የኮሮናቫይረስ ታማሚው ሆስፒታል ውስጥ ሌላ ታማሚን ገደለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ፣ ካሊፎርንያ ውስጥ በኮሮናቫይረስ ተይዞ ሆስፒታል የነበረ ግለሰብ ሌላ ቫይረሱ ያለበትን ታማሚ ገደለ።
የ37 ዓመቱ ግለሰብ ባለፈው ሳምንት ታማሚውን የገደለው በኦክስጅን መያዣ ታንክ ደብድቦት ነው።
ግለሰቡ በግድያ እና በጥላቻ ወንጀል ተከሷል።
ጀሲ ማርቲኔዝ የተባለው ግለሰብ የ82 ዓመት አዛውንት በኮሮናቫይረስ ተይዘው እሱ የሚገኝበት የሆስፒታል ክፍል ውስጥ ከገቡ በኋላ ነው ግድያውን የፈጸመው።
ለሎስ አንጀለስ ፖሊስ በሰጠው ቃል መሠረት አዛውንቱ የሆስፒታሉ ክፍል ውስጥ እየጸለዩ ስለነበረ ተበሳጭቶባቸዋል።
አዛውንቱ በኦክስጅን ታንክ ከተመቱ በኋላ በቀጣዩ ቀን ሕይወታቸው አልፏል።
ፓሊስ እንዳለው፤ ሁለቱ ግለሰቦች በተመሳሳይ የሆስፒታል ክፍል ውስጥ ሕክምና ሲደረግላቸው ነበር። ከዚያ በፊትም አይተዋወቁም።
አንቲሎፕ ቫሊ በተባለውና በደቡብ ካሊፎርንያ በሚገኝ ሆስፒታል ሕክምና ሲደረግለት የነበረው ጀሲ "አዛውንቱ ሲጸልዩ ተበሳጨና በኦክስጅን ታንክ ገደላቸው" ሲል ፖሊስ መግለጫ አውጥቷል።
ከግድያ በተጨማሪ የጥላቻ ወንጀል እና አረጋውያንን የማሰቃየት ክስም ተመስርቶበታል።
ካሊፎርንያ ውስጥ በስድስት ሳምንት ብቻ አንድ ሚሊዮን ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። ሆስፒታሎች ህሙማንን ለማስተናገድ እየተጣጣሩም ነው።
ወረርሽኙ ከጀመረ ወዲህ በግዛቲቱ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።
ሆስፒታሎች የጤና ባለሙያዎች እጥረት ስለገጠማቸው ከአውስትራሊያ እና ታይዋን 3000 ባለሙያዎች ለመውሰድ አቅደዋል።
የካሊፎርንያ የጤና ቢሮ ጸሐፊ ዶ/ር ማርክ ጋሊ በዚህ ወር መጨረሻ ለህሙማን አልጋ ላይኖር እንደሚችል ተናግረዋል።
አገረ ገዢው ጋቪን ኒውሰም ዜጎች ከቤት እንዳይወጡ አዘዋል። እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ አገልግሎቶች ውጪ ያሉ ተቋሞችም ተዘግተዋል።












