ቲቢ ጆሽዋ፡ ታዋቂው የሐይማኖት ሰባኪ 'በጥላቻ ንግግር' ምክንያት የዩቲዩብ አካውንታቸው ታገደ

ቲቢ ጆሽዋ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታዋቂው ናይጄሪያዊ የሐይማኖት ሰባኪ ቲቢ ጆሽዋ ከጥላቻ ንግግር ጋር በተያያዘ ቅሬታ ቀርቦባቸዋል በማለት ዩቲዩብ የግል አካውንታቸውን ማገዱን አስታወቀ።

ቅሬታውን ያቀረበው አንድ ገለልተኛ የሰብአዊ መብት ተሟጋች የኢቫንጀሊካን ሐይማኖት ሰባኪውን ሰባት የሚሆኑ የዩቲዩብ ቪዲዮዎች ከተመለከተ በኋላ በሁሉም ላይ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያንን ለመፈወስ ጸሎት ሲያደርግ ነበር ብሏል።

ፌስቡክም ቢሆን የሐይማኖት ሰባኪውን የቲቢ ጆሽዋ አንድ ቪዲዮ አጥፍቶታል። በቪዲዮው ላይ ቲቢ ጆሹዋ "እርኩስ መንፈስ" ለማስወጣት በማለት አንዲት ሴትን በጥፊ ሲመታ ይታያል።

የሐይማኖት ሰባኪው በበኩላቸው የዩቲዩብን ውሳኔ በመቃወም ቅሬታቸውን አሰምተዋል። የዩቲዩብ አካውንታቸውም 1.8 ሚሊየን ተከታዮች አሉት።

ቲቢ ጆሽዋ በአፍሪካ በእጅጉ ከሚታወቁት ኢቫንጀሊካል የሐይማኖት ሰባኪዎች መካከል አንዱ ሲሆኑ በርካታ ፖለቲከኛ ተከታዮች አሏቸው።

መቀመጫውን በዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው 'ኦፕንዴሞክራሲ' የተሰኛው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድን እንዳለው የሐይማኖት መሪው በዩቲዩብ ቻናላቸው ከለጠፉት ቪዲዮች መካከል ሰባት የሚሆኑት ከአውሮፓውያኑ 2016 እስከ 2020 ባሉት ዓመታት የተለቀቁ ናቸው።

"በቪዲዮዎቹም ላይ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች እንደ በሽተኛ ተቆጥረው ጸሎት ሲደረግላቸው ነበር ብሏል" ሲል ነው ቡድኑ ቅሬታውን ያቀረበው።

የዩቲዩብ ቃል አቀባይ እንደተናገሩት የሐይማኖት ሰባኪው ቪዲዮዎች የድርጅቱን ፖሊሲ የሚጣረሱ ናቸው። "በፖሊሲያችን መሰረት አንድ የትኛውም ጾታዊ አመለካከት ያለውን ግለሰብ እንደ በሽተኛ፣ አካል ጉዳተኛ አልያም የበታች አድርጎ ማቅረብ የተከለከለ ነው" ብለዋል።

የቲቢ ጆሽዋ ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ ላይ የተቀመጠው መልዕክት "ከዩቲዩብ ጋር ለረጅም ጊዜ ጥሩ ግንኙነት ነበረን። አሁንም ቢሆን የተወሰነው ውሳኔ በችኮላ ነው" ይላል።

ቅሬታ ከቀረበባቸው ቪዲዮዎች መካከል በአንደኛው ላይ ቲቢ ጆሽዋ ስሟ ያልተጠቀሰ አንዲት ሴትን ቢያንስ 16 ጊዜ በጥፊ ሲመቷት ይታያል።

"የሚረብሽሽ መንፈስ አለ። መንፈሷ ሴት ናት። እራሷን አንቺ ውስጥ አስገብታለች" ሲሉም ይሰማሉ።

ቪዲዮው በዩቲዩብ ላይ ከ1.5 ሚሊዮን ጊዜ በላይ የታየ ሲሆን ሴትዮዋ በሕዝብ ፊት ቆማ እንደተፈወሰች ትናገራለች። "መንፈሷ ለቅቃኝ ሄዳለች" በማለት የሐይማኖት ሰባኪው ጸሎት እንደረዳት ትናገራለች።

አክላም "ከዚህ በኋላ ለሴቶች ምንም አይነት ስሜት የለኝም፤ ከዚህ በኋላ የምወደው ወንዶችን ብቻ ነው" ስትል ትሰማለች ትላለች።