በሳፋሪኮም የሚመራው ጥምረት ከወራት በኋላ በኢትዮጵያ አገልግሎት እንደሚጀምር አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በቅርቡ የኢትዮጵያ ቴሌኮምን ፈቃድ ያሸነፈው "ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ" የተሰኘው የኩባንያዎች ጥምረት ከወራት በኋላ በኢትዮጵያ አገልግሎት እንደሚጀምር አስታውቋል።
በኬንያው ሳፋሪኮም የሚመራው ጥምረት በትናንትናው ዕለት ግንቦት 16፣ 2013 ዓ. ም ይፋዊ በሆነው ድረ ገፁ ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ የሚሰጠው የቴሌኮም አገልግሎት ከመጪው ዓመት ጥር 2014 ዓ. ም በኋላ ይጀምራል ብሏል።
ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ የተሰኘው ይህ ጥምረት በዘርፉ አሉ የሚባሉ ስመ ጥር የቴሌኮም ኩባንያዎችንና ተቋማትን በቅንጅት የያዘ ሲሆን እነዚህም ሳፋሪኮም፣ ቮዳኮም ግሩፕ፣ ቮዳፎን ግሩፕና ሱሚቶሞ ኮርፖሬሽንና ሲዲሲ ግሩፕ ናቸው።
ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በፊት የቴሌኮም ዘርፉን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት እንደምታደርግ ካሳወቀች በኋላ ሁለት ፈቃዶችን ለዘርፉ ተሳታፊዎች በጨረታ ማቅረቧን ተከትሎ ሁለት ተቋማት በጨረታው ተሳታፊ መሆናቸውን ማሳወቃቸው ይታወሳል።
በዚህም መሠረት የተለያዩ ኩባንያዎች ጥምረት የሆነው ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ የተባለው ተቋም ከፍተኛውን 850 ሚሊዮን ዶላር በማቅረብ በጨረታው ተመራጭ ሲሆን ሁለተኛው ፈቃድ ሳይሰጥ ቀርቷል።
ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ የተሰኘው ጥምረት የተመሰረተው በአገሪቱ ላይ የምጣኔ ሀብትና ማኅበራዊ ለውጦችን ለማምጣት አንደሆነ የጠቆመው መግለጫው፤ በዚህም መሰረት ትብብሩ ዋጋው ተመጣጣኝ የሆነ የሞባይልና የኢንተርኔት አገልግሎት በመስጠት ሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያንን ባካተተ መልኩ ጥራት ያለው የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ ይፈጠራል ብሏል።
ጥምረቱ ለኢትዮጵያ የዲጂታል ሽግግር ድጋፍ እንደሚያደርግና የዜጎችንም ሕይወት በበጎ መልኩ እንደሚቀይር ተስፋ መጣሉንም መግለጫው አስረድቷል።
ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች አንዱ የሆነው ኢትዮቴሌኮም ገቢው ትርፋማ ከሚባሉ ድርጅቶች አንዱ ቢሆንም ከሌሎች የቀጠናው ኩባንያዎች ጋር ሲወዳዳር ዝቅተኛ ነበር ይላሉ በዘርፉ ያሉ ተንታኞች።
ኢትዮጵያ ኢትዮቴሌኮምን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን ድርሻ ለመሸጥ የወሰነችው በዋነኝነት ያላትን ከፍተኛ ዕዳ ለመክፈል እንደሆነ ተንታኞች የሚናገሩ ሲሆን፤ በተጨማሪነት የቴሌኮምን ተደራሽነት ለመጨመርና አገልግሎቱን ለማቀላጠፍ እንደሆነም ይጠቀሳል።
በውጭ ኩባንያዎች ከሚያዙት ሁለቱ የቴሌኮም ፈቃዶች በተጨማሪ ዋነኛው የአገሪቱ አገልግሎት ሰጪ ኢትዮቴሌኮምም በሩን ለባለሀብቶች ይከፍታል። በዚህም በመንግሥት ብቸኛ ባለቤትነት ሥር የቆየው ተቋሙ በቅርቡ 40 በመቶ ድርሻውን ለውጪ ባለሀብቶች፣ 5 በመቶውን ለኢትዮጵያውያን እና 55 በመቶውን መንግሥት እንደሚይዘው ይጠበቃል።
በዓለም ላይ ካሉ አገራት የቴሌኮምን ዘርፍ ተወዳዳሪነት ከከፈቱት የመጨረሻ ከሚባሉ አገራት አንዷ እንደሆነች የጠቀሰው መግለጫው፤ አገሪቷ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት በመታገዝ ከያዘችው የምጣኔ ሀብት ማሻሻያዎች መካከል አንዱ በማድረግም ለሦስት ዓመታት ያህል የቴሌኮምን ድርሻን ለመሸጥ በሂደት ላይ ነበረች ብሏል።
እነዚህ አገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያዎች የሥራ እድልን ለመጨመር፣ ድህነትን ለመቀነስና የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ሁሉን አካታችና ዘለቄታ ባለው መልኩ ለማሳደግ ጠቃሚ ናቸው።
