የአሜሪካ ምርጫ፡ በሺዎች የሚቆጠሩ የትራምፕ ደጋፊዎች በዋሽንግተን ዲሲ ሰልፍ አካሄዱ

የትራምፕ ደጋፊዎች ያደረጉት ሰልፍ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የምርጫው ውጤት ተጭበርብሯል የሚለውን አስተያየታቸውን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው በዋሽንግተን ዲሲ በመሰባሰብ በውጤቱ ላይ ያላቸውን ተቃውሞና ለፕሬዝዳንቱ ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።

የአሜሪካን ባንዲራ ያነገቡ ሰልፈⶉች በጎዳናዎች ላይ ተሰባስበው የታዩ ሲሆን አንዳንዶቹ የጭንቅላት መከላከያ እና የጥይት መከላከያ ጃኬትም ጭምር አድርገው እንደነበር ተገልጿል።

ቀደም ብሎ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመኪናቸው ሲኣልፉ ደጋፊዎቻቸው መንገዱን ከብበው ድጋፋቸውን ገልጸውላቸው ነበር።

በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ተቀናቃኝ የነበሩት ጆ ባይደን ባሳለፍነው ጥቅምት 24 ላይ ነበር ማሸነፋቸው የተረጋገጠው።

አርብ ዕለት ደግሞ ጆ ባይደን በጎርጂያ ግዛት አብላጫውን ድምጽ በማግኘት ከ1992 በኋላ በአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ታሪክ ከዴሞክራቲክ ፓርቲ ተወክሎ በዚኢህ ግዛት ያሸነፈ የመጀመሪያው ሰው መሆን ችለዋል።

ተመራጩ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እስካሁን በጠቃላይ 306 ድምጽ ያገኙ ሲሆን ለማሸነፍ ማግኘት ይጠበቅባቸው የነበረው ደግሞ 270 ነበር።

ነገር ግን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአንዳንድ ቁልፍ ግዛቶች ላይ በምርጫ ውጤት ላይ ሕጋዊ ጥያቄዎችን አነሳለሁ እያሉ ነው። የትራምፕ ጠበቃ ሩዲ ጁሊያኒ ለፎክስ ኒውስ ሲናገሩ ትራምፕ ሽንፈቱን ቢቀበሉ ስህተት ነው ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ፤ "ይህ ምርጫ ቢያንስ ሦስት ወይም አራት እንደውም 10 በሚሆኑ ግዛቶች ስለመሰረቁ ማስረጃ አለ።" ይላሉ ጠበቃው። ጨምረውም የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ምርጫው ስለመጭበርበሩ የሚያረጋግጡ "ጠንካራ ማስረጃዎችን" ይዞ ይቀርባል በማለት አስተያየታቸውን መስጠታቸው የሚታወስ ነው።

ፕሬዝደንት ትራምፕ ደጋፊዎች ከዋይት ሀውስ በስተምስራቅ በኩል በሚገኘው ከ 'ፍሪደም ፕላዛ' አቅራቢያ በመሰባሰብ ወደ የአሜሪካ ጠቅላእ ፍርድ ቤት ሊያመሩ ነበር።

ሰልፈⶉቹም የፕሬዝዳንቱ መለያ የሆነችውን 'አሜሪካን በድጋሚ ታላቅ እንደርጋለን' የምትለውን አረፍተ ነገር በትልልቅ ጨርቆችና ወረቀቶች ላይ ጽፈው ሲንቀሳቀሱ ነበር።

አርብ ዕለት ፕሬዝዳንቱ በመንገድ ሲያልፉ ቆም ብለው ደጋፊዎቻቸውን ሰላም ሊሉ እንደሚችሉ ጠቁመው የነበረ ሲሆን ቅዳሜ ዕለት ግን ወደ ጎልፍ መጫወቻ ሜዳቸው ሲሄዱ መኪናቸውን ሳያቆሙ አልፈው ሄደዋል።

ከአፍታ በኋላ ደግሞ ፕሬዝዳንቱ በትዊተር ገጻቸው በኩል ብቅ ብለው 'እናሸንፋለን' የሚል መልዕከት ያጋሩ ሲሆን ከደጋፊዎቻቸው ጋር በድጋሚ ይገናኙ አይገናኙ ግን ያሉት ነገር የለም።

በሰልፉ ላይ ከተስተዋሉ ነገሮች ጎልቶ የወጣው ደግሞ አብዛኛዎቹ ተሳታፊዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ አለማድረጋቸው ነው።

ከሳምንት በፊት ደግሞ የጆ ባይደንን ድል ተከትሎ በተለያዩ ከተሞች ነዋሪዎች ደስታ ፈንቅሏቸው ወደ አደባባይ ወጥተዋል፡፡

በበርካታ የአሜሪካና ከአሜሪካ ውጭ ባሉ ከተሞችም ጭምር ነበር ድግሱ የተጧጧፈው፡፡ እነዚህ ድግሶች ብዙዎቹ ታስቦባቸው የተሰናዱ ሳይሆኑ መገናኛ ብዙኃን የባይደንን አሸናፊነት መናገራቸውን ተከትሎ በግብታዊነት ሕዝብ ደስታ ፈንቅሎት አደባባይ በመውጣት የተከበሩ ነበሩ።

ኒውዮርክ ሎስ አንጀለስ በዚህ ረገድ የቀደማቸው የለም፡፡ በአጭር ደቂቃ ውስጥ አደባባዮቻቸው በሕዝብ ተሞልተዋል፡፡

በኒውዮርክ ታይምስ ስኩዌር አደባባይ ሰዎች ለመገናኘትና ድሉን ለማጣጣም አዋጅና መጠራራት አላስፈለጋቸውም፡፡ በደቂቃዎች ውስጥ አደባባዩ በሕዝብ ታጨቀ፡፡

በትራምፕ መኖርያና ቢሮ (ዋይትሐውስ) ደጃፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ዜጎች ድሉን ተከትሎ አደባባይ ወጥተዋል፡፡ ብዙዎቹ የአፍ-አፍንጫ ጭምብል ማጥለቃቸውን በማየት ብቻ የማን ደጋፊ እንደሆኑ መናገር ይቻላል፡፡

ዋይትሐውስ ከድሉ ቀደም ብሎ ረብሻ ሊቀሰቀስ ይችላል በሚል ዘለግ ያለ አጥር እንዲታጠር ተደርጎ ነበር፡፡ ሆኖም የድጋፍ ሰልፉ ሰላማዊ ሆኖ አልፏል፡፡