ጤና፡ "ያለ ብልት መወለዴን ያወቅኩ እለት"

የፎቶው ባለመብት, Julian Peter
በርካታ ሴቶች ለየትኛውም ጉዳይ የጤና ማዕከላትን ሲጎበኙ በመጀመሪያ የሚጠየቁት ጥያቄ ከወር አበባ (ፔሬድ) ጋር የተያያዘ ነው።
መቼ ነው ለመጨረሻ ጊዜ የወር አበባችሁን (ፔሬድ) ያያችሁት? የሚል ነው። ከዚያ በኋላ ነው ሌሎች ጥያቄዎችና ምርመራዎች የሚከተሉት። ለ 29 አመቷ ጁሊያን ፒተር ስለ ወር አበባ በተጠየቀችበት እለትም ነው ያለ ብልት፣ ማህፅን፣ መወለዷን ያወቀችው።
ወቅቱም ከአስራ ሁለት አመታት በፊት ነበር፤ ታሪኳን ለቢቢሲዋ አን ጉጊ እንዲህ አጫውታታለች።

ሜየር ሮኪታንስኪ ኩስተር ሃውሰር (Mayer-Rokitansky-Küster-Hauser syndrome (MRKH)) ወይም በአህፅሮተ ቃል አጠራሩ ኤም አር ኬኤች ተብሎ ከሚታወቀው ህመም ጋር ነው የተወለድኩት።
ይህ ህመም ያለባቸው ሴቶች ማህፀን ወይም ብልት አንዳንድ ጊዜ ደግሞ አንድ ኩላሊት ሳይኖራቸው ይወለዳሉ።
አንዲት ሴት ኤም አር ኬኤች አለባት ማለት መቼም ቢሆን የወር አበባ (ፔሬድ) አታይም።
እኔ ያለሁበትን ነገር ስለለመድኩት ምንም መጥፎ ስሜት አይሰማኝም። ብዙዎች ግን ስላለሁበት ሁኔታ በርካታ አስተያየቶችን ይሰጡኛል።
በአንድ ወቅት አንድ ሰው ፀሎት የሚደረግበት ቦታ እንድሄድ ነገረኝ፤ መድኃኒትም ታጘኛለሽ አለኝ።
ሌላ ግለሰብ ደግሞ በተለምዶ ጥንቆላ ይደረግበታል ተብሎ ከሚታወቀው የኬንያዋ ኡካምባኒ ግዛት መሆን አለብሽ አለኝ። እንዲያውም አያትሽ ጠንቋይ ሳትሆን አትቀርም፤ ለዚያ ነው እንዲህ ሆነሽ የተወለድሽው በማለት በድፍረት ተናገረኝ።
በርካታ ሰዎች የፈለጉትን ማለት እንደሚችሉ ይሰማቸዋል። እኔም በርካቶች የሚሉኝን በአንድ ጆሮዬ ሰምቼ በሌላው አፈሰዋለሁ።
ዋናው ነገር ግን የሚሉኝን እንዴት ነው የምወስደው የሚለው ነው። የሚሉኝንማ ከሰማሁ ላብድ ሁሉ እችላለሁ። የሚሉት እውነት እንዳልሆነ ልቦናዬ ያውቀዋል። ስለ ህመሜ ያወቅኩት 17 አመቴ እያለ ነው። ተማሪም ነበርኩ።
እግሬ አብጦ ወደ ሆስፒታል በሄድኩበት ወቅት ዶክተሯ መጀመሪያ የጠዬቀችኝ "መቼ ነው ለመጨረሻ ጊዜ የወር አበባሽን ያየሽው የሚል ነበር" የኔም መልስ ግራ በተጋባ መልኩ ጭራሽ የወር አበባ አይቼ አላቅም አልኩ።