በርካቶች የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚ ሆኑ ማለት ለምጣኔ ሀብቱ መመንደግ እንደሚመጣ ያሰመረው መግለጫው በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሥራ እድሎች ሊፈጠሩ እንደሚችሉም ጠቁሟል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት የመጀመሪያውን ፈቃድ ያገኘው የውጭ ተቋም በርካታ ጥቅሞችን ለአገሪቱና ለሕዝቧ ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል። በተለይ በየጊዜው እያደገ ከመጣው የሥራ ፈላጊ ወጣት ቁጥር አንጻር አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የተነገረ ሲሆን ከፍተኛ መጠን ያለው የሥራ ዕድልን ይፈጥራል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ገንዘብ ሚኒስትር አማካሪ ዶ/ር ብሩክ ታዬ ለኤኤፍፒ እንደተናገሩት፤ ተቋሙ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ እስከ 1.5 ሚሊዮን የሚደርሱ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን የሚፈጥር ሲሆን 8.5 ቢሊየን ዶላር የሚደርስ መዋዕለ ነዋይን ወደ አገሪቱ ያስገባል።
"የዲጂታል የሕይወት ዘይቤ ለመፍጠር የቴሌኮም ኔትወርክ በመዘርጋት ከኢትዮጵያውያን ጋር ለመሥራት እድል በማግኘታችን ደስተኞች ነን። በባለፉት ዓመታት የዲጂታል ሽግግርን ኃያልነትና በደንበኞቻችን ላይ ያመጣውን ተፅእኖ ተረድተናል። በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የሥራ ባለድርሻዎች ጋር በመሥራት ተመሳሳይ ሽግግር ለማምጣት እንደምንችልም እናምናለን" በማለት የሳፋሪኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፒተር ንዴግዋ ተናግረዋል።
ከ120 ዓመታት በኋላ በአገሪቱ በብቸኝነት ተይዞ የነበረው የቴሌኮም ዘርፍ ፈቃድ መሰጠትን ተከትሎ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ "ታሪካዊ ውሳኔ" ብለውታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመረጠው ተቋም ከፍተኛ የፈቃድ ክፍያ ዋጋ እና አስተማማኝ የመዋዕለ ነዋይ ፍሰት ዕቅድ እንዳቀረበ ጠቅሰው ይህም "እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ ከተደረጉት የውጪ ቀጥተኛ የዋዕለ ነዋይ ፍሰቶች ብልጫ እንዳለው" በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
የቮዳኮም ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሻሜል ጆሱብ በበኩላቸው "ጥምረቱ አሻጋሪ የሚባል የቴክኖሎጂ አገልግሎትን በማቅረብ ጥሩ ልምድ ያካበተ ነው። በተለይም በጤና፣ በትምህርትና በግብርና ዘርፉ ጥራቱን የጠበቀ የቴሌኮም ኔትወርክ በመገንባት ስም የገነባ ነው። በኢትዮጵያውያን ሕይወትም ላይ መጠነ ሰፊ የዲጂታል አካታችነትን በማስተዋወቅ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት እንፈልጋለን። ይህም አካታችነት ቮዳኮም በ2025፤ 100 ሚሊዮን አፍሪካውያን የዲጂታል ግንኙነት እንዲኖራቸው ቃል የገባው ነው" ብለዋል።
የጥምረቱ አባል የሆነው የሲዲሲ አፍሪካ ኃላፊ አቶ ትንቢተ ኤርሚያስ በበኩላቸው "ዘመናዊ፣ የተረጋጋና የሚመነደግ ምጣኔ ሀብት የሚገነባው አስተማማኝ በሆነና ተመጣጣኝ ዋጋ ባለው የዲጂታል መሰረተ ልማት ነው" ብለዋል።
በተጨማሪም፤ "ለዓለም አቀፉ ንግድ አቅርቦት ወሳኝ ነው። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ መሰረታዊ የሚባሉ የምጣኔ ሀብት ዕድሎችን ለአስር ሚሊዮን ኢትዮጵያን ለመፍጠር ምቹ የሆነ ኔትወርክ ለመዘርጋት ዝግጁ ነን። ይህም ለከተሜው ነዋሪ፣ ለአርሶ አደሮች፣ ከትልቅ የንግድ ተቋማት እስከ ትንንሾቹ ድረስ ዕድልን የሚፈጥር ነው። ለመላው አገሪቷም ትልቅ ዜና ነው" ብለዋል።
በመግለጫው ላይ የጥምረቱ አባላት የሆኑት የቮዳፎን ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኒክ ሪድ፤ በአገሪቱ ውስጥ ያለው ከፍተኛ የምጣኔ ሀብትና ልማት ላይ አዎንታዊ ሚና መጫወት እንደሚፈልጉ መልዕክታቸው ሰፍሯል።
በተመሳሳይም የሱሚቶሞ ኮርፖሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንትና ዋና የዲጂታል ኃላፊ ቶሺካዙ ናምቢ፤ ኩባንያቸው በተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች ቢሳተፍም ሚዲያና ዲጂታል ዘርፉ ጉልህ ስፍራ የሚሰጡት እንደሆነ ገልፀው፤ በጃፓንና በተቀረው እስያ ያለውን ልምዳቸውን እንዲሁም የመጠቁ የዲጂታል ሽግግሮችንም ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት እንደሚፈልጉ መናገራቸው ሰፍሯል።












