የአፍሪካ ሚሊየነሩ ሰባኪ ‘ነብይ’ ቡሺሪ ከደቡብ አፍሪካ አመለጠ

የፎቶው ባለመብት, Ecg ministries
በአፍሪካ የናጠጠ ሀብታም ነው የሚባለው አወዛጋቢው ሰባኪ ነብይ ሸፐርድ ቡሺሪ ከደቡብ አፍሪካ አመለጠ። ቡሺሪ በደቡብ አፍሪካ በቁጥጥር ሥር ውሎ የፍርድ ሂደቱን እየተከታተለ ነበር።
አወዛጋቢው ቡሺሪ በደቡብ አፍሪካ በቁጥጥር ሥር ውሎ የነበረው ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ ነበር።
የተመሰረተበት ክስ ደግሞ ከማጭበርበርና ከሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ጋር የተያያዘ ነበር። ይህን የፍርድ ሂደት በመከታተል ላይ ሳለ ነው በድንገት ከደቡብ አፍሪካ አምልጦ ወደ ትውልድ አገሩ ማላዊ የገባው።
ሚሊየነሩ ነብይ ቡሺሪ እንዴት ሊያመልጥ ቻለ የሚለው ደቡብ አፍሪካዊያንን እያነጋገረ ሲሆን ምናልባት የማላዊ ፕሬዝዳንት በሚጠቀሙበት ቻርተርድ ጄት አውሮፕላን እንደሸሸ ተገምቷል።
አንዳንድ ዘገባዎች እንዲያውም የማላዊው ፕሬዝዳንት ላዛረስ ቸክዌራ ናቸው ሸሽገው በግል አውሮፕላናቸው ከደቡብ አፍሪካ ያስወጡት ይላሉ።
የማላዊ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ግን ይህንን ክስ አስተባብሏል።
የሚሊየነሩ ሰባኪ ሼፐርድ ቡሺሪ ጉዳይ በደቡብ አፍሪካና በማላዊ መካከል የዲፕሎማሲ ቅራኔ ሊፈጥር ይችላል የሚል ስጋት አለ።
የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ማላዊ ተጠርጣሪውን ከነባለቤቱ አሳልፍ እንድትሰጣት እንደምትጠይቅ ተናግራለች። ደቡብ አፍሪካና ማላዊ ወንጀለኞችን አንዱ ለሌላው አሳልፎ የመስጠት ስምምነት አላቸው።
አወዛጋቢውን ቡሺሪን በተመለከተ ማላዊ አሳልፋ ተሰጠዋለች ወይ ተብለው የተጠየቁት የማላዊ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አይዘናወር ምካካ አገራቸው "ማላዊ የዜጎቿን ደኅንነት የመጠበቅ ግዴታ አለባት" በማለት ድፍን ያለ ምላሽ ሰጥተዋል።
ሼፐርድ ቡሺሪ ያመለጠው ከባለቤቱ ሜሪ ቡሺሪ ጋር በመሆን ነው። ቡሺሪና ባለቤቱ የዋስ መብት ተከብሮላቸው ነገር ግን ከደቡብ አፍሪካ እንዳይወጡ በሚል ነበር የፍርድ ሂደታቸውን ውጪ ሆነው ሲከታተሉ የነበረው።
ሸፐርድ ቡሺሪ "ያመለጥኩት የግድያ ዛቻ ስለደረሰብኝ ሕይወቴን ለማትረፍ ነው" ብሏል። ጨምሮም "የደቡብ አፍሪካ መንግሥት የሚገባኝን ጥበቃ አላደረገልኝም" ሲል ከሷል።
ቡሺሪ ኢንላይትድ ክርስቲያን ጋዘሪንግ የተባለው ቤተክርስቲያን መሥራችና ባለቤት ነው። ከ50 ሺህ ሰዎች በላይ በሚገኙባቸው ስታዲየሞች ትልልቅ የሰበካና የተአምራት አገልግሎት በመስጠት በአፍሪካ እውቅ ሰባኪ ነው። ከዚህም ባሻገር የቴሌቪዥን የስብከት አገልግሎት ይሰጣል።
ሼፐርድ ቡሺሪ በአፍሪካ እጅግ አወዛጋቢ ከሚባሉት ሰባኪዎች አንዱ ሲሆን በአየር ላይ እራመዳለሁ፣ ኤችአይቪን ፈውሻለሁ፣ ካንሰርንም እፈውሳለሁ፣ ዓይነ ሥውራንን አበራሉሁ፣ ሽባዎች ቆመው እንዲራመዱም አደርጋለው ይላል።
ቦስዋና ግለሰቡ አጭበርባሪ ነው በሚል አገሯ እንዳይገባ አግዳው ታውቃለች።
ቡሺሪ ከመንፈሳዊ አገልግሎቱ ባሻገር ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ውስጥ የተሰማራ አፍሪካዊ ነው። የተወለደውና ያደገው በማላዊ ቢሆንም ወደ ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በማቅናት ኢንላይትንድ ክርስቲያን ጋዘሪንግ ቤተክርስቲያን ከፍቶ እጅግ አነጋጋሪው አፍሪካዊ ሰባኪ ለመሆን በቅቷል።
ቡሺሪ ስታዲየም ሙሉ ለተሰበሰቡ ድሆች ተአምራዊ ቅባት ቸብችቦ አላግባብ በልጽጓል በሚልም ክስ ይቀርብበታል።
አሁን በደቡብ አፍሪካ የቀረበበት የማጭበርበር ገንዘብ መጠን 102 ሚሊዮን ራንድ ወይም ከ6 ሚሊዯን ዶላር በላይ ይገመታል።















