ኮሮናቫይረስ ፡ የኮቪድ-19 ክትባትን ለማግኘት ፖለቲካዊ ጦርነት ያጋጥም ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለዓለም ስጋት ሆኖ በቀጠለበት በዚህ ወቅት የማንነካ ነን የሚሉ ታላላቅ አገራትን እያብረከረካቸው ይገኛል። የሰው ልጅ ደረስኩበት የሚለውን የሳይንስ ልህቀት ፈትኗል፤ እየፈተነም ይገኛል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እስካልተገታ ድረስ የዓለም ሕዝብ ወደቀደመው ህይወት መመለስ አይችልም።
እናም ቀጣዩ እሽቅድምድም የኮቪድ-19 ክትባትን ማግኘት ሆኗል።
በርካታ ኃያላን አገራት አሜሪካ፣ ቻይና ሩሲያና ዩናይትድ ኪንግደም ሙሉ ትኩረታቸውን ወደ ክትባቱ በማዞር ሳይንሳዊ ምርምሮቻቸውን እየፈተኑ ይገኛሉ።
በርካታ ሳይንቲስቶቻቸውን በማሰማራትና የምርምር ማዕከላትም ላይ በርካታ መዋዕለ ንዋይም እያፈሰሱ ይገኛሉ።
ምንም እንኳን በዚህ ሰዓት በሙከራ ላይ ካሉ ክትባቶች መካከል የትኛው ቀድሞ ይደርሳል የሚለውን መገመት ቢከብድም፤ የበለፀጉት አገራት በመቶ ሚሊዮን ዶላሮች እያወጡ ከላብራቶሪዎች እነዚህን ክትባቶች እየገዙ ይገኛሉ።
በዚያም መንገድ አቅርቦታቸውንም እየጨመሩ ነው።
ለምሳሌ ዩናይትድ ኪንግደም የክትባት ሙከራውን ከሚያቀርቡት አስትራዜንካ፣ ፋይዘርና ባዮንቴክና ቫልኔቫ ከተባሉት ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ፈርማለች።
እነዚህ ስምምነቶች ሁለት አገራትን ያካተቱ ሳይሆኑ በኩባንያዎችና በአገራት ወይም በግለሰቦች መካከል የሚፈፀሙ ክስተቶች በመሆናቸውም "የክትባት ብሔርተኝነትም" እየተባለ ነው።
ለክትባቶች የሚደረገውን እሽቅድድም በተመለከተ ቢቢሲ ካውንስል ኦን ፎሬይን ሪሌሽንስ (የውጭ ግንኙነት ጉባኤ) ጥናት ማዕከል ፕሬዚዳንት የሆኑትን ሪቻርድ ኤን ሃስን አናግሯል።
ግለሰቡ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮም በፖሊሲ አውጪ ዳይሬክተር እንዲሁም የአፍጋኒስታን እጣፈንታ ፕሮግራምና አየርላንድንም በተመለከተ ልዩ መልዕክተኛና አስተባባሪ ሆነው ሰርተዋል።

በባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ እነዚህ ኃያላን አገራት የተለያዩ የክትባት ሙከራዎች ዕውቅና ከማግኘታቸው በፊት እየሸመቱ ይገኛሉ። እሽቅድምድም ይመስላል። ይህንንም በማስመልከት እርስዎም "የክትባት ብሔርተኝነት" እየታየ፣ እየጎላ ነው በሚል ፅፈዋል። እንዲሁም ጥፋት ሊያስከትል እንደሚችል አስፍረዋል። እንዴት እንዲህ ሊሉ ቻሉ?
