንዲያዳብሩ ማድረግ አለብን” ይላሉ ሳይንቲስቷ።
ስለ ክትባቱ ሲናገሩም፤ “ከእዚህ በፊት እንደዚህ አይነት ክትባት ብዙ ጊዜ ተጠቅመናል፤ ስለዚህ እንግዳ ነገር ይገጥመናል ብለን አናስብም” በማለት ተስፋቸውን ይገልጻሉ።
አሁን ላይ ትኩረታቸው የቤተ ሙከራ ምርምር እና የክትባቱን ምርት ማፋጠን እንደሆነም ፕሮፌሰር ሳራ ጊልበርት ያስረዳሉ።














