የኤል ሳቫዶሩ ፕሬዝደንት ቢትኮይንን ሕጋዊ ለማድረግ አቅደዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአል ሳልቫዶር ፕሬዝደንት ቢትኮይን የተባለው ክሪፕቶ ከረንሲ ሕጋዊ እንዲሆን እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
የፕሬዝደንቱ ሐሳብ በኮንግረሱ ከፀደቀ ማዕከላዊ አሜሪካዊቷ ሃገር 'ዲጂታል ከረንሲ' ወይም መገበያያን ሕጋዊ በማድረግ የመጀመሪያ ሃገር ትሆናለች።
የፕሬዝደንቱ ዕቅድ ከተሳካ ቢትኮይን ከአሜሪካ ዶላርና ከኤል ሳልቫዶር ኦፊሴላዊ ኖት እኩል መገበያያ ይሆናል ማለት ነው።
ፕሬዝደንት ናይብ ቡኬሌ እንደሚሉት ቢትኮይን በሌላው ዓለም የሚኖሩ ሳልቫዶሪያዊያን ወደ ሃገራቸው በቀላሉ ገንዘብ እንዲልኩ ያስችላል ይላሉ።
"ቢትኮይንን ሕጋዊ ማድረግ ሥራ ይፈጥራል፤ እንዲሁም በሺዎች ለሚቆጠሩ በኢ-መደበኛ ሥራ ለተሰማሩ አማራጭ ይሆናል" ሲሉ ፕሬዝደንቱ ፍሎሪዳ በነበረው የቢትኮይን ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።
ፕሬዝደንቱ አክለው ቢትኮይን ኢንቨስትመንትን እንደሚያበረታታ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ቡኬሌ አዲሱን ረቂቅ ሐሳብ በሚቀጥለው ሳምንት ለኮንግረስ እንደሚልኩ አሳውቀዋል።
ረቂቁ ከፀደቀ 70 በመቶ ለሚሆኑ የባንክ ሒሳብ ለሌላቸው ሳልቫዶሪያዊያን መፍትሄ ይሆናል ይላሉ ፕሬዝደንቱ።
የኤል ሳልቫዶር ምጣኔ ሃብት ከውጭ በሚላክ ገንዘብ ላይ ጥገኛ ሲሆን ከሬሚታንስ የሚገኘው ገቢ 20 በመቶ አጠቃላይ የሃገር ውስጥ ምርትን ይሸፍናል።
ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሳልቫዶሪያዊያን ከሃገራቸው ውጭ ይኖራሉ። በዓመት እስከ 4 ቢሊዮን ዶላር ድረስ ወደቤት ይልካሉ።
ሰዎች ገንዘብ ወደ ቤታቸው ሲልኩ የመላላኪያ ገንዘብ ይከፍላሉ፤ ቤት እስኪደርስም ቀናት ሊወስድበት ይችላል።
"ይህ ጉዳይ የሚሊዮኖችን ሕይወትን ያሻሽላል" ይላሉ ቡኬሌ። ፕሬዝደንቱ አዲሱ ፖሊሲ እንዴት እንደሚሠራ ያሉት ነገር የለም።
ቢትኮይን የተሰኘው ዲጂታል መገበያያ መሬት ላይ ካለው ምጣኔ ሃብት ጋር ግንኙነት የሌለው ሲሆን ባለፉት ወራት ዋጋው ወደላይና ወደታች ሲዋዥቅ ነበር።
ምን እንኳ ኤል ሳልቫዶር ቢትኮይንን ሕጋዊ ለማድረግ ብታቅድም አዲሱ ከረንሲ እንዴት ሥራ ላይ እንደሚውል በውል የሚታወቅ ነገር የለም።