ምርመራቸውንም ጀመሩ። ስካን ሲያደርጉኝም የብልቴ የውጨኛው ክፍል የተዘጋ መሆኑን አሳየ። ብልቴንም ለመክፈት ቀዶ ጥገና ባደርግም ብዙ የተሳካ አልነበረም።
ሌላ ስካን በሚያደርጉበት ወቅት ከብልቴ ጀምሮ መተላለፊያ ቱቦዎች እንዲሁም ማሕፀን እንደሌለኝም ተረዱ።
በዚያንም ወቅት ነው ኤም አር ኬኤች የተባለው ችግር እንዳለብኝ ያወቁት። ሲነግሩኝም በመጀመሪያዋ እለት አለቀስኩኝ፤ ኃዘኔም የመረረ ነበር፤ ለሶስት ቀናትም ያህል አለቀስኩ።
ከዚያም በቃ ተቀበልኩት። 17 አመቴ ነበር፣ ገና ታዳጊም ነኝ፤ ቅድሚያ ለትምህርት ስለሰጠሁም፤ ትምህርት ቤት መመለስ ብቻ ነው የፈለግኩት።
ሆስፒታል የሄድኩት እናቴ ጋር ነበር። አባቴ በህይወቴ ውስጥ የለም። ምርመራውን ስትሰማ ደነገጠች፣ አንዘፈዘፋት። እንደ ማንኛውም ቤተሰብ እናቴም ራሷን የጠየቀችው ምን አይነት ስህተት ፈፅሜ ይሆን? የሚለው ነበር።
'ቀዶ ጥገና ማድረግ አልፈለግኩም ነበር'
ትምህርት ቤት ባዮሎጂ (ስነ ህይወት) ከመማሬ አንፃር ዶክተሯ የምትለው ነገር በሙሉ ገብቶኝ ነበር። ትምህርት ቤት በአስቸኳይ መመለስም ስለምፈልግ ቀዶ ጥገና ማድረግ እንደማልፈልግ ነገርኳት።
ከአስር አመታት በኋላ እዛው ሆስፒታል ተመልሼ ቀዶ ጥገና አደረግኩኝ። የተሳካ ነበር ማለት እችላለሁ።
በቦታው ብልት ባይኖረኝም ብልት መሳይ ነገር ፈጥረው በትንሹ ከፍተውታል። ኤም አር ኬኤች ከሰው ሰው ቢለያይም የኔ አይነቱ ግን ብልት ፣ ማህፀንም ሆነ አንድ ኩላሊቴት የለኝም።
ለኔ ሁኔታዬ ህይወቴን ከመኖር አላዳገተኝም፤ ጣልቃ አይገባብኝም ብል ቀለል ያለ ነው።
ለብዙዎች ግን ስነ ልቦናዊ ጫናው በጣም ከፍተኛ ነው። ሸክም የሆነባቸውም ለአመታት በስነ ልቦናዊ ምክር ማለፍ አለባቸው። ለኔ ሁኔታዬን ከመረዳቴም አንፃር፤ ልጆች እወልዳለሁ ብሎ ማሰብ የማይታለም ነው።
Mayer-Rokitansky-Küster-Hauser
Characterisedby absence of the vagina, cervix and the uterus
Affectsone in 5,000 women
Type 1refers to the absence of reproductive organs
Type 2refers to the absence of, or abnormality with, a kidney
Usually discoveredduring puberty when menstruation does not start