በርካታ አገራት የኮቪድ 19 ክትባትን የግላቸው ለማድረግ እየተሽቀዳደሙ ነው። አገራቱ ማንም እንዳይቀድማቸው በገፍ እየሸመቱም ይገኛሉ። ይሄ መቅረት የሚችል ብሔርተኝነት ነው።
መንግሥታት ከሁሉ በፊት የራሳቸውን አገራት በማስቀደምም ላይ ይገኛሉ፤ ምክንያቱ ግልፅ ነው። እነዚህ መሪዎች ለዜጎቻቸው የኮሮናቫይረስን ወረርሸኝን በመግታትና ክትባቱንም አቅርቡ በሚል ከፍተኛ ጫና ደርሶባቸዋል።
ችግሩ ግን እነዚህ አገራት ብቻ በበላይነት ክትባቶቹን ከያዟቸው ቢሊዮኖችን ያገላል፤ አይደርሳቸውም። በተለይም ተጋላጭ ለሆኑት ማኅበረሰብ አለመድረሱ ቀውስን የሚፈጥር ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ክትባት ብሔርተኝነትን ሙጭጭ ብለው ለያዙት ለእነዚህ አገራት መንግሥታትም ውጤቱ አሉታዊ ነው።
በእነዚህ አገራት በኮሮናቫይረስ የተጠቁ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ቢኖራቸው በሽታው በዚያው አይገታም። ዓለም ካለችበት የግሎባላይዜሽን ሥርዓት በሽታው ይዛመታል፤ ወደ ሌሎች አገራትም መሰራጨቱ ስለማይቀር ነው።
በአሁኑ ወቅት ከክትባቶቹ ጀርባ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ የሆነ የብልጦች አካሄድ ላይ የተመሰረተ ጨዋታ ላይ ናቸው። በሆነ መንገድ ዓለም አቀፋዊ ስምምነት ላይ መደረስ ካልተቻለ ቀውስ ይፈጠራል።
በአገራቱ ያለውን የፖለቲካ ጫና በተወሰነ መልኩ እረዳዋለሁ። ለአንድ መንግሥት ሌሎች አገራትን መርዳት አለብን እንዲሁም በተመሳሳይም ራሳችን መርዳት አለብን የሚለውን አብሮ ማስኬድ ፈታኝ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የኮሮናቫይረስ ክትባት ፖለቲካዊ ጦርነት ላይ ነን ወይስ ሊገጥመን ይችላል?
ጦርነት ባልለውም ለክትባት የሚደረግ ውድድርና እሽቅድምድም እለዋለሁ። ሁሉም ቀዳሚ መሆን ይፈልጋል። አንዳንዶች ለንግድና ትርፍን ለማጋበስ ሲሆን በርካቶች ደግሞ ፖለቲካዊ ምክንያቶችን ከጀርባው ሰንቀዋል።
ዋናው ችግሩ ከዚህ በበለጠ በርካቶች በቫይረሱ የሚያዙ ከሆነ መላው የዓለም ሕዝብም ተጋላጭ ነው። የዚህም በሽታ ዋነኛ አስተማሪነቱ ይሄ ነው።
አንድ አገር ከሁሉ ቀድማ የኮሮናቫይረስ ክትባቱን ብታመርትም በሌሎች አገራት ላይ ጥገኛ መሆኗ አይቀርም።
ምክንያቱም ምርቱን ለማምረት የተለያዩ ግብዓቶችን ከተለያዩ አገራት መፈለግ አይቀርም። የየትኛውንም አገር ድጋፍ ሳያስፈልገኝ መቶ በመቶ ራሴን የቻልኩኝ አገር ነኝ ማለት የሚችል ያለ አይመስለኝም።
በክትባቱም እንደዚሁ ነው፤ ከሌሎች አገሮች ለክትባቱ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ሳልጠቀም መቶ በመቶ በራሴ ብቻ የኮሮናቫይረስ ክትባትን መስራት እችላለሁ የሚል የለም።
ታዲያ መፍትሄው ምንድነው? አገራቱ ስምምነትስ ላይ እንዴት ሊደርሱ ይችላሉ?
ኃላፊነት የሚሰማው መንግሥት ልክ እንደ ኢንሹራንስ ፖሊስ ስምምነት ላይ ለመድረስ ይሞክራል። ይሄ ስምምነትም ዋነኛው ነገር ምንድን ነው አንድ አገር የኮሮናቫይረስ ክትባትን ባያመርት የተለያዩ አገራት ከክትባቱ የሚጠቀሙበትን መንገድ መቀየስና ማከፋፈል ያስፈልጋል።
ይህ ደግሞ ዓለም አቀፋዊ ስምምነት ያሻዋል። ክትባቱ ከተገኘ በኋላ መንግሥታት ለመከፋፈል መንገድ ለማበጀት ስምምነት ላይ መድረስ አለባቸው። ለምሳሌ አንድ መንግሥት ግማሹን ክትባት ለራሱ ሕዝብ ካዋለ ግማሹን ለተቀረው ዓለም የሚሰጥበት መንገድን ማሰብ አለበት።
በዚህም መንገድ ሁሉም ተጠቃሚነቱ ይረጋገጣል። እንደነዚህ አይነት ስምምነቶች ላይ መደረስ ከተቻለ የተለያዩ አገራት ክትባቱን ባያመርቱም እንኳን ለሕዝባቸው ክትባቱን ማግኘት ይችላሉ ማለት ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እንደነዚህ አይነት ስምምነቶች ላይ የሚደረስ ይመስልዎታል?
