አሜሪካውያን በነፍስ ወከፍ 600 ዶላር ሊሰጣቸው ነው

አሜሪካውያን በነብስ ወከፍ 600 ዶላር ሊሰጣቸው ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከወራት ጭቅጭቅ በኋላ የአሜሪካ ሕግ አውጭዎች በወረርሽኙ ምክንያት አቅማቸው ለተዳከመ አሜሪካውያን መደጎሚያ የሚሆን 900 ቢሊዮን ዶላር በጅተዋል።

በጀቱ በወረርሽኙ ምክንያት ሥራቸውን ላጡና ንግዳቸው ለተደካመ ይሆናል ተብሏል።

ከዚህ በተጨማሪ የመንግሥት ሥራዎችን የሚያግዝ 1.4 ትሪሊየን ዶላር በጀትም ተለቋል።

ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ተለቀው የነበሩ ድጎማዎች ማብቂያቸው የያዝነው ወር ነበር።

12 ሚሊዮን አሜሪካዊያን የጤና ሽፋናቸውን ሊያጡ ይችላሉ የሚል ፍራቻ አለ።

የሕዝብ እንደራሴዎችና የሴናተሮች ምክር ቤት አባላት በአዲሱ የድጎማ መርሃ ግብር ላይ ክርክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚያ በመቀጠል ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የመጨረሻ ፊርማቸውን ያሳርፉበታል።

በርካታ አሜሪካውያን ከአዲሱ ድጎማ በነፍስ ወከፍ 600 ዶላር ይደርሳቸዋል። ሥራ አጥ አሜሪካውያን ደግሞ በሳምንት ተጨማሪ 300 ዶላር ያገኛሉ።

ከድጎማው 300 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነው ለንግድ ቤቶች የሚሰጥ ነው።

የተቀረው ደግሞ ክትባት ለማከፋፈል፣ ለትምህርት ቤትና የቤት ኪራይ መክፈል ላልቻሉ ነው ተብሏል።

ድጎማውን ይፋ ያደረጉት ሪፐብሊካኑ የሴኔት አፈ ጉባዔ ሚች ማክኮኔል ናቸው።

ዴሞክራቷ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲና የፓርቲ አጋሯ ቻክ ሹመር ድጎማው አቅም ለሌላቸው አሜሪካውያን 'አስፈላጊ ነው' ሲሉ ተደምጠዋል።

ዴሞክራቶች እንደሚፈልጉት ግን አልሆነላቸውም። የዴሞክራቶች ምኞት የነበረው ከድጎማው ቀንጨብ ተደርጎ ለክፍለ ግዛት አስተዳዳሪዎች እንዲሰጥ ነበር።

ሹመር፤ ድጎማው በሚቀጥለው ዓመት ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ለምናደርገው ርብርብ 'መሠረቱን ገነባ እንጂ ጣራ የለውም' ሲሉ ተችተውታል።

ዴሞክራቶች ጆ ባይደን ሥልጣን እስኪጨብጡ ቸኩለዋል።

በፈረንጆቹ ጥር 20 መንበሩን ከትራምፕ የሚረከቡት ባይደን ተጨማሪ ድጎማ ያፀድቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የአሜሪካ ኮንግረስ ባለፈው አርብ ድጎማውን ያረቃል ተብሎ የነበረ ቢሆንም የፖለቲከኞች ክርክር ቅዳሜና እሁድ ቀጥሎ ውሏል።

ክርክሩ ለበርካታ ወራት በመቆየቱ የዶናልድ ትራምፕ መንግሥት ድጎማ ሳያፀድቅ ይህን የፈረንጆች ዓመት ያገባድዳል ተብሎ ተፈርቶ ነበር።

ባፈለው መጋቢት የአሜሪካ መንግሥት ለዜጎቼ ይሆናል ብሎ 1.4 ትሪሊየን ዶላር መድቦ ነበር።

በወቅቱ አሜሪካውያን 1200 ዶላር በነፍስ ወከፍ ተከፍሏቸዋል። ሥራ አጦች ደግሞ በሳምንት 600 ዶላር አግኝተዋል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ አሜሪካን ማናወጥ ከጀመረ ወዲህ 20 ሚሊዮን አሜሪካውያን የዕለት ጉርሳቸው ምንጭ ከሆነው የሥራ ገበታቸው ተፈናቅለዋል።

ነገር ግን ከዚያ በኋላ ባለው ጊዜ ግማሽ ያህሉ መልሰው ሥራቸውን አግኝተዋል።

ባለፉት 5 ወራት አሜሪካ ውስጥ የድህነት መጠኑ 11.7 ደርሷል። በአሁኑ ወቅት ከ8 ሚሊዮን በላይ አሜሪካውያን በድህነት ይኖራሉ።

አሜሪካ ባለፉት 60 ዓመታት ይህን የመሰለ የድህነት አዘቅት አይታ አታውቅም።