ኮሮናቫይረስ፡ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ መምህር በቫይረሱ ሕይወታቸው አለፈ

የፎቶው ባለመብት, Axum University
በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የሕብረተሰብ ጤና ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶ/ር ፍሰሃየ አለምሰገድ በኮሮናቫይረስ ተይዘው የህክምና እርዳታ ሲደረግላቸው ቆይተው ዛሬ ሕይወታቸው ማለፉን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኪሮስ ጉዑሽ ለቢቢሲ ገለፁ።
ሕክምና እየተከታተሉ በሚገኙበት የመቀለ የኮሮና ታማሚዎች ማገገሚያ ማዕከል ሕይወታቸው ማለፉንም የገለፁት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት፤ ከእርሳቸው ጋር የቅርብ ንክኪ ያላት አንድ ግለሰብም በቫይረሱ መያዟ ተረጋግጦ ሕክምና እየተደረገላት እንደሚገኝ አክለዋል።
በዩኒቨርስቲው የተለያዩ ግቢዎች በሚገኙ ለይቶ ማቆያዎች የሚሰሩ 1 ሹፌር፣ 2 የፀረ ተህዋስ ኬሚካል ርጭት ባለሙያዎች፣ 23 የፅዳት ሰራተኞች እና 10 የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ መያዛቸውን በዩኒቨርሲቲው ኮርፖሬት ኮሚኒኬሽንና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተወካይ ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ዘ ሚካኤል ገልፀውልናል።
ዶ/ር ፍሰሃየ ከመምህርነት ባሻገር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የኮሮናቫይረስ ፈጣን ግብረ መልስ ቡድን መሪ በመሆን እንዲሁም በትግራይ ክልል ጤና ቢሮ በኮሮናቫይረስ መረጃ ትንተና እና ትንበያ ክፍል እየሰሩ እንደነበር ዶ/ር ኪሮስ ገልፀውልናል።
ዶ/ር ፍሰሃየ አለምሰገድ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በመምህርነት፣ በተመራማሪነትና በሙያ አማካሪነት ለ17 ዓመታት አገልግለዋል።
ከመስከረም 2012 ዓ.ም ጀምሮ ወደ አክሱም ዩኒቨርሲቲ በመዛወር በዩኒቨርሲቲው የሕብረተሰብ ጤና ትምህርት ክፍል ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
ፕሬዚዳንቱ ዶ/ር ፍሰሃየ በእናቶችና ህፃናት ህክምና፣ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች፣ በስነ-ምግብ፣ በወባ፣ በኤች አይቪ ኤድስና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን ጨምሮ በሌሎች የሕብረተሰብ ጤና ዘርፎች ከ50 በላይ ችግር ፈቺ ጥናቶችን በታዋቂ ጆርናሎች ማሳተማቸውን አክለዋል።
የቀብር ሥነ ስርዓታቸውም ነገ በመቀለ ከተማ እንደሚፈፀም ዶ/ር ኪሮስ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
በትግራይ ክልል እስካሁን በተደረገ 25 ሺህ 579 ናሙናዎች ተመርምረው 1016 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን የ5 ሰዎች ሕይወት አልፏል።