አይሆንም፤ የሚደረስ አይመስለኝም። በርግጠኝነት አሜሪካ፣ ቻይና የመሳሰሉት አገራት ክትባቱን በመጀመሪያ የሚያገኙት እነሱ እንደሆኑ ልበ ሙሉ ናቸው።
እናም ከዚህ ክትባት ቅድሚያ መጠቀም ይፈልጋሉ፤ ይሄንንም ለዓለም ሕዝብ አሳልፈው መስጠት አይፈልጉም። ቅድሚያ ለሕዝባቸው እንደሚሉም እርግጠኛ ነኝ።
በአሁኑ ሰዓት ብሔራዊ ስሜት በከፍተኛ ሁኔታ የጎለበተበት ወቅት ነው። ቅድሚያ ለእኔ! ለብቻዬ የሚሉ ሁኔታዎችም ይሰማሉ።
መንግሥታት ከሌሎች አገራት ጋር የኮሮናቫይረስ ክትባትን ለመከፋፈል ስምምነት ላይ ቢደርሱ በአገራቸው ፖለቲካዊ ክፍተት ይፈጠራል፤ እንዲሁም ጨና ይፈጠርብናል ብለው ያምናሉ፤ ሊሆንም ይችላል።
ከዚህም በተጨማሪ የኮሮናቫይረስ ክትባትንም ለማግኘት የመጀመሪያ መሆን በራሱ ድል የማድረግ ስሜት አለው፤ ጠንካራ ምልክትም ነው፤ በተለይ የፖለቲካ ኃይልንን ለመቆጣጠር።
ክትባቱን በመጀመሪያ ማግኘት የራሱ ጥቅሞች አሉት። ነገር ግን አሁን ያለውን አካሄድ ስንመለከተው በርካታ ክትባቶች ይፈጠራሉ እነዚህ ክትባቶች ደግሞ መፍትሄ አይሆኑም።
ሁሉም ክትባቶች የራሳቸው ውስንነት አላቸው። ምን ያህል ሰዎችን መርዳት ይችላሉ እንዲሁም ከጎንዮሽ ጉዳቶችና ሌሎችም ነገሮች ተያይዞ ማለት ነው።
ይህን ውይይታችንን የበለጠ አስገራሚ የሚያደርገው ደግሞ ሰዎች ክትባቱ ሲገኝ የወርቅ ሜዳልያ እንደተገኘ ያህል ሊቆጥሩት እንደሚችሉ ሳስብ ነው። ብዙዎች የክትባቱ መገኘት የኮቪድ-19 መፍትሄ ነው፤ አበቃ አከተመለትም ሊሉ ይችላሉ።
ነገሩ ግን እንደዚያ አይደለም። የክትባቶችን ታሪክ ብናይ ለበሽታዎች ክትባት ሲገኙ የተወሰነውን ሰው ነው መርዳት የሚችሉት ሁሉንም አይደለም። ለተወሰነ ጊዜም የሆነውን ማኅበረሰብ ክፍል ይረዳሉ። ያልተፈለገ የጎንዮሽ ጉዳትም ያስከትላሉ ብዙዎች አንወስድም ብለው ያቆሙታል።
የእኔ ግምት አንድም ይሁን ሌሎች ክትባቶች ቢገኙም የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት አሁን የምናደርጋቸውን ጥንቃቄዎች አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ ጭምብል ማድረግ እንዲሁም እጅን በተደጋጋሚ መታጠብና በፀረ ተህዋሲያን ማፅዳቱን የምንቀጥልበት ይሆናል።
በርካቶች ክትባቱ ሲገኝ የሚኖረውን ሚና ያገዝፉታል ወይም ያዳንቁታል። ክትባቱ ሁላችንንም አያድነንም። ክርክሩ በመርህ ደረጃ ልክ ነው። እውነታውን ካየነው በአሁኑ ሰዓት አገራት ክትባቶችን የራሳቸው ለማድረግ ነው እንጂ ለሌሎች ሲያስቡ አይታይም።
በአገራቱ መካከል ስምምነቶች መደረስ ካልቻሉስ ዋናው አደጋ የሚሆነው ምንድን ነው?
ዋናው አደጋማ የሰብዓዊ ቀውስ ይፈጠራል። በርካታ አገራት የምጣኔ ሃብትም ሆነ ለጤና ሥርዓቱ ምላሽ መስጠት አይችሉም። ክትባቶቹንም በብልህነት ካልተጋራናቸው ቫይረሱ ዓለማችንን ሊያጥለቀልቃት የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠራል። በርካቶችም ተጋላጭ ይሆናሉ።














