ሀይማኖት፡ ሀብታቸው ከ130 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመተው ናይጄሪያዊ ፓስተር

ናይጄሪያዊ ፓስተር ኤኖክ አዴቦዬ

የፎቶው ባለመብት, PASTOR E. A. ADEBOYE

ኤኖክ አዴቦዬ ናይጄሪያዊ ፓስተር ናቸው። ‘ዳዲ ጎ’ በሚል ቅጽል ስም ይጠራሉ።

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሏቸው እኚህ የ78 ዓመት ፓስተር፤ በሚሰጧቸው ፆተኛ አስተያየቶች በበርካቶች ይተቻሉ።

ሬድመንድ የተባለ ቤተ ክርስቲያንን ለ40 ዓመታት መርተዋል። ቤተ ክርስቲያኑ በሳቸው አስተዳደር ስር እንዳደገ ይነገርለታል።

በብዛት የክርስትና እምነት ተከታዮች በሚገኙበት ደቡባዊ ናይጄሪያ ውስጥ የሬድመንድ ቤተ ክርስቲያን የሌለበት አካባቢ ለማግኘት ያስቸግራል።

ሁለት የሬድመንድ ቤተ ክርስቲያኖች የሚገኙባቸው ጎዳናዎችም አሉ። በየቦታው በእርግብ የሚመሰለውን ይህን ቤተ ክርስቲያን ማየት የተለመደ ነው።

ሆኖም ግን ፓስተሩ ስለ ትዳር እንዲሁም ስለ ፆታ ሚና ያላቸው አመለካከት በርካቶችን አስቆጥቷል። ናይጄሪያ ወግ አጥባቂ የሚባል አገር ቢሆንም ፓስተሩ የሚሰነዝሯቸውን አስተያየቶች የሚኮንኑ በዝተዋል።

ማብሰል የምትችል ሴት አግቡ

ፓስተሩ ባለፉት ዓሠርታት በማኅበራዊ ሚዲያዎች በንቃት ይሳተፋሉ።

ባለፈው ሐምሌ የባለቤታቸውን ልደት አስታከው “ለሴቶች ትምህርት” በሚል በማኅበራዊ ሚዲያ የጻፉት መልዕክት በትዊተር ላይ ከፍተኛ ክርክር ቀስቅሶ ነበር።

“ምንም ያህል ብትማሩና ስኬታማ ብትሆኑ ባላችሁ የቤቱ አለቃ ነው። ምን ጊዜም እንደ አለቃ ልታዩት ይገባል” ሲሉ ለ1.3 ሚሊዮን ተከታዮቻቸው ጽፈዋል።

በኢንስታግራም ገጻቸው ላይ “ባለቤቴ ምንም አይነት እቅድ ቢኖራት ሰርዢውና ከኔጋ እዚህ ቦታ እንሂድ ብላት፤ ያቀደችውን ነገር ሰርዛ እኔን ትከተለኛለች” ሲሉም ጽፈዋል።

ባለ ትዳር ልጃቸው ቢሮ ሲሄድ “ሊያያት የሚፈልግ” ጸሐፊውን እንዲያባርራት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው መጻፋቸውም አይዘነጋም።

ፓስተሩ ከአራት ዓመት በፊት ላጤ ወንዶችን “ሰነፍ ሴት አታግቡ፤ ከቤት ውጪ ለመመገብ የሚወጣ ወጪ ስለሚከብዳችሁ ማብሰል የማትችል ሴት አታግቡ” ብለው ነበር።

ይህ በቴሌቭዥን የተላለፈው ንግግራቸው ሴት የመብት ተሟጋቾችን አስቆጥቷል።

በእርግጥ የተናገሩትን የደገፉም ነበሩ። እንደ ንግድ ተቋም የሚያስተዳድሩት ቤተ ክርስቲያን አባላት ከነዚህ መካከል ይገኙበታል።

ፓስተር ኤኖክ ሴቶችን በተመለከተ ለሚሰጧቸው አስተያየቶች መጽሐፍ ቅዱስን ያጣቅሳሉ። እነዚህ ጥቅሶች በተያየ መንገድ ሊተረጎሙ እንደሚችሉ የሚከራከሩም አሉ።

“ክርስትና እና ሀይማኖቶች የወንድ የበላይነትን ማስፈጸሚያ ናቸው። ስለዚህም አንድ የሀይማኖት መሪ እንዲህ አይነት አመለካከት ቢኖረው አይገርምም” የምትለው ናይጄሪያዊቷ የክርስትና እምነት ተከታይ ጸሐፊ ማርታ ኤደም ናት።

ፓስተሩ የባለቤታቸውን ልደት አስታከው ፆተኛ አስተያየት ከሚሰጡ ይልቅ፤ ጥንዶች እርስ በእርስ እንዲከባበሩና እንዲዋደዱ መልዕክት ማስተላለፍ ይችሉ ነበር ትላለች።

መንግሥተ ሰማያትን እንድትወርሱ መባ ስጡ”

