ቦትስዋና የቡሺሪ ቤተ-ክርስቲያንን ዘጋች

የፎቶው ባለመብት, Shepherd Bushiri/Facebook
ቦትስዋና በአየር ላይ መራመድ እችላለሁ የሚሉትን አወዛጋቢውን እራሳቸውን ነብይ ብለው የሚጠሩትን የማላዊ ዜጋ ቤተ-ክርስቲያን ዘጋች።
''የታአምር ገንዘብ'' ከተሰኘ ድርጊት ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ስጋት ምክንያት የሃገሪቱ መንግሥት የእረኛ ቡሺሪ ቤተ-ክርስቲያን እድትዘጋ ማድረጉን አረጋግጧል።
ግለሰቡ ወደ ቦትስዋና እንዳይገቡ ከተከለከሉ ከወራት በኋላ የተወሰደው የመዝጋት እርምጃን ቤተ-ክርስቲያኗን በመቃወም አቤቱታ እንዳቀረበች ተዘግቧል።
ቡሺሪ ሊካሄድ በነበረ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ እቅድ የነበራቸው ሲሆን፤ የቦትስዋና ሚኒስትር ኤድዊን ባትፁ ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ላይ እንዳሳወቁት በአሁኑ ወቅት ነዋሪነታቸውን ደቡብ አፍሪካ ያደረጉት ቡሺሪ የመግቢያ ቪዛ እንደሚያስፈልጋቸው ተነግሯቸዋል።
ነገር ግን ማንኛውም የማላዊ ዜጋ ወደ ቦትስዋና ሲገባ ቪዛ አያስፈልገውም ነበር።
የቦትስዋና ጋዜጣ የቤተ-ክርስቲያኗ የምዝገባ ፈቃድ መሰረዙን የሚገልፅ ደብዳቤ እንደተፃፈ ዘግቦ፤ መንግሥትም ቤተክርስቲያኗ እስከ መጨረሻው መዘጋቷን አሳውቋል።
ጋዜጣው ጨምሮ እንደዘገበው ቤተ-ክርስቲያኗ የተዘጋችው ''የታአምር ገንዘብ'' የተሰኘውንና ገንዘብ ምትሃት በሚመስል መንገድ የሚገኝበትን ሁኔታ በምዕመኑ መካከል በማስፋፋቷ ነው። ይህም የሃገሪቱን ሕግ የሚቃረን ድርጊት ነው ብሏል።
ቡሺሪ 2.3 ሚሊዮን የፌስቡክ ወዳጅ ያላቸው ሲሆን በጆሃንስበርግ በሚገኝ ትልቅ ስታዲየም ሙሉ ሕዝብ የታደመበት የአዲስ ዓመት ዋዜማ ዝግጅት ነበራቸው።
ነገር ግን ቤተ-ክርስቲያናቸው እስካሁን ቦትስዋና ውስጥ ስለገጠማት ችግር በይፋ ምላስ አልሰጠችም።
በተቀማጠለ የአኗኗር ዘይቤያቸው የሚታወቁት የቤተክርስቲያኗ መሪ ቡሺሪ፤ በበርካታ የአፍሪካ ሃጋራት ውስጥ ቤተ-ክርስቲያናቸውን በማስፋፋት የተሳካላቸው ናቸው።
ባለፈው ዓመት ከቡሺሪ ጋር የእራት ግብዣን ለመታደም የሚፈልጉ ሰዎችን ከ80 እስከ 2ሺህ ዶላር አስከፍለዋል ተብሎ በደቡብ አፍሪካው ኒውስ24 ከተዘገበ በኋላ ተቃውሞ ተቀስቅሶባቸዋል።