አራት ያህል ጊዜ ስካን ተደርጌ እንቁላል የሚያመርተው የሰውነት ክፍል እንቁልጢ (ኦቫሪስ) እንደሌለኝም ተረጋግጧል።
መውለድ የማይችሉ ሴቶች እንደሚያደርጉት የአይቪኤፍ (በቤተ ሙከራ ውስጥ እንቁላል ከወንድ ዘር ፍሬ ጋር ተዋህዶ ጽንስ የሚፈጠርበት መንገድ ነው) ህክምናን ማድረግ አልችልም። ምክንያቱም ትርጉም የለም፤ መቼም ቢሆን መውለድ አልችልም።
በቃ ያለው ምርጫ ያለሁበትን እውነታ መቀበል ነው። ነገር ግን እንዲህ እንደሚባለው ቀላል አይደለም።
እንደ ሌሎች ሴቶች አለመሆኔን ስረዳ ሁኔታውን ከበድ ያደርገዋል። በእውነቱ የሚያዋራ፣ የሚያዋይ ሰው ያስፈልጋል። ደ
ግነቱ እዚሁ ኬንያ የኔ አይነት ተመሳሳይ ሁኔታ ያለባቸው ሰዎች አግኝቻለሁ። ያለፍንበትን፣ እየሆንን ስላለው ነገር እናወራለን። ቀድሜም ራሴን ስላሳመንኩኝ ደህና ነኝ፤ ራሴን ተቀብያለሁ።
ለፍቅረኛስ እንዴት ይነገራል?
የወንድ ጓደኞች ማለቴ ፍቅረኞች ኖረውኝ ያውቃሉ። ሆኖም ነገሮች ጠንከር ከማለታቸውና ወደ ሌላ ከመሄዱ በፊት ቁጭ አድርጌ ስለ ሁኔታዬ አስረዳቸዋለሁ።
ከፈለጉ ይቀበሉት ነው። ያው ሰው ስንባል አስቸጋሪ ነን። ወንዶቹ በነገርኳቸው ወቅት ወዲያው ነው የሸሹኝ። አንዳንዶቹ ደግሞ ሆን ብዬ ውሸት ፈጥሬ የነገርኳቸው ነው የመሰላቸው። እነሱን ለማራቅ የፈጠርከትም ምክንያት ነው ያሉንም ነበሩ።
በአሁኑ ሰዓት የፍቅር ጓደኛ የለኝም፤ ያው የአምላክ ስራ ስለሆነ ተቀብየዋለሁ።
ወሲባዊ ግንኙነት ሲመጣ ከሁለት አመታት በፊት ብልት በቀዶ ጥገና ተሰርቶልኛል። ሆኖም እስካሁን ወሲባዊ ግንኙት ለማድረግ ዝግጁ አይደለሁም። ልጅ መውለድ ከፈለግን ሁልጊዜም ቢሆን ማሳደግ እንደምችል ባውቀውም፤ ለማግባትም እንዲሁ ዝግጁነት የለኝም።
ታሪኬንም ለማጋራት ከአስር አመት በላይ ወስዶብኛል።
በጣም ብዙ ሰዎች ስለ ኤም አር ኬኤች አያውቁም፤ ግንዛቤም መፍጠር የኔ ኃላፊነት ነው ብዬ ስላሰብኩ ነው ለመንገርም የወሰንኩት

የፎቶው ባለመብት, Julian Peter
በመጀመሪያ ደረጃ ምክሬ ለቤተሰቦች ነው። ከኤም አር ኬኤች ጋር የተወለዱ ልጆችን ቀዶ ጥገና ለማስደረግ እንዳይቻኮሉ ነው የምመክረው።
ካደጉ በኋላ ይደርሳል። ሁኔታቸውን ከተረዱት በኋላ፣ ሄደቴንም ገምግመው ካጤኑ በኋላ መሆን አለበት።
ምክንያቱም ቀዶ ጥገናው የተወሳሰበ ነው፤ ረዥም ጊዜም የሚወስድ ነው።
በጣም ከፍተኛ ህመም ስላለውም ልጆች ያሉበትን ሁኔታ ለመረዳት ይከብዳቸዋል።
እንደ ወላጅም ስለ ኤም አር ኬኤች የተፃፉ ነገሮችን በደንብ ማንበብ አለባችሁ፤ በጥልቀትም ልታውቁ ይገባል።
ሴቶች ልጆቻችሁ ሲያድጉና ሁኔታውን ሲረዱ የሚደርስባቸውን አድልዎና መገለል እንዴት መጋፈጥ እንዳለባቸው ዝግጁ ልታደርጓቸው ይገባል።
የናንተ ድጋፍ በፅኑ ያስፈልጋቸዋል።
ኤም አር ኬኤች ያለባቸው ቡድን ስላለን እርስ በርስ እንደማመጣለን፤ ያሉትን ፈተናዎችም እየሰማን ምክር እንለጋገሳለን።
ከኛ ውስጥ ያገቡም አሉ፤ ልጅ እንዲወልዱም ከፍተኛ ጫና ከአማቾቻቸው ይደርስባቸዋል። ወንድ ናችሁ ተብለውም የተነገራቸውም አሉ።
ቢሆንም ተደጋግፈን ራሳችንን እናበረታታለን። ጉዞው ከባድና ፈታኝ ቢሆን እንዲህ አይነትና ድጋፍ ማግኘታችን ዕድለኛ ነን።