በኮሮናቫይረስ ምክንያት በርካታ ሰዎች በአንድ ቦታ እንዳይሰበሰቡ ከመወሰኑ በፊት ዘወትር እሁድ የፓስተር ኤኖክ፣ ሬድመንድ ቤተ ክርስቲያን በመቶ ሺዎች በሚቆጠሩ አማኞች ይሞላ ነበር።

ተዐምራት የሚፈልጉ፣ ዘላለማዊ ሕይወት እንሻለን የሚሉ፣ ሀጢያት የሚናዘዙ፣ ንግዳቸው እንዲጎመራ የሚመኙና ሌሎችም አማኞች ይሰባሰባሉ።

አቡጃ በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን የነበረ አንድ አማኝ “ከእግዚአብሔር ጎን መሆን እፈልጋለሁ። በእውነተኛ የክርስትና አስተምህሮት መኖር እሻለሁ። ይህንን ያገኘሁት በሬድመንድ ቤተ ክርስቲያን ነው። ምኞቴ ገነት መግባት ነው” ሲል ተናግሯል።

ሌሎች አማኞች በፓስተሩ “ቅዱስነት” እንደተማረኩ ሲናገሩ፤ “ፓስተሩ የሚያስተምሩትን ስለሚኖሩ” ወይም “ራሳቸውን ዝቅ ስለሚያደርጉ” እንደተሳቡ የሚገልጹም አሉ።

የፓስተሩን ቤተ ክርስቲያን የረገጡ አማኞች ገንዘብ ከመስጠት ወይም ከቤተ ክርስቲያኑ ቁሳ ቁስ ከመግዛት ወደ ኋላ አይሉም።

አብዛኞቹ ከደሞዛቸው 10 በመቶ አስራት ለመስጠት ፍቃደኛ ናቸው።

ፓስተሩ ከሁለት ዓመት በፊት፤ “አስራት የማይሰጥ ሰው መንግሥተ ሰማያትን አይወርሱም” ብለው ነበር።

ፓስተሩ ምን ያህል ሀብት እንዳላቸው ለማወቅ ከባድ ነው። በሳቸው የግል ንብረትና በቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብት መካከል ያለው መስመር ደብዛዛ ነው።

ሀብታቸውን ከ60 ሚሊዮን ዶላር እስከ 130 ሚሊዮን ዶላር የሚገምቱ አሉ።

ይህም አጠቃላይ ጥሪታቸውን ከአገሪቱ ታዋቂ ድምጻውያን ጋር ያቀራርበዋል። ሀብታቸው በተለያዩ አገራት ከሚኖሩ ናይጄሪያዊ እግር ኳስ ተጫዋቾች በላይ ሊሆንም ይችላል።

ቀድሞ በሌጎስ ዩኒቨርስቲ የሒሳብ መምህር የነበሩት ፓስተሩ፤ ከመገናኛ ብዙሀን ጋር ለመነጋገር ፍቃደኛ አይደሉም።

በቢራቢሮ ክራቫትና በባለ መስመር ካናቴራ የሚታወቁት ፓስተሩ፤ ከሌሎች ዘናጭ ፓስተሮች አንጻር የሳቸው አለባበስ ቆፍጠን ያለ ነው።

የሚያብረቀርቅ ጫማ አያደርጉም። ጸጉራቸውን በቅባት አያስተኙም። የአሜሪካውያን ቅላጼ የተጫነው እንግሊዘኛም አይናገሩም።

የፓስተር ኤኖክ ቤተሰቦች ድሃ ነበሩ። በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች ፓስተሩ ራሳቸውን ዝቅ እንደሚያደርጉም ይናገራሉ።

ሆኖም ግን እሳቸው ወይም ቤተ ክርስቲያናቸው ዩኒቨርስቲ፣ ጀት እንዲሁም ቅንጡ መኪኖች አሏቸው።

ፓስተሩ በፖለቲካ

ፓስተሩ ፖለቲካ ውስጥም ተሰሚነት አላቸው። መካከለኛ ገቢ ባላቸው ከተሜ ናይጄሪያውያን ዘንድ አክብሮት አትርፈዋል።

ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ሲካሄድ ተፎካካሪ ፖለቲከኞች በፓስተሩ የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ ይገኛሉ። ከፓስተሩ ጋር ይጨባበጣሉ።

ፓስተሩ ከተለያዩ የዓለም መሪዎች ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ የሚያሳዩ ፎቶዎች በድረ ገጻቸው ይገኛሉ።

እኚህ ፓስተር የተወለዱት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1942 በደቡብ ምዕራብ ናይጄሪያ ኦሱን ግዛት ነው። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሒሳብ አግኝተዋል።

1967 ላይ ከፎሊኬ አዴቦዬ ጋር ትዳር መስርተዋል።

በሬድመንድ ቤተ ክርስቲያን ፓስተር የሆኑት 1967 ላይ ሲሆን፤ በ1981 የቤተ ክርስቲያኑ የበላይ ጠባቂ ሆነዋል።