ትራምፕ ለአሜሪካውያን 600 ሳይሆን 2 ሺህ ዶላር ነው የሚገባቸው አሉ

ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በወረርሽኙ ምክንያት ገቢያቸው ለተዳከመ ዜጎቻቸው የተዘጋጀውን ድጎማ ውድቅ አደረጉ።

ፕሬዝደንቱ፤ አሜሪካዊያን በነብስ ወከፍ 2 ሺህ ዶላር እንዲከፈላቸው ኮንግረሱን ጠይቀዋል።

በትዊተር ገፃቸው ላይ በለጠፉት የቪድዮ መልዕክት ነው ትራምፕ "ይህን ብኩን እና አላስፈላጊ ኮተት" የሞላውን ድጎማ ወዲያ በሉልኝ ያሉት።

ሰኞ ዕለት የአሜሪካ ኮንግረስ ያፀደቀውን ድጎማ ትራምፕ "እጅግ አሳፋሪ" ሲሉ ዘልፈውታል።

"ለስሙ የኮቪድ ድጎማ ብላችሁታል፤ ነገር ግን ስለ ኮቪድ አንዳች ነገር የለውም" ሲሉ ተደምጠዋል ተሰናባቹ ፕሬዝደንት።

በሚቀጥለው ጥር ሥልጣናቸውን ለጆ ባይደን አሳልፈው የሚሰጡት ትራምፕ ሰኞ ዕለት የቀረበላቸውን የድጎማ ጥያቄ ሰነድ ፊርማ በማሳረፍ ያፀድቁታል ተብሎ ተጠብቆ ነበር።

ነገር ግን ከዋይት ሐውስ ሆነው ባስተላለፉት መልዕክት "ገንዘቡ ችግር ላሉ አሜሪካዊያን የሚበቃ አይደለም" ብለዋል።

"ድጎማው 85.5 ሚሊዮን ዶላር ለካምቦዲያ፣ 134 ሚሊዮን ዶላር ለበርማ፣ 1.3 ቢሊዮን ዶላር ለግበጽና የግብፅ መከላከያ ኃይል [በእርግጠኝነት በዚህ ገንዘብ የሩስያ መሣሪያ ነው የሚገዙበት]፣ 25 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ለፓኪስታን ዴሞክራሲና የፆታ እኩልነት እንዲሁም ለሌሎች አገራት የያዘ ነው" ብለዋል ትራምፕ።

ትርምፕ "ለምንድነው ዲሲ የሚገኘው የኬኔዲ አርት ማዕከል ሳይከፈት 40 ሚሊዮን ዶላር ድጎማ የተመደበለት" ሲሉ ጠይቀዋል።

አልፎም ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለአሜሪካ መንግሥት ማዕከል ለሆነችው ዲሲ ሙዚየሞች መመደቡ ትክክል አይደለም ሲሉ ወርፈዋል።

"ኮንግረሱ ለውጭ አገራት በርካታ ገንዘብ ካገኘ በጣም ለሚያስፈልጋቸው አሜሪካዊያን እንዴት ይህን ማድረግ ተሳነው። ይህ የእነሱ ጥፋት አይደለም፤ የቻይና እንጂ" ብለዋል ትራምፕ በቪድዮ መልዕክታቸው።

"ኮንግረሱ ለአሜሪካዊያን በነብስ ወከፍ 600 ዶላር ሲል የመደበውን አስቂኝ ድጎማ ወደ 2 ሺህ [ለጥንዶች 4 ሺህ] ከፍ እንዲያደርግ እጠይቃለሁ።

"በተጨማሪም አላስፈላጊ የሆኑ ድጎማዎችን አስወግዶ የመጨረሻ ፊርማ እንዳሳርፍ ያቅርብልኝ። አለበለዚያ ቀጣዩ መንግሥት ነው የኮቪድ ድጎማ የሚያፀድቀው።"

የትራምፕ አስተያየት በርካታ ፖለቲከኞችን አስደንግጧል።

ለወራት ሲያከራክር የቆየው የኮቪድ-19 ድጎማ ድጋሚ ሌላ ውጥንቅጥ አግኝቶታል።

ዴሞክራቶችና ሪፐብሊካኖች በዚህ ጉዳይ ከባለፈው ሐምሌ ጀምሮ ሲሟገቱ ቆይተዋል።

ነገር ግን ድጎማው በርካታ አጠርጣሪና ከኮቪድ-19 ጋር ግንኙነት የሌላቸው አንቀፆች አዝሏል ሲሉ የአሜሪካ መገናኝ ብዙሃን ተችተውት ነበር።

ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ይህ ድጎማ ቅድመ ክፍያ ነው እንጂ በቀጣይ መንግሥት ዳጎስ ያለ ድጎሞ ያዘጋጃል ብለው ነበር።

የትራምፕ ቀንደኛ ተቃዋሚ የሆኑት የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አፈ ጉባዔዋ ናንሲ ፔሎሲ "ፕሬዝደንቱ ትክክል ናቸው፤ ክፍያው 2 ሺህ ዶላር ሊሆን ይገባል" ሲሉ ተደምጠዋል።

ባፈለው ሰኞ ከሰዓታት ክርክር በኋላ የፀደቀውን ድጎማ በርካታ ሕግ አውጭዎች በውል አላነበብነውም ሲሉ አማረው ነበር።

ድጎማው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ችግር ላሉ በርካታ ሚሊዮን አሜሪካዊያን በነብስ ወከፍ ይደርሳል ተብሎ ተጠብቆ ነበር።

ባለፈው መጋቢት የአሜሪካ መንግሥት ለተቸገሩ አሜሪካዊያን የሚሆን 2.4 ትሪሊዮን ዶላር መድቦ ነበር።

አሁን ለአሜሪካዊያን የተመደበው 600 ዶላር ካለፈው ጋር ሲነፃፀር ግማሽ ያህል ነው።